ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሁለት አንጋፋ ፖለቲከኞች ዕይታ በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጥረት ዙሪያ
በኢትዮጵያ ለዓመታት የተከማቸውን የፖለቲካ ችግር በውይይት እና በብሔራዊ መግባባት እንዲፈታ ብዙዎች ሲወተውቱ ቆይተዋል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በልሂቃን መካከል በአገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት አለመኖሩ በመካከላቸው ያለው አለመተማመን እና ጥርጣሬ የዴሞክራሲ የሽግግር ሂደቱን ፈታኝ አድርጎታል ሲባል ቆይቷል።
በአገሪቱ የተለያየ አካባቢዎች የሚስተዋሉት ግጭቶችም ለዓመታት እልባት ባላገኙ ታሪካዊ ክስተቶች እና የፖለቲካ አመለካከት ልዩነቶች የመጡ ናቸው።
እንደ አገር የሚታዩ ልዩነቶችን ለመፍታት እና ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ሀገራዊ ምክክር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን የፖለቲካ ልሂቃን ይገልጻሉ።
በኢትዮጵያ ያለው የፖለቲካ ልዩነት በምርጫ ብቻ የማይፈታ በመሆኑ የተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠር ይችላል የተባለውን የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ተቋቁሞ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው።
በአዋጅ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከፖለቲካ ወገንተኝነት፣ ከማንኛውም የመንግሥት ወይም ሌላ አካል ተጽዕኖ ነጻ የሆነ እና ራሱን የቻለ የሕግ ሰውነት ያለው አካል ሆኖ ተጠሪነቱ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሆነ በአዋጅ በግልጽ ሰፍሯል።
በአገሪቱም መተማመን የሰፈነበት የፖለቲካ ሥርዓት ለመመስረት ይሰራል ተብሎም ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን 11 ኮሚሽነሮች በየካቲት 2014 ዓ.ም ከተሾሙለት በኋላ ወደ ሥራ መግባቱን ይናገራል።
ይህ ኮሚሽን ከሁሉ በላይ የብሔራዊ መግባባት እንዳይኖሩ አድርጓል የተባሉ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ የማፈላለግ ተልዕኮን ይዞ ሥራ እንደጀመረ ይነገራል።
ኮሚሽኑ መሠረታዊ በሆኑ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ለተፈጠሩ ልዩነቶች ምክንያቶችን በመለየት ገለልተኛ ናቸው ተብለው በተሾሙት 11 ሰዎች እየተመራ ጉዳዮቹ ላይ ውይይት እንዲካሄድባቸው ያደርጋል።
ነገር ግን አሁንም በዋነኛ ጉዳዮች ላይ ውይይት ከመጀመሩ በፊት በፖለቲከኞች መካከል ስለ ኮሚሽኑ አንድ ወጥ የሆነ የሚያስማማ አስተያየት ሲሰጥ አይሰማም።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ 50 ዓመታትን ያሳለፉት ጎምቱው የፖለቲካ ሰው አቶ ሌንጮ ለታ፣ “ኢትዮጵያ አሁን የተጋፈጠቻቸው ችግሮች ካለፉት ሥርዓቶች ተገፍተው የመጡ ናቸው” ይላሉ።
“ከ50 ዓመት በፊት እኛ ትግል ስንጀምር ኢትዮጵያ የአንድ ብሔር፣ የአንድ ባሕል እና የአንድ ቋንቋ ናት ተብሎ ይሰበክ ነበር። እኛም በዚያ ሰዓት አይሆንም ኢትዮጵያ ኢምፓየር ናት። ከዚህ ውስጥ ወጥተን መብታችንን ማስከበር አለብን ብለን ወደ ትግል ገባን” በማለት አንዴት ወደ ትግል እንደገቡ ያስታውሳሉ።
ከ1983 ዓ.ም. በኋላ ግን አገሪቱ ብዙ ብሔሮች የሚኖሩባት አገር ስለሆነች፣ ሕዝቦች በአብሮነት መኖር የሚያስችል “ብዙ ብሔረሰቦችን መብት የሚያጎናጽፍ ፌዴሬሽን ተመሠረተ፤ ይህም አንድ እርምጃ ነበር” ይላሉ አቶ ሌንጮ።
አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ሌንጮ ብዝኀነት ያለው ፌዴሬሽን መመሥረቱ አንድ እርምጃ ቢሆንም እንኳ፣ ፌዴሬሽኑ እንደተፈለገው ዲሞክራሲያዊ አለመሆኑ አሁን አገሪቱ ለገጠማት ችግር መነሻ ነው ብለው ያምናሉ።
አቶ ሌንጮ አሁን ለብሔራዊ ምክክር የተቋቋመው ኮሚሽን ውስጥ በአማካሪ ኮሚቴነት ከሚሰሩት ውስጥ መካከል አንዱ ናቸው።
“በአሁኑ ሰዓት ኢትዮጵያ አንድ ምርጫ ብቻ ነው ያላት። እርሱም ብዝኀነት ያለውን ፌዴሬሽን ዲሞክራሲያዊ ማድረግ ነው። ይህ ካልሆነ ግን የአገሪቱ ሥርዓት ይወድቃል የሚል ስጋት አለኝ።
“ሥርዓት ሲፈርስ ደግሞ ጎረቤታችን ሶማሊያን አይተናል። አንድ ቋንቋ፣ አንድ ባሕል፣ እምነት ያለው ሕዝብ ካለፉት 30 ዓመት በኋላ መልሶ አገሪቱን ለመገንባት አልቻለም” በማለት ያላቸውን ስጋት ያብራራሉ።
አክለውም “ኢትዮጵያ የመፍረስ አደጋ ገጠማት ማለት ደግሞ ይህችን አገር መልሶ ለመገንባት እንደ ቀላል የሚታይ ጉዳይ ነው ብዬ አላስብም” ይላሉ።
አቶ ሌንጮ በሀገሪቱ ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ ለመፈለግ ብሔራዊ ምክክሩ ወሳኝ አማራጭ እንደሆነ እና ይህንኑም እንደሚደግፉ ይናገራሉ።
ይህ ምክክር እንዲሳካ ደግሞ የኦሮሞ ሕዝብ ከሁሉ በላይ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት ሲሉ ጥሪያቸውን ያቀርባሉ።
“ይህ የብሔራዊ ምክክር ስኬታማ ሆኖ በአገሪቱ እውነተኛ ዲሞክራሲ እንዲስፋፋ ኦሮሞ ኃላፊነት አለበት። የኃላፊነት ስሜትም ሊሰማው ይገባል። እንደከዚህ ቀደሙ ከሌሎች አካላት መጠበቅ የለበትም” ይላሉ።
“አሁን ሊከናወን እየተኬደበት ላለው የብሔራዊ ምክክር ኦሮሞ መሳተፍ አለበት። ማኅበሰረሰቡ እርስ በእርሱ ካልተረዳዳ በስተቀር ይህ ምክክር ላይሳካ ይችላል። ካልተሳካ ደግሞ የሚጎዳው ሁሉም ነው። ኦሮሚያም ሆነ ይህች አገር አይኖሩም። ትልልቅ ችግሮች ሊፈጠሩ እችላሉ” በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
የኦሮሞ ኮንግረስ ፌደራሊስት (ኦፌኮ) ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ደግሞ የብሔራዊ ምክክሩ ፓርቲያቸው ለብዙ ዓመታት ሲጠይቅ የነበረው ጉዳይ መሆኑን ያስታውሳሉ።
ቢሆንም እንኳ ኮሚሽኑ አሁን በተዋቀረበት አካሄድ አገሪቱ ያለችበትን ችግር ይፈታል የሚል እምነት እንደሌላቸው ይገልጻሉ።
“አሁን የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚባለው ምንም ነገር መሬት ሳያስይዝ የሞተ ነው። ይህ ኮሚሽንም ለአንድ ዓመት፣ ለሁለት ዓመት ቴአትር ተጫውቶ የሚያልፍ እንጂ ትልቅ ነገር የሚያመጣ አይደለም” የሚል እምነት አላቸው።
የተቋቋመው የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን ከመንግሥት ወገን ብቻ የተቋቋመ በመሆኑ ችግሮችን ይፈታል የሚል እምነት እንደሌላቸው ሲገልጹ መቆየታቸውን ያወሳሉ።
“በእንዲህ ዓይነት ጉዳይ ላይ ሁሉም አካል ነበር መሳተፍ የነበረበት። ይህም ሲባል የመንግሥት አካላት እና ተቃዋሚዎችም ጭምር ማለት ነው። ሽምግልና ከሁለቱም ወገን ነው አንጂ ከአንዱ ወገን ብቻ አይደለም የሚሆነው። መንግሥት ኮሚሸኑን ይህንን ጊዜ ለማለፍ ነው ያቋቋመው። አንድ ተጫዋች ነው የራሱን ፍላጎት ለማሳካት ያቋቋመው” ሲሉ ይከስሳሉ ፕሮፌሰር መረራ።
በማስከተልም ይህ ኮሚሽን ከተቋቋመ በኋላ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ፣ አንድም ተጨባጭ ሥራ ያላሳካ “መንግሥት ጊዜ ሊገዛበት ብቻ ያቋቋመው ነው” በማለት ይተቹታል።
አቶ ሌንጮ ለታ ግን አሁን የታሰብው የብሔራዊ ምክክር ለዚህች አገር መፍትሔ ሊያመጣ እንደሚችል ተስፋ አላቸው።
ተስፋቸው እውን እንዲሆን ግን የሕዝቦች ተሳትፎ እና አንድነት በጣም አስፈላጊ ነው ባይ ናቸው።