ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ ከአየር ንብረት ለውጥ ደንብ ጀርባ ያለውን የአሜሪካ ሳይንሳዊ እርምጃ ሰረዙ
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ አሜሪካ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦባማ የሥልጣን ዘመን የዓለምን የሙቀት መጠን ለመቀነስ የወሰደቻቸውን ሳይንሳዊ እርምጃዎች በሙሉ ቀለበሱ።
ይህ በቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦባማ የሥልጣን ዘመን የወጣው እና "ኢንዳንጀርመንት ፋይንዲንግ" እየተባለ የሚታወቀው ሳይንሳዊ ግኝት በርካታ የግሪን ሃውስ ጋዝ ልቀቶች የሕዝብ ጤናን አደጋ ላይ መጣላቸውን ይዘረዝራል።
ሳይንሳዊ ግኝቱ የፌደራል መንግሥቱ ሕግ ማዕቀፎች መነሻ በመሆን ያገለገለ ሲሆን በተለይ ከተሽከርካሪዎች የሚወጣውን የበካይ ጋዝ ልቀት መጠን ለመቀነስ እርምጃ እንዲወሰድ አድርጓል።
ዋይት ሐውስ የዚህን ሳይንሳዊ ግኝት መሰረዝ "በአሜሪካ ታሪክ ትልቁ የሕግ ቅልበሳ" ነው ብሏል።
የአካባቢ ጥበቃ ቡድኖች ውሳኔው በአየር ንብረት ለውጥ ላይ እስካሁን ከተሞከረው ወደኋላ የማፈግፈግ ተግባር ትልቁ መሆኑን ጠቅሰው በፍርድ ቤት ጉዳዩን ለመሞገት ዝተዋል።
ሐሙስ ዕለት በኦቫል ኦፊስ መግለጫ የሰጡት ፕሬዚዳንት ትራምፕ እአአ በ2009 የወጣው መመሪያ "በኦባማ የሥልጣን ዘመን ከወጡ አውዳሚ ፖሊሲዎች መካከል አንዱ እና የአሜሪካን አውቶ ኢንዱስትሪ ክፉኛ የጎዳ ነው፤ በዚህም በአሜሪካውያን ሸማቾች ላይ ከፍተኛ ዋጋ ጭማሪ አስከትሏል" ሲሉ ተናግረዋል።
ሪፐብሊካኑ ፕሬዝዳንት ስለ ዴሞክራቶች የአየር ንብረት አጀንዳ ሲናገሩም "ይህ ጥብቅ ሕግ በአየር ንብረት ለውጥ ስም ለሚደረግ አዲስ ማጭበርበር ሕጋዊ መሠረት ሆኗል። በታሪክ ትልቀ የሆነው ማጭበርበር" ብለዋል።
በሥልጣን ላይ ስላሉ ፕሬዚደንቶች ፖሊሲዎች አልፎ አልፎ አስተያየታቸውን የሚሰጡት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ግኝቶቹን ውድቅ ማድረግ አሜሪካውያንን የበለጠ ተጋላጭ ያደርጋቸዋል ሲሉ ተችተዋል።
በኤክስ ገጻቸው "ያለዚያ ደህንነታችን በሚገባ አይጠበቅም፤፣ ጤናችን ለአደጋ ይጋለጣል እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመዋጋት አንችልም፤ ይህም በመሆኑ የነዳጅ ዘይት ኢንዱስትሪው የበለጠ ገንዘብ ማግኘት እና ማትረፍ ይችላል" ሲሉ ጽፈዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ኤጀንሲ በግሪን ሃውስ ተጽዕኖዎች ላይ ለመጀመርያ ጊዜ እርምጃ የወሰደው እአአ በ2009 በኦባማ የመጀመርያው የሥልጣን ዘመን ላይ ነበር።
ኤጀንሲው ለፕላኔታችን ስድስት ቁልፍ ነገሮች ግሪን ሃውስን በማሞቅ አስተዋጽኦ አንዳላቸው ዘርዝሯል።
ከእነዚህም መካከል ካርቦን ዳይኦክሳይድ እና ሚቴን ጨምሮ ሌሎች በካይ የጋዝ ልቀቶች ለሰው ልጅ ጤና አደገኛ መሆናቸውን በመጥቀስ ውሳኔ አሳልፏል።
በወቅቱ የኮንግረስ አባላት የዓለም ሙቀት መጨመር ላይ ላይ ወጥ አቋም ለመያዝ ተቸግረው የነበረ ሲሆን የኤጀንሲው ውሳኔም ግኝቱ የፌደራል መንግሥቱ የበካይ ጋዝ ልቀቶችን ለመቆጣጠር የሚያደርጋቸው ጥረቶች ማዕከል በመሆን ለዓመታት አገልግለዋል።