ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፖፕ ፍራንሲስ የሰው ልጅ ለ‘ስልጣንና ኃብት’ መስገብገቡን አወገዙ
የካቶሊኩ ሊቀ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ የሰው ልጅ ለ’ስልጣንና ኃብት’ የሚያደርገውን ስግብግብነት አወገዙ።
ፖፕ ፍራንሲስ በቫቲካን የእየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል ዋዜማ ቅዳሴ ላይ ነው ይህንን የተናገሩት።
ሊቀ ጳጳሱ ይህንን ሲናገሩ መነሻ ያደረጉት ለዓለም ህዝብ ሰቆቃን ያተረፉ ጦርነቶችንና ግጭቶችን ነው።
“ስንት ጦርነቶችን አይተናል?” ያሉት አቡነ ፍራንሲስ የነዚህ ግጭቶች ገፈት ቀማሾች ህዝቡ በተለይም ተጋላጭ የሆኑትና ደካሞች ናቸው ብለዋል።
“ከሁሉም በላይ በጦርነት፣ በድህነት እና በፍትህ እጦች እየተሰቃዩ ያሉ ልጆች ያሳዝኑኛል” ሲሉ ርዕሰ ሊቃነ ጻጳሱ አክለው ገልጸዋል።
ፖፕ ፍራንሲስ በቫቲካን ለተገኙ የቅዱስ ጴጥሮስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናንም ነው መልዕክታቸውን ያስተላለፉት።
የ86 አመቱ ፖፕ ፍራንሲስ ቅዳሜ አመሻሽ ላይ በነበረው ቅዳሴ ለመታደም ወደ ቤተ ክርስቲያን የገቡት በዊልቸር ሲሆን አገልግሎቱም እስኪጠናቀቅ ተቀምጠው ነበር።
“እንስሳት በጋጦቻቸው ውስጥ ሲመገቡ በዓለማችን ያሉ ወንዶችና ሴቶች ለሃብትና ስልጣን በመስገብገባቸው ጎረቤቶቻቸውን፣ እናቶቻቸውንና ልጆቻቸውን ሳይቀር ለሰቆቃ አጋልጠዋል” ብለዋል።
በዚህ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሩሲያና የዩክሬንን ወይም በተለያዩ አገራት እየተካሄዱ ያሉ ጦርነቶችን አልጠቀሱም።
ሩሲያ ዩክሬንን በወረረችበት በመጀመሪያዎቹ ወቅት ሩሲያን ቀጥታ አልወቀሱም በሚል ፖፕ ፍራንሲስ ወቀሳ ቀርቦባቸው ነበር።
“ጦርነቱን በትንኮሳ ተነስቷል ወይም መከላከል አልተቻለም” የሚል አስተያየታቸውን በመጀመሪያ ቢሰጡም በኋላ ግን የሩሲያ ወታደሮች ፈጸሙ ያሉትን ግፍ አውግዘዋል።
ፖፕ ፍራንሲስ ዛሬ የእየሱስ ክርስቶስ ልደትንም በዓል ምክንያት በማድረግ በየአመቱ እንደሚያደርጉት በቅዱስ ጴጥሮስ ባሲሊካ በረንዳ ላይ ሆነው ለዓለም ህዝብ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።
በዩናይትድ ኪንግደም የካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ ጀስቲን ዌልቢ በዓለም ዙሪያ ጦርነት እና ግጭቶች እንዲሁም የኑሮ ውድነት የሰውን ልጅ እየፈተነው ቢሆንም በእየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል “ተስፋ ያንሰራራል” ሲሉም ተደምጠዋል።