ትራምፕ ኮስተር ብለው የተነሱት ፎቶ የቀጣዩ የሥልጣን ዘመናቸው ይፋዊ ፎቶ እንዲሆን ተለቀቀ

የፎቶው ባለመብት, TRUMP VANCE TRANSITION TEAM HANDOUT/EPA
በተለያዩ ስፍራዎች ላይ የሚቀመጡት የተመራጩ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ እና የምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ኦፊሴላዊ ፎቶ ይፋ ሆነ።
ትራምፕ እና ቫንስ በሚመጣው ሰኞ በሚካሄድ በዓለ ሲመት የአሜሪካንን የመሪነት ሥልጣን ይረከባሉ።
ተመራጩ ፕሬዝደንት እና ምክትላቸው ሰማያዊ ሱፍ በነጭ ሸሚዝ እና በሰማያዊ ክራቫት ለብሰው የተነሱት ፎቶግራፍ ነው ይፋዊ የሥልጣን ዘመናቸው መለያ የሆነው።
በፎቶግራፉ ላይ ትራምፕ ከምክትላቸው በተለየ ኮስተር ብለው ይታያሉ። ቫንስ ደግሞ እጃቸውን አጣምረው፤ ፈገግታ ተላብሰው ተነስተዋል።
የዶናልድ ትራምፕ ኦፊሴላዊ የሥልጣን ዘመን ፎቶ በአውሮፓውያኑ 2023 ክስ ሲመሠረትባቸው በፖሊስ ጣቢያ ከተነሱት ፎቶ ጋር ይመሳሰላል።
በወቅቱ የ2020 ምርጫ ፍትሐዊ አይደለም በሚል ለመቀልበስ ሞክረዋል የሚል ክስ ነበር የቀረበባቸው። ትራምፕ ክሱን ያስተባብላሉ።
ትራምፕ ፖሊስ ጣቢያ የተነሱትን ፎቶ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ተጠቅመውበት ያውቃሉ።
የትራምፕ እና ቫንስ የሽግግር አስተዳደር ቡድን ባወጣው መግለጫ ፎቶዎቹ "ድንቅ ናቸው" ብሏል።
47ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው በሚመጣው ሰኞ ቃለ-መሐላ የሚፈፅሙት፣ ትራምፕ በ2017 የተነሱት ኦፊሴላዊ ፎቶ ከአሁኑ የተለየ ነው።

የፎቶው ባለመብት, TRUMP VANCE TRANSITION TEAM HANDOUT/EPA
"ምናልባት ትራምፕ አሁን ያሉበትን ሁኔታ የሚያንፀባርቅ ፎቶ ፈልገው ይሆናል። ከክስ አምልጠው ምርጫ ማሸነፋቸውን የሚያሳይ የጥንካሬ ምልክት የሆነ ፎቶ እንዲሆን ሳይፈልጉ አይቀርም" ይላሉ በጆርጅ ዋሺንግተን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ ፕሮፌሰሩ ኩዋድሪኮስ ድሪስኬል።
"ካለፈው ጊዜ በተለየ ኮስተር ብለው መነሳታቸው በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸው ፈርጠም ብለው እንደሚመጡ ጠቋሚ ሊሆን ይችላል" የሚል ትንታኔ ይሰጣሉ።

የፎቶው ባለመብት, Fulton County Sheriff's Office
የትራምፕ እና ቫንስ በዓለ ሲመት ሲከናወን በርካታ ሰዎች በካፒቶል ሕንፃ አቅራቢያ ተገኝተው እንደሚታደሙት ይጠበቃል።
ከትራምፕ እና ቫንስ እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸው ቀጥሎ ትልቅ እንግዳ የሚባሉት ተሰናባቹ ፕሬዝደንት እና ምክትላቸው ናቸው።
ባለፈው የኅዳር ምርጫ የተሸነፉት ምክትል ፕሬዝደንቷ ካማላ ሀሪስ እና ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ይኖራሉ ማለት ነው። ቀዳማዊ እመቤት ጂል ባይደን እና የካማላ ባለቤት ዳግ ኤምሆፍ ይታደማሉ።
በተጨማሪም ጆርጅ እና ላውራ ቡሽ እና ባራካ ኦባማ እንደሚገኙ ይጠበቃል። ሚሼል ኦባማ አይደታደሙም የሚሉ ጭምጭምታዎች አሉ።
ምንም እንኳ ትራምፕ ባለፈው ኅዳር ቢሆንም ምርጫውን ያሸነፉት በኦፊሴላዊ መንገድ ፕሬዝደንት የሚሆኑት ይህን ቃለ-መሐላ ሲፈፅሙ ነው።
ሲመተ በዓሉ በሙዚቃ ድግስ እና በንግግር የሚታጀብ ሥነ-ሥርዓት ይሆናል። ትራምፕ ለመረጧቸው ሰዎች መልዕክት ያስተላልፋሉ። በሚቀጥሉ አራት ዓመታት ምን ሊሠሩ እንዳሰቡም አቅጣጫ ያስቀምጣሉ።












