በከባድ ቅዝቃዜ ምክንያት አዳራሽ ውስጥ የሚካሄደው የትራምፕ በዓለ ሲመት

የአሜሪካ ባንዲራ ፊት ለፊት የካፒቶል ሕንፃ

ተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ድጋሚ ዋይት ሐውስ የሚገቡበት ቀን ተቃርቧል። ትራምፕ ሰኞ ጥር 12/2017 ለሁለተኛ ጊዜ በሚረከቡት ሥልጣን 47ኛው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ሆነው ይሾማሉ።

በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ቃለ-መሐላ ይፈፅማሉ። የሙዚቃ ድግስም ይኖራል። ሌሎች ትርዒቶች እና የእራት ግብዣ ሥነ-ሥርዓትም ይጠበቃል።

ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስም ሰኞ ከትራምፕ ጎን ሆነው ቃለ-መሐላ ይፈፅማሉ።

የአሜሪካ በዓለ ሲመት ምን ይመስላል?

ቅዝቀዜ የሚያስተጓጉለው በዓለ ሲመት

የዶናልድ ትራምፕ ሁለተኛው የሥልጣን ዘመን የበዓለ ሲመተ ሥነ ሥርዓት በአደገኛ የአየር ሁኔታ ምክንያት በተቀዛቀዘ ሁኔታ እንደሚካሄድ ተነገረ።

በዚህም ምክንያት በሚቀጥለው ሳምንት በዋሺንግተን ይኖራል ተብሎ በተተነበየው "አደገኛ ቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ" ሰኞ በሚካሄደው በዓለ ሲመት ላይ ተመራጩ ፕሬዝዳንት የሚያደርጉት ሥልጣን የሚረከቡበት ወሳኝ ንግግር ከቀደሙት ፕሬዝዳንቶች በተለየ በቤት ውስጥ የሚካሄድ ይሆናል።

ቀደም ሲል የፕሬዝዳንቱ ንግግር እና ሌሎች የበዓለ ሲመቱ ሥነ ሥርዓቶች በሺዎች የሚቆጠሩ ታዳሚዎች በሚገኙበት ሰፊ መስክ ላይ ይካሄዳል ተብሎ ፕሮግራም ተይዞ የነበረ ቢሆንም፣ በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ምክንያት ካፒቶል ሂል ውስጥ ይካሄዳል።

በአውሮፓውያኑ 1985 በቀዝቃዛ የአየር ሁኔታ ምክንያት በቤት ውስጥ ከተካሄደው ከሮናልድ ሬጋን በዓለ ሲመት በስተቀር የሁሉም የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች የሥልጣን ርክክብ ሥነ ሥርዓት ከአዳራሽ ውጪ በሰፊ መስክ ላይ ነው የተካሄዱት።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዚህም ምክንያት ዶናልድ ትራምፕ 47ኛው ፕሬዝዳንት ሆነው ሥልጣን ሲይዙ ንግግራቸውን በአዳራሽ ውስጥ በማድረግ ከሬጋን ቀጥለው ሁለተኛው ይሆናሉ።

ዶናልድ ትራምፕ የራሳቸው የሶሻል ሚዲያ መድረክ በሆነው 'ትሩዝ ሶሻል' ላይ ባሰፈሩት መልዕክት እጅግ በሚቀዘቅዘው የአየር ሁኔታ "ማንም ሰው በምን ሁኔታ ጉዳት እንዲደርስበት አልፈልግም" በማለት የመረሃ ግብሩ ለውጥ ለሕዝቡ ደኅንነት ሲባል የተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የትረምፕ በዓለ ሲመት በሚካሄድበት ዕለት ሰኞ ጥር 12/2017 ዓ.ም. በዋሺንግተን እና በአካባቢዋ ከባድ የሚባል ቅዝቃዜ እንደሚኖር ተተንብይዋል። በዕለቱ ቅዝቃዜው እጅግ ከወረደ ከዜሮ በታች 11 ሴሊሺየስ እና ከፍ ካለ ደግሞ ከዜሮ በታች 5 ሴሊሺየስ ይሆናል ተብሏል።

ከአራት ዓመት በፊት በተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በዓለ ሲመት ወቅት በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ተጥሎ በነበረው የሰዎች የመሰብሰብ ዕገዳ ምክንያት 1,000 የሚደርሱ ሰዎች ብቻ ነበር የታደሙት።

የአሜሪካ ተመራጭ ፕሬዝዳንቶች በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ሥልጣን ለመረከብ ቃለ መሐላ ከፈጸሙ በኋላ አስተዳደራቸው የሚያከናውናቸውን ተግባራት እና የአሜሪካ መንግሥት ትኩረት የሚያደርግባቸውን ጉዳዮች የሚያስተዋውቁበት ነው።

እስካሁን ከአሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ሁሉ በታሪክ ረጅሙን የየበዓለ ሲመት ንግግር ያደረጉት በወቅቱ የ68 ዓመት አዛውንት የነበሩት ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሄንሪ ሃሪሰን ሲሆኑ፣ ወቅቱም በአውሮፓውያኑ 1841 ነው።

ሥነ ሥርዓቱ የተከናወነበት ጊዜ እንዳሁኑ ቀዝቀዛ ስለነበረ ፕሬዝዳንቱ በበዓለ ሲመታቸው ዕለት ጉንፋን ይዟቸው ወደ ኒሞኒያ ተቀይሮባቸው ከአንድ ወር በኋላ ለህልፈት ተዳርገዋል። በዚህም ምክንያት ፕሬዝዳንት ዊሊያም በአሜሪካ የፕሬዝዳንትነት መንበር ላይ ለአጭር ጊዜ የቆዩ ሆነው ተመዝግበዋል።

በዓለ ሲመት ምንድነው?

በዓለ ሲመት ማለት አንድ መሪ በይፋ ሥልጣን የሚረከብበት እና የቀደመው መሪ ደግሞ የሚሰናበትበት ቀን ነው።

ይህ ቀን በዋሺንግተን ዲሲ ትልቅ ሥፍራ ከሚሰጣቸው ቀናት መካከል ነው። የሥልጣን ሽግግር ምልክትም ነው።

በዚህ ቀን ተመራጩ ፕሬዝዳንት በሕዝብ ፊት ቆመው ቃለ-መሐላ ይፈፅማሉ። የቃለ-መሐላው ግርድፍ ትርጉም ይህን ይመስላል፡

"የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ቢሮን ሥራ በአግባቡ ልፈፅም፤ በቻልኩት አቅም የዩናይትድ ስቴትስን ሕገ-መንግሥት ለመጠበቅ፣ ለመከላከል እና ለመመከት ቃል እገባለሁ።"

ምንም እንኳ ትራምፕ ምርጫውን ያሸነፉት ባለፈው ኅዳር ቢሆንም በኦፊሴላዊ መንገድ ፕሬዝዳንት የሚሆኑት ይህን ቃለ-መሐላ ሲፈፅሙ ነው።

በሙዚቃ ድግስ እና በንግግር የሚታጀብ ሥነ-ሥርዓት ይሆናል። ትራምፕ ለመረጧቸው ሰዎች መልዕክት ያስተላልፋሉ። በሚቀጥሉ አራት ዓመታት ምን ሊሠሩ እንዳሰቡም ዕቅዳቸውን እና የትኩረት አቅጣጫቸውን ያሳውቃሉ።

ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዓሉ ሲመቱ የትና መቼ ይከናወናል?

ሁለተኛው የትራምፕ በዓለ ሲመት የሚጀምረው ዋሺንግተን ዲሲ በሚገኘው በታሪካዊው ቅዱስ ዮሐንስ ቤተ-ክርስቲያን ነው። ቀጥሎ ለሻይ ፕሮግራም ወደ ዋይት ሐውስ ያመራሉ።

ዋናው ሥነ-ሥርዓት ከካፒቶል ሂል ፊል ለፊት በተንጣለለው ዌስት ሎውን መስክ ላይ ይካሄዳል ተብሎ የነበረ ቢሆንም በከባድ ቅዝቃዜ ምክንያት ተስተጓጉሏል። የሙዚቃ ድግስ እና የመክፈቻ ንግግሩም ከመስክ ወደ አዳራሽ ውስጥ ተዘዋውሯል። ሥነ-ሥርዓቱ በከተማዋ ሰዓት አቆጣጠር ጥዋት 3፡30 እንደሚጀምር ይጠበቃል።

ቀጥሎም ትራምፕ እና ቫንስ ቃለ-መሐላ ይፈፅማሉ፤ ንግግር ያደርጋሉ።

ከዚህ በኋላ ትራምፕ ፕሬዝዳንትስ ሩም ወደ ተሰኘው የመሪዎች ክፍል ይገባሉ። ከዚህ ክፍል ሆነው በአዲሱ አስተዳደር ስም ወረቀቶች ላይ ፊርማቸውን ያኖራሉ።

አዲሱ ፕሬዝዳንት የኮንግረሱ ጥምር ኮሚቴ በሚያዘጋጀው የምሳ ግብዣ ላይ ይታደማሉ።

ከዚህ በኋላ ነው ከካፒቶል ተነስቶ በፔንሲልቬኒያ ጎዳና ወደ ዋይት ሐውስ የሚደረገው ሰልፍ የሚጀምረው።

አመሻሹን ትራምፕ ወደ ሦስት ቦታዎች ለግብዣ ይሄዳሉ። አንደኛው ኮማንደር ኢን ቺፍ ወይም የአገሪቱ ጦሩ አዛዥ ሲሆን፣ ሁለተኛ ሊበርቲ ኢናጉራል፣ ሦስተኛው ደግሞ ስታርላይት ይባላል።

ዶናልድ ትራምፕ በሦስቱም አዳራሾች ንግግር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

በዓለ ሲመቱን እንዴት መታደም ይቻላል?

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት በዓለ ሲመትን በአካል ተገኝተው መታደም የሚፈልጉ ብዙዎች ናቸው። ወደ ሥነ ሥርዓቱ ስፍራ የመግቢያ የግብዣ ቲኬት በነፃ የሚታደል ቢሆንም ማግኘት ግን ቀላል አይደለም።

የአገሜሪካ ምክር ቤት (ኮንግረስ) አባላት ለመረጣቸው ሕዝብ የሚሰጡት የተወሰነ ያህል የግብዣ ቲኬት ያገኛሉ።

ዋይት ሐውስ በዓለ ሲመቱን ቀጥታ ያስተላልፋል። ቢቢሲም በዜና ጣቢያዎቹ የቀጥታ ቴሌቪዥን ሥርጭት አለው። በድረ-ገፅም በቀጥታ መከታተል ይቻላል።

ማን ይታደማል?

የአካባቢው እና የፌዴራል ባለሥልጣናት 200 ሺህ ሰዎች ዋሺንግተን ዲሲ ተገኝተው ሥነ ሥርዓቱን ያደምቁታል ብለው የጠበቁ ቢሆንም ቀዝቃዛው የአየር ሁኔታ ነገሮችን ይቀይራቸዋል ተብሏል። የትራምፕ ደጋፊዎች ብቻ ሳይሆን ተቃዋሚዎችም ድምፃቸውን ሊያሰሙ ይችላሉ።

በርካታ የአሜሪካ ሴናተሮች እና የኮንግረስ አባላት ይገኛሉ።

ከትራምፕ እና ቫንስ እንዲሁም ቤተሰቦቻቸው ቀጥሎ ትልቅ እንግዳ የሚባሉት ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት እና ምክትላቸው ናቸው።

ባለፈው የኅዳር ምርጫ የተሸነፉት ምክትል ፕሬዝዳንቷ ካማላ ሀሪስ እና ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በሥነ ሥርዓቱ ላይ ይታደማሉ ማለት ነው። ቀዳማዊት እመቤት ጂል ባይደን እና የካማላ ባለቤት ዳግ ኤምሆፍም ይገኛሉ።

ብዙውን ጊዜ የቀድሞ ፕሬዝዳንቶች እና ቀደማዊ እመቤቶች በበዓለ ሲመት ይታደማሉ።

በዚህኛው ዓመት ጆርጅ እና ሎውራ ቡሽ እና ባራካ ኦባማ እንደሚገኙ ይጠበቃል። ሚሼል ኦባማ አይደታደሙም የሚሉ ጭምጭምታዎች አሉ።

የሀገረሰብ ሙዚቃ አቀንቃኝ ኬሪ አንደርውድ የሙዚቃ ሥራዋን ታቀርባለች። የዲስኮ ዘውግ ቡድን የሆኑት 'ዘ ቪሌጅ ፒፕል' በአንዱ ፕሮራግራም ላይ የሙዚቃ ሥራቸውን አንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።

ዘ ቪሌጅ ፒፕል የተጫወቱት 'ዋይኤምሲኤ' እና 'ማቾ ማን' የተባሉ ሙዚቃዎችን በትራምፕ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት መስማት የተለመደ ነበር።

ሌሎችም ሙዚቀኞች የትራምፕን በዓለ ሲመት እንደሚያደምቁት ተነግሯል።