ስፔን ዋንጫ እንድታነሳ የማሸነፊያ ግብ ያስቆጠረችው ኦልጋ ከድል በኋላ የአባቷ ሞት ተነገራት

አውስትራሊያ እና ኒው ዚላንድ በጥምረት ባዘጋጁት የሴቶች የዓለም ዋንጫ ብቸኛዋን ግብ በማስቆጠረ የስፔን ብሔራዊ ቡድን የውድድሩ አሸናፊ እንዲሆን ያደረገችው የቡድኑ አምበል ኦልጋ ካርሞና ከድሉ በኋላ የአባቷን ሞት ተረድታለች።

የ23 ዓመቷ የሪያል ማድሪድ ክለብ የግራ መስመር ተከላካይ ኦልጋ ካርሞና፣ ስፔን እንግሊዝን ባሸነፈችበት ጨዋታ ብቸኛዋን ጎል አስቆጥራለች።

የኦልጋ አባት ለረጅም ጊዜ የቆየ የጤና ችግር እንደነበረባቸው እና ሕይወታቸው ያለፈው አርብ ዕለት እንደነበረ ሮይተርስ ዘግቧል።

ይሁን እንጂ ተጫዋቿ ውድድሩን እስክትጨርስ የአባቷ ሞት ለሁለት ቀናት ሳይነገራት ቆይቷል።

ተጫዋቿ የአባቷ ሞት ከተረዳች በኋላ በማኅበራዊ ሚዲያ ገጿ ያጠለቀችውን ሜዳሊያ እየሳመች “ዛሬ ምሽት እየተመለከትከኝ እንደነበር እና እንደኮራህብኝ አውቃለሁ። አባቴ ነፍስህ በሰላም ትረፍ” የሚል ጽሁፍን አስፍራለች።

ጨምራም “ሳይታወቀኝ ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት መልካም ስሜት ነበረኝ። አንድ የተለየ ነገር እንዳሳካ ጥንካሬ የሚሆን ነገር እንደሰጠኸኝ አውቃለሁ” ብላለች።

የስፔን እግር ኳስ ማኅበር በማኅብራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባሰራጨው ጽሑፍ “የኦልጋ ካርሞና አባት ማለፋቸውን ስንገልጽ በታላቅ ሐዘን ነው” ብሏል።

“ተጨዋቿ አሳዛኙን ዜና [ከሴቶች] የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ በኋላ ተረድታለች። የተሰማንን ሐዘን ለኦልጋ እና ለቤተሰቧቸ እንገልጻለን። እንውድሻለን። ኦልጋ ለስፔን ታሪካዊ ጎል አስቆጥረሻል” ሲል አክሏል።

ቤተሰቦቿ እና ጓደኞቿ የተጫዋቿን አባት ህልፈት ከፍጻሜው ጨዋታ በፊት ላለማርዳት መወሳናቸውን በስፔን የሚገኝ ሬልቮ የተሰኘው ሚዲያ ዘግቧል።

ምክንያታቸው ደግሞ ጨዋታው ላይ ትኩረት እንድታደርግ ነው። እናቷ እና ወንድሞቿ እሷን ለመደገፍ ባለፈው ቅዳሜ አውስትራሊያ ተገኝተው ነበር።

ክለቧ ሪያል ማድሪድም “የተሰማውን ሐዘን ለተጨዋቿ እና ለቤተሰቧቿ እንዲሁም ለሚወዷት ሁሉ ይገልጻል” ብሏል።