የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጤና ባለሙያዎች በሆስፒታሎች ነጻ ህክምና እንዲያገኙ ፈቀደ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በስሩ የሚገኙ ጤና ባለሙያዎች እና ቤተሰቦቻቸው በከተማ አስተዳደሩ በሚተዳደሩ ሆስፒታሎች ውስጥ ነጻ ህክምና እንዲያገኙ ፈቀደ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጤና ባለሙያዎች ውሳኔውን ቢደግፉም፤ ይህ አሰራር አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ የፌደራል ሆስፒታሎች የሚሰሩ ባለሙያዎችን የማያካትት እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ባለሙያዎች በፌደራል ሆስፒታሎች ነጻ ህክምና እንዲያገኙ የማያስችል መሆኑን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ይህ "የጥቅማ ጥቅም ፓኬጅ" አሁን ከተጀመረው የ2018 በጀት ዓመት አንስቶ ተግባራዊ እንዲሆን መመሪያ ያስተላለፈው ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሐምሌ 17/2017 ዓ.ም. ነው። ይህንን መመሪያ የያዘው እና በቢሮው ኃላፊ ዶ/ር ጀማሉ ጀምበር የተፈረመው ደብዳቤ የተላከው በከተማ አስተዳደሩ ስር ለሚገኙ ሰባት ሆስፒታሎች እና የጤና ሳይንስ ኮሌጆች እንዲሁም ለክፍለ ከተማዎች ነው።

ይህ የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ የተላለፈው የጤና ባለሙያዎች ጥቅም ጥቅምን እና የጤና ስርዓትን የተመለከቱ ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱ ግንቦት ላይ በመላው ሀገሪቱ ከፊል አድማ ካደረጉ በኋላ ነው።

የጤና ባለሙያዎች አድማ ከመምታታቸው አስቀድሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲመለሱ ካቀረቧቸው 12 ጥያቄዎች መካከል የደመወዝ ጭማሪ እና የትርፍ ሰዓት ክፍያ አሰራር ወጥነት እንዲኖር የሚሉት ይገኙበታል።

"የቤት ኪራይ፣ የተጋላጭነት እንዲሁም የማበረታቻ አበል ላይ አስቸኳይ ማስተካከያ እንዲደረግ" እንዲሁም ሁሉም የጤና ባለሙያዎች እና ቤተሰቦቻቸው "በሁሉም የመንግሥት ሆነ የግል የጤና ተቋማት ላይ የነጻ ህክምና" እንዲያገኙ የሚሉትም ከጥያቄዎቹ መካከል ናቸው።

የጤና ባለሙያዎችን ያደረጉትን አድማ ተከትሎ 'ተወካዮቻቸው' ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ እና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር ውይይት አድርገዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት ከጤና ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርገው ነበር። በዚህ ውይይት ላይም ከንቲባ አዳነች "በከተማ አስተዳደሩ አቅም ለሚፈቱ" ጥያቄዎች መልስ እንደሚሰጥ ቃል ገብተው ነበር።

ባለፈው ሳምንት የተጻፈው የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ደብዳቤ እንደሚያስረዳው "የጤና ባለሙያዎች የጥቅማ ጥቅም ፓኬጅ" እንዲተገበር መመሪያ የተላለፈው የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ነው።

የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጀማሉ ፤ በከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ መሰረት "ተግባራዊ እንዲሆን የወጣ" መመሪያ መኖሩን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ደብዳቤው፤ "ካቢኔ ተወያይቶ ተግባራዊ እንዲሆኑ ውሳኔ ካሳለፈባቸው ጤና ባሙያዎች ጥቅማ ጥቅም ፓኬጅ ውስጥ ከዚህ ቀጥሎ በዝርዝር የቀረቡት ተግባራዊ እንዲሆኑ" በማለት አራት ጉዳዮችን ዘርዝሯል።

በቀዳሚነት የተጠቀሰው ጉዳይ የጤና ባሙያዎች የትርፍ ሰዓት ክፍያን የሚመለከት ነው። በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ የጤና ተቋማት ይህንን ክፍያ "የትርፍ ሰዓት አገልግሎት ክፍያ መሰረት ባደረገ እና በአገልግሎት አሰጣጥ ስታንዳርድ መሰረት" ተግባራዊ እንዲያደርጉ አዝዟል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት በከተማዋ ስራ ባሉ የጤና ተቋማት የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች እንደሚገልጹት የትርፍ ሰዓት ክፍያን የተመለከተው መመሪያ ከዚህ ቀደምም በአሰራር ደረጃ የተቀመጠ ነው።

ይሁን እንጂ የጤና ተቋማት የትርፍ ሰዓት ስሌቱን አሰራሩ በሚፈቅደው መሰረት ሲተገብሩ እንዳልነበረ አስረድተዋል።

በአሰራሩ መሰረት የቅዳሜ እና እሁድ፣ የበዓል ቀናት እንዲሁም ምሽት ከ4 ሰዓት በኋላ በስራ ላይ የሚያሳልፉ ባለሙያዎች የእነዚህ ቀናት የትርፍ ሰዓት ክፍያቸው ስሌት ከፍ ተደርጉ ሊሰላ እንደሚገባው በከተማዋ ሆስፒታል የሚሰራ አንድ ዶክተር አስረድቷል።

"እስካሁን ይሄ ተግባራዊ እየሆነ አልነበረም። ሲከፈለን የነበረው [የጤና ተቋማቱ] በሚፈልጉት መንገድ ነበር" ሲል እስካሁን የነበረውን አሰራር ገልጿል። አሁን የተላለፈው መመሪያ ይህንን አሰራር ወደ ወጥ ህጋዊው መንገድ ይቀይረዋል ብሎ እንደሚያስብም ጠቅሷል።

በደብዳቤው ላይ የተጠቀሰው ሁለተኛው ጉዳይ የጤና ባለሙያዎች ነጻ ህክምና ጋር የተያያዘ ነው። እስከአሁን በነበረው አሰራር በአዲስ አበባ ከተማ ስር በሚገኙ የጤና ተቋማት ሲታመሙ በነጻ ህክምና ማግኘት የሚችሉት በሚሰሩበት የጤና ተቋም ውስጥ ብቻ እንደነበር ቢቢሲ ያነጋገራቸው የጤና ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ይህ አሰራር በጤና ተቋማት ደረጃ "የተለመደ አሰራር" እንጂ በከተማ አስተዳደሩ "የተወሰነ" እንዳልነበረ አንድ የጤና ባለሙያ ገልጿል።

በዚህም ምክንያት ከሚሰሩበት የጤና ተቋም አቅም በላይ የሆነ የጤና እክል በሚያጋጥማቸው ጊዜ የህክምና ወጪውን በራሳቸውን ለመሸፈን እንደሚገደዱ አስረድተዋል።

የጤና ባለሙያዎቹ በሚሰሩበት ተቋም የሚያገኙት ነጻ ህክናም ቢሆን ቤተሰቦቻቸውን የሚያካትት አለመሆኑን አክለዋል።

አሁን የከተማ አስተዳደሩ ያስተላለፈው መመሪያ እነዚህ አሰራሮች የቀየረ ነው። በአዲሱ አሰራር መሰረት የጤና ባለሙያዎች "ቅድሚያ በሚሰሩበት የጤና ተቋም በሌሎች የከተማ አስተዳደሩ የመንግስት ጤና ጣቢያዎች እና ሆስፒታሎች ነጻ ህክምና እንዲያገኙ" የሚያደርግ ነው።

ይህ ነጻ ህክምና ከጤና ባለሙያዎች በተጨማሪ "የትዳር አጋራቸው እና ከ18 ዓመት በታች የሆኑ ልጆቻቸውን" ጭምር እንደሚያካትት ደብዳቤው ላይ ሰፍሯል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር ከሚገኙት ሆስፒታሎች መካከል ጋንዲ መታሰቢያ፣ ዘውዲቱ መታሰቢያ፣ ዳግማዊ ሚኒሊክ፣ ራስ ደስታ እና ጥሩነሽ ቤጂንግ ይገኙበታል። የካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ እና ዳግማዊ ሚኒሊክ ጤና ሳይንስ ኮሌጅም የሚተዳደሩት በከተማ አስተዳደሩ ነው።

ደብዳቤው ላይ የተጠቀሰው ሌላኛው የጥቅም ጥቅም ፓኬጅ አካል፤ "በሁሉም የጤና ተቋማት ውስጥ የሸማቾች የህብረት ስራ ማህበራት ሱቆች" እንዲቋቋሙ የሚያዝዝ ነው። ይህ የሚደረገው "የኑሮ ውድነቱን ጫና ለማቃለል" እንደሆነ የሚያስረዳው ደብዳቤው፤ በእነዚህ ሱቆች ውስጥ "በመንግሥት የድጎማ የሚቀርቡ ምርቶችን የጤና ባለሙያዎች በቀላሉ ማግኘት እንዲችሉ ሁኔታዎች እንዲመቻችላቸው" ትዕዛዝ አስተላልፏል።

ሌላኛው የከተማ አስተዳደሩ ውሳኔ፤ "በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮጀክት በጊዜያዊነት የተቀጠሩ" ሰራተኞችን በቋሚነት መቅጠርን የሚመለከት ነው። እነዚህ ሰራተኞች "የቤት ለቤት የወላጆች እና አሳዳጊዎች ምክር ሰጪ" እንደሆኑ ደብዳቤው ላይ ተጠቅሷል።

በጤና ባለሙያዎች እንቅስቃሴ ውስጥ የነበረ አንድ ባለሙያ ለቢቢሲ እንደገለጸው፤ በዚህ መንገድ ስራ ላይ የነበሩት በአብዛኛው ነርሶች ናቸው። የእነዚህ ባለሙያዎች ብዛት "በአንድ ተቋም እስከ 50" ሊደርስ እንደሚችል የሚጠቅሰው ባለሙያው፤ የስራ ቅጥር ውሉ ሊቋረጥ ይችላል የሚል ስጋት ውስጥ እንደነበሩ ተናግሯል።

የከተማ አስተዳደሩ ባለፈው ሳምንት በጻፈው ደብዳቤ፤ "በቢሮው፣ በክፍለ ከተማ እና በጤና ጣቢያዎች ላይ የሚገኙ ሱፐርቫይዘሮች እና ኮኦርዲኔተሮች አሰራሩን ጠብቆ ቋሚ ሰራተኞች እንዲሆኑ" በማለት መመሪያ ተሰጥቷል።

ደብዳቤው አክሎም፤ እነዚህ "የጥቅማ ጥቅም ፓኬጆች ከ2018 በጀት ዓመት ጀምሮ ለጤና ባለሙያዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ክትትልና ድጋፍ እንድታደርጉ" ሲል ደብዳቤው የተጻፈላቸውን የጤና ተቋማት እና ክፍለ ከተሞች አሳስቧል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው በከተማው ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎች ይህንን ማሻሻያ በተመለከተ እስካሁን ድረስ በይፋ የተደረገላቸው ገለጻ አለመኖሩን ገልጸዋል። አንድ የጤና ባለሙያ በበኩሉ በሚሰራበት ተቋም ውስጥ ይህንን ውሳኔ ለመተግበር እየተደረጉ ያሉ እንቅስቃሴዎች ስለመኖራቸው እንደሚያውቅ ተናግሯል።

የጤና ባለሙያው የተደረገውን ማሻሻያ "እንደ ጥሩ ጅምር" እንደሚመለከተው ለቢቢሲ ተናግሯል። ይሁን እንጂ፤ ይህ ማሻሻያ ተግባራዊ የሚሆነው በአዲስ አበባ ከተማ ስር ባሉ ተቋማት ውስጥ ላሉ ባለሙያዎች እንደሆነ፤ ባለሙያዎች ያቀረቡት ጥያቄ ደግሞ በሀገር አቀፍ ደረጃ ምላሽ እንዲሰጥ እንደነበር አንስቷል።

ሌላ ባለሙያ በበኩሉ፤ "ከዚህ በኋላ አድማ ወይም እንቅስቃሴ ይቀጥላል የሚል ሀሳብ ስላለ አዲስ አበባ ያለውን ባለሙያ ዝም የማስባል ሙከራ ነው እንጂ በጭራሽ ጥያቄ የሚመልስ አካሄድ አይደለም" በማለት ተችቷል።

የተሰጠውን የህክምና ሽፋን በምሳሌነት የሚያነሳው ባለሙያው ይህ ማሻሻያ አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኙ ነገር ግን በከተማ አስተዳደሩ ስር ባልሆኑ እንደ ጥቁር አንበሳ እና ቅዱስ ጳውሎስ ባሉ ሆስፒታሎች የሚሰሩ ባለሙያዎችን እንደማያካትት ጠቅሷል።

ሌላ ባለሙያ በበኩሉ በከተማው የጤና ተቋማት የሚሰሩ ባለሙያዎች አሁንም ቢሆን በፌደራል መንግሥት ስር በሚገኙ የጤና ተቋማት ህክምና ለማግኘት ቢፈልጉ ወጪውን በራሳቸውን መሸፈን እንደሚኖርባቸው ገልጿል። ከጊዜያዊ ሰራተኞች ቅጥር እና ከሸማች ማህበራት ሱቆች መከፈት ጋር በተያያዘ የተላለፉ ውሳኔዎችንም ተግባራዊ እስከሚሆኑ ድረስ የሚመለከታቸው በጥንቃቄ እንደሆነ ተናግሯል።

ቢቢሲ፤ ከአዲስ አበባ ከተማ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ኃብት ልማት እንዲሁን ጤና ቢሮዎች ስለተደረገው ማሻሻያ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት እና ስለተነሱ ስጋቶች ጥያቄ ለማቅረብ ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም።