የጤና ባለሙያዎች የሚታከሙባቸው "የሠራተኛ ክሊኒኮች" እንዲቋቋሙ እና የጤና ተቋማት ለሠራተኞች ተሽከርካሪዎቻቸውን እንዲያቀርቡ ተወሰነ

ጤና ሚኒስቴር፤ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች በሥራቸው በሚገኙ ጤና ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ የሕክምና ባለሙያዎች እና ቤተሰቦቻቸው በነጻ ሕክምና የሚያገኙበትን "የሠራተኛ ክሊኒክ" እንዲያዘጋጁ መመሪያ አስተላለፈ።

ሚኒስቴሩ፤ የጤና ተቋማት "ያላቸውን ተሽከርካሪ በመጠቀም" በሕክምና ባለሙያዎች የሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቀርብ መወሰኑንም አስታውቋል።

'የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ' ውሳኔዎቹን "እንደ ጥሩ ጅምር" ቢወስደውም፤ የቀረቡት ማሻሻያዎች ተፈጻሚ ሊሆኑ የሚችሉበትን አግባብ በተመለከተ ጥያቄ አንስቷል።

የጤና ሚኒስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ ባለፈው ሳምንት ሰኞ፣ ነሐሴ 12/2017 ዓ.ም. ለክልል መንግሥታት እና የከተማ አስተዳደሮች በጻፉት ደብዳቤ ተግባራዊ እንዲሆኑ የተወሰኑ "የጥቅማ ጥቅም ፓኬጆችን" አስታውቀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዲኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ለጤና ባሙያዎች የተወሰነውን ጥቅማ ጥቅም ማሻሻያ የያዘ ሰርኩላር ለክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች መሠራጨቱን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የፌደራል መንግሥት ይህንን ማሻሻያ ይፋ ያደረገው የጤና ባለሙያዎች ከደመወዝ ማሻሻያ እና የአሠራር ለውጥ ጋር በተያያዘ ያቀረቧቸው 12 ጥያቄዎች ምላሽ አለማግኘታቸውን ተከትሎ ግንቦት ላይ አድማ ከመቱ ሦስት ወራት በኋላ ነው።

በወቅቱ የጤና ባለሙያዎቹ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ሌሎች ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ውይይት አድርገው ነበር።

ከዚህም በኋላ ቢሆን ጥያቄያቸው በተገቢ ሁኔታ አለመመለሱን የሚገልጹት ባለሙያዎቹ በመስከረም ወር ሌላ አድማ ለመምታት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

ዶ/ር መቅደስ በጻፉት ደብዳቤ፤ ለጤና ባለሙያዎች የሚተገበር የጥቅማ ጥቅም ፓኬጅ "ከክልል ክልል እንዲሁም በጤና ተቋሞቻችን መካከል ያለው አፈጻጸም ወጥነት የጎደለው" ነው ብለዋል።

ይህ መሆኑም የጤና ባለሙያዎች ላይ "ቅሬታ በመፍጠር ጥያቄ እንዲያነሱ" ማድረጉን ጠቅሰዋል።

ዶ/ር መቅደስ፤ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በተደረገው ውይይት፤ "በአጭር፣ መካከለኛ እና ረጅም ጊዜ ሊፈጸሙ የሚገባቸው ጉዳዮችን" ተለይተው እንዲተገበሩ መወሰኑን አስታውሰዋል።

ከደብዳቤው ጋር የተያያዘው የጤና ሚኒስቴር ሰርኩላር ከመስከረም 2018 ዓ.ም. ጀምሮ "ለጤና ዘርፍ ሠራተኞች" ተፈጻሚ እንዲሆኑ መመሪያ የተሰጠባቸውን ሰባት ጉዳዮች ዘርዝሯል።

በማሻሻያው ላይ የተጠቀሰው ቀዳሚው ጉዳይ በጤና ባለሙያዎች ሲጠየቅ የነበረው የነጻ ሕክምና አገልግሎት ነው። ባለፈው ወር ሐምሌ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስሩ ለሚገኙ ጤና ባለሙያዎች በሰጠው የተናጠል ምላሽ በዚህ ጥያቄ ላይ ማሻሻያ አድርጎ ነበር።

የአዲስ አበባ ከተማ የጤና ባለሙያዎች እና ቤተሰቦቻቸው በከተማ አስተዳደሩ በሚተዳደሩ ሆስፒታሎች በነጻ ሕምክና እንዲያገኙ ወስኖ ነበር።

አሁን በሁሉም ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች እንዲተገበር የተላለፈው ማሻሻያ ከዚህ ለየት ያለ መፍትሔ አቅርቧል። የጤና ሚኒስቴር ሰርኩላር፤ ቋሚ መፍትሔ እንዲሆን ያቀረበው "የጤና ዘርፍ ሠራተኞች፣ የትዳር አጋራቸው እና ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆቻቸው የጤና መድህን ሽፋን እንዲያገኙ" ማድረግን ነው።

ይህንን ሂደት ለማገዝ እንዲቻልም "በሁሉም የጤና መድህን አገልግሎቶች ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤቶች የመጠቀሚያ መለያ ቁጥር እንዲሰጥ" ትዕዛዝ አስተላልፏል።

እስከዚያው ድረስ እንዲተገበር የቀረበው አሠራር ደግሞ በጤና ተቋማት ውስጥ "የሠራተኛ ክሊኒክ" ማቋቋም የሚል ነው።

የጤና ተቋማት እንዲያዘጋጁ የታዘዘው "የሠራተኛ ክሊኒክ" የሕክምና ባለሙያዎች እና ቤተሰቦቻቸው "ብቻ የመታከሚያ አገልግሎት የሚያገኙበት" እንደሚሆን ተገልጿል።

ይህ ዓይነቱ ክሊኒክ "ተለይቶ እንዲዘጋጅ እና ሕክምና በነጻ እንዲያገኙ እንዲደረግ" ሲል ሚኒስቴሩ መመሪያ ሰጥቷል።

ሌላኛው የጤና ሚኒስቴር ማሻሻያ፤ የሕክምና ባለሙያዎች የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲቀርብላቸው የሚያደርግ ነው።

"ለጤና ባለሙያው በሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ልዩ ትኩረት በመስጠት የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲደረግ" ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ይህ አገልግሎት የሚቀርበውም "የጤና ተቋማት በአሁኑ ወቅት ያላቸውን ተሽከርካሪ በመጠቀም" እንደሚሆን ተጠቅሷል።

ከዚህ በተጨማሪም "የሕዝብ ትራንስፖርት ባለባቸው" ከተሞች የጤና ባለሙያዎችን የሥራ ባህሪ "ታሳቢ ያደረገ አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋጋር እንዲመቻች" ጠይቋል።

የጤና ባለሙያዎች ቅሬታ ሲያነሱባቸው ከነበሩ ጉዳዮች አንዱ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ የመንግሥት ሠራተኞች የሚቀርበው የፐብሊክ ሰርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጥበት ሰዓት የተወሰነ መሆኑ ነው።

የፐብሊክ ሰርቪስ ተሽከርካሪዎች የሚሰማሩበት የሥራ መግቢያ እና መውጫ ሰዓት ከጤና ባለሙያዎች የሥራ ጊዜ ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንዳልቻሉ ቅሬታቸውን ሲገልጹ ነበር።

በጤና ባለሙያዎች በኩል ሲነሳ የነበረው ጥያቄ የትርፍ ሰዓት ክፍያ ስሌት በሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን መመሪያ መሠረት እንዲተገበር የሚጠይቅ ነበር።

በ2014 ዓ.ም. የወጣው የትርፍ ሰዓት ሥራ የክፍያ መጠንን የተመለከተ መመሪያ፤ የተለያዩ ስሌቶች አስቀምጧል።

በመመሪያው መሠረት እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት ድረስ ለሚከወን የትርፍ ሰዓት ሥራ ክፍያ የሚፈጸመው ደመወዙ በ1.25 ተባዝቶ ነው። ከምሽቱ አራት ሰዓት በኋላ ይህ ክፍያ በ1.5 ይባዛል።

በሳምንቱ የእረፍት ቀናት የሚኖረው ብዜት ወደ 2 የሚያድግ ሲሆን በበዓል ቀናት ደግሞ በ2.5 ይባዛል።

ይህ መመሪያ ከጸደቀ ሦስት ዓመታት ቢያልፍም፤ የጤና ባለሙያዎች በምሽት፣ በእረፍት ቀናት እና በበዓላት ለሚያከናውኑት የትርፍ ሰዓት ሥራ ክፍያ ሚፈጸምላቸው ደመወዛቸው በአንድ ተባዝቶ እንደሆነ ሲገልጹ ቆይተዋል።

ጤና ሚኒስቴር ባለፈው ሳምንት ያሠራጨው ሰርኩላር ስሌቱ በመመሪያው "አግባብ ተግባራዊ እንዲደረግ" ሲል አሳስቧል።

በጤና ተቋማት ባለሙያዎች የሚመገቡበት እና የሚያርፉበት ክፍል እንዲመቻች ማድረግ እንዲሁም ለድኅረ ምረቃ (ሬዚደንት ሐኪሞች) "የመኖሪያ ቤት እንዲዘጋጅ ማድረግ" በሰርኩላሩ ላይ የተጠቀሱ ሌሎች ጉዳዮች ናቸው።

"ለጤናው ዘርፍ ሠራተኞች የቁጠባ እና ብድር ኅብረት ማኅበር በማቋቋም እንዲሁም አሁን ያሉትን በማጠናከር የተሻለ አገልግሎት እና የመነሻ ካፒታል እንዲያገኙ ድጋፍ እንዲደረግ" የሚለውም ተካትቷል።

ቢቢሲ፤ ውሳኔ የተሰጠባቸውን ማሻሻያዎች በተመለከተ ከጤና ሚኒስቴር ማብራሪያ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።

የሕክምና ባለሙያዎችን አድማ ሲያስተባብር የነበረው 'የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች ንቅናቄ' የተባለው ስብስብ፤ በጤና ሚኒስቴር እንዲሁም በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች እየተደረጉ ያሉ ማሻሻያዎችን "እንደ ጥሩ ጎን" እንደሚመለከተው ከአስተባባሪዎቹ አንዱ ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ለዘመናት ስናነሳቸው የነበሩ ጥያቄዎችን ለመፍታት የሚሄዱበትን መንገድ እናደንቃለን" የሚለው አስተባባሪው፤ አሁን ይፋ የተደረጉን ማሻሻያዎች ሊፈጸሙ የሚችሉ ናቸው ወይ የሚለው ላይ ግን ጥያቄ እንዳላቸው ገልጿል።

የሕክምና ባለሙያዎች እና ቤተሰቦቻቸው ነጻ ሕክምና እንዲያገኙ ሊዘረጋ የታሰበው አሠራር ለጥያቄው ምላሽ የሚሰጥ ቢሆንም "ውስንነት" ያለበት እንደሆነ አስረድቷል።

የጤና ሚኒስቴር ደብዳቤ የሚተገበር "ቀጥታ እንደወረደ" ሳይሆን በክልሎች እና በከተማ አስተዳደሮች "ማስፈጸሚያ መመሪያ" ተዘጋጅቶለት መሆኑን ጠቅሷል።

በዚህም የተነሳ ይህ አሠራር ሲተገበር ጤና ባለሙያዎች ሕክምና የሚያገኙት "በክልሎቻቸው ውስጥ በሚገኙ የጤና ተቋማት ብቻ" እንዲሆን ሊያደርግ እንደሚችል ስጋቱን ገልጿል።

ከክልሎች የጤና ባለሙያዎች "እንደ ጥቁር አንበሳ ባሉ የሀገሪቱ ትላልቅ ተቋማት" ሕምክና እንዲያገኙ አያስችልም የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸው አስረድቷል።

የንቅናቄው አስተባባሪዎች በተመሳሳይ የተግባራዊነት ጥያቄ የሚያነሱበት ሌላኛው ማሻሻያ የትራንስፖርት አቅርቦትን የተመለከተው ነው።

ሰርኩላሩ የጤና ተቋማቱ "ያላቸውን ተሽከርካሪ በመጠቀም" አገልግሎት እንዲቀርብ እንደሚያሳስብ የሚያነሳው አስተባባሪው፤ ተቋማቱ "እዚህ ግባ የሚባል መኪና የላቸውም" ይላል።

"ለምሳሌ ጤና ተቋማትን ብንወስድ አብዛኞቹ ከአምቡላንስ ባለፈው [ሌላ ተሽከርካሪ] የላቸውም" ሲልም የተግባራዊነት ጥያቄ የሚነሳበትን ምክንያት ይጠቅሳል።

አስተባባሪው እንደሚያስረዳው፤ ለሬዚደንት ሐኪሞች መኖሪያ ቤት እንዲዘጋጅ እንዲሁም ለባለሙያዎች መመገቢያ እና ማረፊያ ክፍሎች እንዲመቻቹ የቀረቡት ማሻሻያዎች ግንባታ የሚያስፈልጋቸው ስለሚሆኑ "ረጅም ጊዜ" ሊወስዱ ይችላሉ።

ለሬዚደንት ሐኪሞች የሚሆን መኖሪያ ቤት እስከሚገነባ ድረስ "ተገቢ የሆነ ክፍያ ተከፍሏቸው" ተከራይተው የሚኖሩበት መንገድ መመቻቸት አለበት የሚል አቋም እንዳላቸው ገልጿል።

የብድር እና ቁጠባ ማኅበራትን በተመለከተም፤ "እንደ መመሪያ ጥሩ ነው፤ ወደፊት ልጆቻችን ይጠቀሙ ይሆናል። እኛን እንኳ ብዙ ይጠቅማል የሚል እምነት የለንም፤ ምክንያቱም የምንቆጥበው ነገር የለም" ሲል ይህንን ውሳኔ በተመለከተ ያላቸውን ምልከታ አጋርቷል።

በጤና ሚኒስቴር ይፋ የተደረጉት ማሻሻያዎች በመስከረም ወር የተጠራውን ሁለተኛ ዙር አድማ ያስቀረው እንደሆነ ጥያቄ የቀረበለት አስተባባሪው፤ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥቧል።