አል ሻባብ በሞቃዲሾ የሶማሊያ ባለሥልጣናት በሚያዘወትሩት ሆቴል ላይ ጥቃት ፈጸመ

በሶማሊያ ዋና ከተማ ሞቃዲሾ ውስጥ የሚገኝና የመንግሥት ባለሥልጣናት በሚያርፉበት ሆቴል ላይ አል ሸባብ ጥቃት ፈጸመ።

ቪላ ሮዝ ተብሎ በሚታወቀው ሆቴል ላይ አል ሸባብ ጥቃቱን ከፈጸመ በኋላ በወቅቱ በሆቴል ውስጥ የነበሩት የአገሪቱ አካባቢ ጥበቃ ሚኒስትር አድም አው ሂሪሲ ከጥቃቱ መተረፋቸውን ተናግረዋል።

ሌላ እውነትነቱ ያልተረጋገጠ መረጃ ደግሞ በጥቃቱ የሶማሊያ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሞሐመድ አህመድ ጉዳት እንደደረሰባቸው አመልክቷል።

ከ15 ዓመታት በላይ ሶማሊያያ ውስጥ ሲንቀሳቀስ የቆየው እስላማዊ ቡድኑ አልሸባብ ሆቴሉ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን አረጋግጧል።

ቪላ ሮዝ ሆቴል በማዕከላዊ ሞቃዲሾ ከሚገኘው የፕሬዝዳንቱ ቤት መንግሥት በቅርብ ርቀት ውስጥ የሚገኝ ነው።

ቁጥራቸው ያልታወቁ ተቀጣጣይ ቦንቦች እና መሳሪያ ያነገቡ ታጣቂዎች በጥቃቱ መሳተፋቸውን ፖሊስ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ገልጿል።

አንድ የዐይን እማኝ ከፍተኛ ፍንዳታ እና የተኩስ ልውውጥ መስማቱን ተናግሯል።

“ደነገጥን። ከቤት ሳንወጣ የተኩሱን ድምጽ ስንሰማ ነበር” ብሏል አህመድ አብዱላሂ የተባለው እና ጥቃቱ ከደረሰበት ሆቴል አቅራቢያ የሚኖረው የዐይን እማኝ።

የተወሰኑትን የመንግሥት ባለሥልጣናት የሆቴሉን መስኮቶች በመጠቀም ከጥቃቱ መታደግ መቻሉን ሞሐመድ አብዲ የተባሉ የፖሊስ መኮነን ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ሥልጣን ከተረከቡ ሦስት ወር ብቻ ያስቆጠሩት ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐመድ፣ ታጣቂ ቡደኑ በሞቃዲሾ በሚገኝ ሌላ ሆቴል ላይ በሰነዘረው ጥቃት 20 ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ አል ሸባብ ላይ በሁሉም መስክ ጦርነት ለመክፈት ቃል ገብተው ነበር።

ይሀንን ካሉ ከሁለት ወራት በኋላ በሁለት ተሽከርካሪዎች በሞቃዲሾ በሰዎች እንቅስቃሴ በተሞላ ስፍራ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት ቢያንስ ለ100 ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሆኗል።

ለዚህ ጥቃት ኃላፊነቱን በወሰደው አል ሸባብ ላይ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ የሶማሊያን ጦር እና በመንግሥት የሚደገፉ የጎሳ ሚሊሻዎችን በማዝመት ከአልሸባብ መንድሮችን እና አነስተኛ ከተሞችን ለመንጠቅ ጥረት አድርገዋል።

የአገሪቱ “መብረቅ” የተባለው የጦር ብርጌድ አል ሸባብ ላይ ሚያነጣጥር ሲሆን፣ በአሜሪካ የገንዘብ ድጋፍ ይደረግለታል።

ታጣቂ ቡድኑ የተቋቋመውን የመንግሥትን መዋቅር በማፍረስ በጥብቅ እስላማዊ ሕግጋት የሚመራ አስተደዳር በሶማሊያ የመመሰረት ግብ አለው።