ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በአል-ሸባብ ታግተው የነበሩ 14 ኢራናውያን ከዓመታት በኋላ ተለቀቁ
በሶማሊያ በአል-ሸባብ ታጣቂዎች ታግተው የነበሩ 14 ኢራናውያን አሳ አስጋሪዎች ከዓመታት በኋላ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል።
ታጋቾቹ ለማስለቀቅ ከመንግሥት ባለስልጣናት፣ ከጎሳ መሪዎች እና ከሶማሊያ የአገር ሽማግሌዎች ጋር ረጅም ድርድር ከተደረገ በኋላ መለቀቃቸውን የኢራን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ባለፈው ቅዳሜ ወደ አገራቸው የተጓዙት ታጋቾቹ በኢራን ደቡባዊ ክፍል ወደ ሚገኘው እና ቻባሃር ወደ ተባው የትውልድ ስፍራቸውም አቅንተዋል።
ለሶማሊያ ቅርብ ከሆነው ዓለም አቀፍ የውሃ አካል ከታገቱት አሳ አስጋሪዎች መካከል እስከ 8 ዓመት በአል-ሸባብ ተይዘው የቆዩ እንዳሉም ተሰምቷል።
አሳ አስጋሪዎቹ ከመለቀቃቸው ከአንድ ወር ገደማ በፊት የሶማሊያ ፖሊስ በታጣቂዎች ተይዞ በነበረ ስፍራ ላይ 20 የውጪ አገራት ዜጎችን ማግኘቱን አስታውቆ ነበር።
ከእነዚህ ውስጥ 14 የኢራን ዜግነት ያላቸው ሲሆን የተቀሩት ደግሞ ፓኪስታናውያን ናቸው ተበሏል።
የፈረንሳይ የዜና ወኪል ፖሊስን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ ከታጋቾቹ አሳ አስጋሪዎች መካከል የተወሰኑት እንደ አውሮፓውያኑ በ2014 የታገቱ ሲሆኑ ሌሎች ደግሞ በ2019 አጋማሽ በታጣቂዎች የተያዙ ናቸው።
አስራ አራቱ አሳ አስጋሪዎች ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ቴህራን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ሲደርሱ ቤተሰቦቻቸው ባዘጋጁት ፕሮግራም አቀባበል አድርገውላቸዋል።
እስላማዊ ታጣቂው አል-ሸባብ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ በሞቃዲሾ 120 ሰዎች የሞቱበትን መኪና ላይ የተጠመደ ቦምብ በመጠቀም ጥቃትን ጨምሮ በቅርብ ወራት በርካታ ጥቃቶችን ፈጽሟል።
የሶማሊያ መንግሥት ከጎሳ ሚሊሻዎች ጋር በመሆን አልሸባብ ላይ መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ ከፍቷል።
የአል-ሸባብ ታጣዊዎች ከ15 ዓመት በላይ ለሆነ ጊዜ በሶማሊያ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ሲሆን ሰፊ ገጠራማ አከባቢዎችን መቆጣጠር ችለው ነበር። በከተሞች የሚያደርሱትን ጥቃትም ቀጥለዋል።