ሥልጣን የለቀቁት የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶን ማን ሊተካ ይችላል?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የጀስቲን ትሩዶ የሊበራል ፓርቲ ሥልጣናቸውን እንደሚለቁ ይፋ በማድረጋቸው ለዘጠኝ ዓመታት የዘለቀው የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትርነታቸው እያበቃ ነው።
ይህ ማለት ፓርቲያቸው በቀጣይ በሚደረገው ምርጫ ፓርቲውን ወክሎ የሚወዳደር አዲስ መሪ ማፈላለግ ይኖርበታል። ፓርቲው በምርጫው ሊሸነፍ እንደሚችል የህዝብ አስተያየት መስጫዎች ጠቁመዋል።
የሊበራል ፓርቲ መሪ ለመሆን ሊወዳደሩ ይችላሉ ተብለው የሚጠበቁ ግለሰቦች የሚከተሉት ናቸው።
የቀድሞዋ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ክሪስቲያ ፍሪላንድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቶሮንቶ የፓርላማ አባል የሆኑት ክርስቲያ ፍሪላንድ በጣም ታዋቂ ከሆኑት የትሩዶ ቡድን አባላት አንዷ ናቸው። ተሰናባቹን መሪ ለመተካት ከቀዳሚ ተፎካካሪዎች መካከል ተደርገውም ይወሰዳሉ።
ለረዥም ጊዜ የጠቅላይ ሚንስትሩ ታማኝ የቅርብ ሰው እንደሆኑ ለረዥም ጊዜ ሲታዩ ቢቆዩም ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት በታህሳስ ወር የስራ መልቀቂያ አስገብተዋል።
የስልጣን መልቀቂያ ደብዳቤ ሲያስገቡ በአደባባይ ትሩዶ ላይ ትችት መሰንዘራቸው ጫናውን ከፍ አድርጎባቸው ከኃላፊነት መነሳታቸውን የማይቀር አስመስሎታል።
በምዕራብ አልበርታ ግዛት ከዩክሬናዊ እናት የተወለዱት የ56 ዓመቷ ፍሪላንድ ወደ ፖለቲካ ከመግባታቸው በፊት ጋዜጠኛ ነበሩ።
እአአ በ 2013 የአገሪቱን ምክር ቤት የተቀላቀሉ ሲሆን ከሁለት ዓመት በኋላ ፓርቲው ወደ ሥልጣን ሲመጣ የትሩዶን የንግድ ካቢኔን ተቀላቀሉ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ደግሞ ካናዳ ከአሜሪካ እና ሜክሲኮ ጋር ነጻ የንግድ ስምምነት እንድትደረስ ለማገዝ እንደገና እንድትደራደር ረድተዋል።
በኋላ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የገንዘብ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ ኃላፊነቱን ያገኘኙ የመጀመሪያዋ ሴት ሆነዋል። በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ካናዳ የሰጠችውን የገንዘብ ድጋፍ ተቆጣጥረዋል።
ባለፈው ወር ከኃላፊነት ሲለቁ ዶናልድ ትራምፕ በካናዳ ምርቶች ላይ ለመጣል ያቀዱትን የታሪፍ ስጋት በመከላከል ረገድ ትሩዶ ጠንካራ አይደሉም ሲሉ ወቅሳዋቸዋል።
ለዩክሬን የሰጡት ጠንካራ ድጋፍ በአንዳንዶች ውዳሴን አስገኝቶላቸዋል። የሃርቫርድ ምሩቅ የሆኑት የፓርላማ አባሏ በቅርቡ "መርዛማ" ተብለው በትራምፕን ከመጠራት ጀምሮ ትችትም አስተናግደዋል።
የቀድሞ ማዕከላዊ ባንክ ገዢው ማርክ ካርኒ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትሩዶ በቅርቡ የገንዘብ ሚኒስትር ለማድረግ ደረጉትን ጥረት ጨምሮ ማርክ ካርኒንን ወደ ለካቢኔያቸው ለመመልመል ለረዥም ጊዜ ጀምሮ ሲሞክሩ እንደነበር ተናግረዋል።
"ካናዳውያን በፖለቲካቸው ውስጥ ጥሩ ሰዎችን በሚፈልጉበት በዚህ ወቅት እሱ አስደናቂ ሠራተኛ ይሆናል" ሲሉ እአአ ሐምሌ 2024 በኔቶ ኮንፈረንስ ላይ ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።
የ59 ዓመቱ ካርኒ ባለፉት ወራት ለትሩዶ ልዩ አማካሪ በመሆን እያገለገሉ ሲሆን ከረጅም ጊዜ ጀምሮ የዋናው ወንበር ተፎካካሪ ተደርገው ሲቆጠሩ ቆይተዋል።
የሃርቫርድ ተመራቂው የመንግሥት ኃላፊነት ይዘው ባያውቁም በካናዳ ባንክ እና በእንግሊዝ ባንክ ከፍተኛ ኃላፊነት ላይ በማገልገል ጠንካራ የኢኮኖሚ ልምድ አላቸው።
የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ልዩ መልዕክተኛ በመሆን ባበረከቱት ሚና ደግሞ በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ ዕውቀት ጨብጠዋል። በቅርቡም የልቀት መጠንን ዜሮ የማድረግ ግብን "የዘመናችን ትልቁ የንግድ ዕድል" በማለት ጠርተውታል።
ካርኒ በሀገሪቱ ወግ አጥባቂዎች ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸው አንዳንድ የሊበራል ፖሊሲዎችን በማራመድ ይታወቃሉ። እንደ ፌዴራል የካርበን ታክስ ፖሊሲ ያሉ እና ተቺዎች ለካናዳውያን የገንዘብ ሸክም ነው የሚጠሩት አይነቶቹ ተጠቃሽ ናቸው።
ለአገሪቱ የያዙት የወደፊት ራዕይ "ዕቅድ አልባ" እና "መፈክር ብቻ" ነው ሲሉም የካናዳ ወግ አጥባቂ ፓርቲ መሪ ፒየር ፖይሌቭርን ተችተዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትር አኒታ አናንድ

የፎቶው ባለመብት, Bloomberg via Getty Images
አናንድ ብዙ ጊዜ ከሊበራል ኮከስ አባላት መካከል ተስፈኞች አንዱ እንደሆኑ ተደርጎ ይታሰባል።
የ57 ዓመቷ የህግ ባለሙያ እአአ በ2019 ከቶሮንቶ ወጣ ብሎ የሚገኘውን ኦክቪልን በመወከል ተመርጠው ወደ ፖለቲካ ገብተዋል።
በኦክስፎርድ የተማሩት አናንድ በፋይናንስ ገበያ ደንብ እና በአስተዳደር ልምድ አላቸው።
በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ክትባቶችን እና የመከላከያ መሳሪያዎችን የማሰባሰብ ኃላፊነት የሚጥልባቸውን የህዝብ አገልግሎቶች እና ግዥ ኃላፊነት አገኙ።
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት ካናደ ለኪዬቭ እርዳታ ለመስጠት የምታደርገውን ጥረት ለመምራት እና በጾታዊ ጥቃት ቅሌቶች የተዘፈቀውን የካናዳ ጦር ኃይል ቀውስ እንዲያስተካክሉ እአአ በ2021 የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ተሾሙ።
አናንድ ኃላፊነቱን ለቀው የግምጃ ቤት ቦርድን በበላይነት እንዲመሩ ሲደረግ ብዙዎች ሥልጣናቸው ዝቅ እንደተደረገ እንዲቆጥሩ አድርጓል። አንድ ቀን ፓርቲውን መምራት ላላቸው ግለሰብ ቅጣት ነው ሲሉ የትሩዶ ተቺዎች ተቃውሟቸውን እስከመግለጽ ደርሰው ነበር።
በታህሳስ ወር በተደረገው የካቢኔ ሽግሽግ ወቅት ደግሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር እና የአገር ውስጥ ንግድ ሚኒስትርነት ሆነው ተሾሙ።
ፍራንሷ-ፊሊፕ ሻምፓኝ- የፈጠራ፣ ሳይንስ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, Toronto Star via Getty Images
የቀድሞው ነጋዴ የዓለም አቀፍ ንግድ ባለሙያ ሲሆኑ ፓርቲውን ለመምራት ግምት ከተሰጣቸው የሊበራል ሚኒስትሮች መካከል ይገኙበታል።
ከአናንድ አንጻር በስልጣን ወደ ትልቅ ደረጃ ያደረጉት ጉዞ ዝግ ያለ የሚባል ነበር።
የ54 ዓመቱ ሻምፓኝ እአአ በ2015 የአገሪቱን ፓርላማ ቢቀላቀሉም ከዚያ ወዲህ በዓለም አቀፍ ንግድ፣ በውጭ ጉዳዮች እና በቅርቡ ደግሞ በኢኖቬሽን፣ ሳይንስና ኢንዱስትሪ ውስጥ አልፈዋል።
ለእሳቸው የሚያደሉ በርካታ ነገሮችም አሉ። ሻምፓኝ በካናዳ ምርጫዎች ውስጥ ድምጹ ብዙ ጊዜ አስፈላጊ ከሆነው ኩዌቤክ ግዛት የመጡ ናቸው።
የካናዳ ምርቶችን ለመሸጥ ሲሉ ዓለምን ለመዞር የነበራቸውን ጉጉት የተመለከቱ አንዳንድ ምሁራን "የካናዳ የማይታክተው ሰው" የሚል ስያሜ ሰጥተዋቸዋል።
በንግድ ዕውቀታቸው ምክንያትም የፖለቲካ ተንታኞች የመሃል ላይ የሚገኙ ሊበራሎችን ወደ አንድ ለመመለስ እንደ አማራጭ አድርገው ይመለከቷቸዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜላኒ ጆሊ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ልክ እንደ ትሩዶ ሁሉ ጆሊ የሞንትሪያል አካባቢን ይወክላሉ።
ለውጭ አገር መሪዎች የ45 ዓመቱ ጆሊ ከ2021 ጀምሮ በዓለም መድረክ ላይ ካናዳን በመወከላቸው ፊታቸው አዲስ አይደለም።
የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንደመሆናቸው መጠን የካናዳ ድጋፍን ለማሳየት ወደ ዩክሬን በተደጋጋሚ ተጉዘዋል። የእስራኤል እና የሐማስ ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅት በአካባቢው የሚገኙ የካናዳ ዜጎችን ለማስወጣት ድጋፍ ለማድረግ ወደ ዮርዳኖስ ተጉዘዋል።
ካናዳ ውስጥ በህንድ ቅጥረኞች የሲክ ተገንጣይ መሪ መገደላቸውን ተከትሎ የተፈጠረውን ዲፕሎማሲያዊ ቀውስ ጨምሮ በአንዳንድ የመንግስት ታላላቅ የውጭ ፖሊሲ ፈተናዎች ወቅት ነው ጆሊ በውጭ ጉዳይ ሚንስትርነት እያገለገሉ የሚገኙት።
በኦክስፎርድ ህግ የተማሩት ፖለቲከኛዋ ከዚህ ቀደምም የሞንትሪያል ከተማ ከንቲባ ለመሆን ተወዳድረው ነበር።
ለፌዴራል መንግስት ኃላፊነት እንዲወዳደሩ በትሩዶ ድጋፍ አስከማግኘት ደርሰዋል።
"'ሜላኒ መወዳደር አለብሽ። እንድትወዳደሪ እንፈልጋለን' እያለ በየጊዜው ይደውልልኛል" ሲሉ ጆሊ ተናግረዋል።
ከፍተኛ አማካሪዎች ከሰባትም ሆነ ከ700 ባልደረቦች ጋር የመሥራት ችሎታቸውን አድንቀዋል። ለሊበራል ፓርቲ መሪነት ለመወዳደር ለረዥም ጊዜ ምኞት ነበራቸው ሲሉ የቅርብ ጓደኞቻቸው ለካናዳው ማክሊንስ መጽሔት ተናግረዋል።
ዶሚኒክ ለብላንክ - የገንዘብና የመንግሥታት ጉዳዮች ሚኒስትር

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የ57 ዓመቱ ለብላንክ ከትሩዶ የቅርብ እና ታማኝ አጋሮች አንዱ ናቸው።
ጓደኝነታቸው ጥልቅ ሲሆን ለብላንክ በወጣትነታቸው ዘመን ትሩዶን ጨምሮ ወንድም እና እህቶቻቸውን በህጻንነታቸው ተንከባክበዋል።
የፍሪላንድ የመልቀቅ ጥያቄ በቀረበ በሰዓታት ውስጥ የገንዘብ ሚኒስትር መሆንን ጨምሮ በአስቸጋሪ ጊዜያት ወደ የመድረስ ታሪክ አላቸው።
ትራምፕን ለማግኘት በህዳር ወር ከትሩዶ ጋር ወደ ማር አላጎ የተደረገውን አስቸጋሪ ጉዞም ተቀላቅለዋል።
የቀድሞው ጠበቃ በኒው ብሩንስዊክ አትላንቲክ ግዛትን በመወከል በ2000 ለመጀመሪያ ጊዜ ከተመረጡ በኋላ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የፓርላማ አባል ሆኖ አገልግለዋል።
ልክ እንደ ትሩዶ ሁሉ ለብላንክ የተወለዱት ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ካለው ቤተሰብ ነው። አባታቸው በትሩዶ አባት በሆኑት በጠቅላይ ሚኒስትር ፒየር ትሩዶ ካቢኔ ውስጥ እና በኋላም ደግሞ የካናዳ ጠቅላይ ገዥ በመሆን በሚኒስትርነት አገልግለዋል።
ለብላንክ ከዚህ ቀደም ፓርቲውን የመምራት ፍላጎት በማሳየት እአአ በ2008 ቢወዳደሩም ግን በሚካኤል ኢግናቲፍ ተሸንፈዋል። ትሩዶ አሸናፊ በሆኑበት በቀጣዩ ፉክክር በድጋሚ አልተወዳደርም።
ክሪስቲ ክላርክ፣ የቀድሞ የክልል ገዢ

የፎቶው ባለመብት, Christy Clark
የብሪቲሽ ኮሎምቢያ የቀድሞ ገዢ ወደ ሊበራል አመራርነት ብቅ ለማለት ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል።
በጥቅምት ወር በሰጡት መግለጫ ትሩዶ ከስልጣን ከለቀቁ "በሊበራል ፓርቲ እና በአገሪቱ የወደፊት አቅጣጫ አካል መሆን እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
የ59 ዓመቷ ክላርክ ከ2011 እስከ 2017 የካናዳ ምዕራባዊ ግዛት መሪ ሆነው አገልግለዋል።
ትሩዶ በፌዴራል ሊበራሎች ጉዳይ መያዛቸው ባለፉት ሁለት ዓመታት በቃለ መጠይቆቻቸው ላይ ደጋግመው ተናግረዋል።
ሬድዮ-ካናዳ እንደዘገበው ከሆነ ደግሞ የፈረንሳይኛ ትምህርት ሲወስዱ ቆይተዋል። ፈረንሳይኛ ቋንቋ ማወቅ ለካናዳ የፌዴራል ፖለቲከኞች እንደ ቅድመ ሁኔታ ይቆጠራል።












