በጎንደር ከተማ የሁለት ዓመት ሕጻን በአጋቾቿ መገደሏ ቁጣን ቀሰቀሰ

በአማራ ክልል ጎንደር ከተማ የሁለት ዓመታ ሕጻን ታግታ ከተወሰደች በኋላ ትናንት ሰኞ ነሐሴ 27/2016 ዓ.ም. ተገድላ አስክሬኗ በወላጆቿ መኖሪያ ግቢ ውስጥ ተጥሎ ተገኘ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የታጋቿ የቅርብ ቤተሰብ ነን ያሉ ግለሰብ ኖላዊት ዘገየ የተባለችው የሁለት ዓመት ታዳጊ ከምትኖርበት ቤት የታገተችው ነሐሴ 24/2016 ዓ.ም. መሆኑን ይናገራሉ።

ይሁን እንጂ አጋቾች ከጠየቁት የማስለቀቂያ ገንዘብ አብዛኛውን መጠን ቢቀበሉም “ጡጦ ያልጣለችውን” ታዳጊ ገድለው መጣላቸውን የቤተሰብ አባሉ ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የሕጻኗን በአጋቾቿ ተገድሎ መጣል አስመልክቶ የተቆጡ የጎንደር ከተማ ነዋሪዎች በትናንትናው ዕለት አደባባይ የወጡ ቢሆንም፣ ከከተማዋ የጸጥታ ኃይሎች ጋር መጋጨታቸውን እና ጉዳት መድረሱን የዓይን እማኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኖላዊት ዘገየ የተባለችው ይህች የሁለት ዓመት ታዳጊ ለቤተሰቧ ብቸኛ ልጅ ነበረች።

ታዳጊዋ የተወሰደችው ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ አርብ ነሐሴ 24/2016 ዓ.ም. ረፋድ 3፡30 ላይ ግቢዋ ውስጥ ስትጫወት መሆኑን የቤተሰብ አባሉ ይናገራሉ።

የኖላዊትን መጥፋት ተከትሎ የአካባቢው ሰው ታዳጊዋን ፍለጋ በየአቅጣጫው ወጥቶ ነበር።

ይሁን እንጂ የታጋቿ ወላጆች ተከራይተው በሚኖሩበት ግቢ ውስጥ በአጋቾቹ የተጣለ ማስታወሻ ወረቀት ከተገኘ በኋላ ኖላዊት መታፈኗ እንደታወቀ የቤተሰብ አባሉ አስረድተዋል።

“በሚኖሩበት ግቢ ውስጥ እኛ አግተን ወስደናታል እስክንደውልላችሁ ታገሱ” የሚል መልዕክት የሰፈረበት ወረቀት መገኘቱን የቤተሰብ አባሉ ይናገራሉ።

በመኖርያ ቤቱ ውስጥ ወዳጅ ዘመድ ተሰብሰብቦ በነበረበት ወቅትም አጋቾቹ “ይህንን ካልበተናችሁ እንገላታለን። ለፖሊስ ብታመለክቱም እንገላታለን” የሚል ማስፈራርያ አዘል ጽሑፍ ግቢ ውስጥ መጣላቸውን አስረድተዋል።

በመቀጠልም አጋቾቹ የማስለቀቂያ 1 ሚሊዮን ብር እንዲከፈላቸው የጠየቁ ሲሆን የታዳጊዋ አባት ተቀጥሮ የሚሰራ ሹፌር በመሆኑ “በድርድር 300 ሺህ ብር ለመቀበል መስማማታቸውን” ገልጸዋል።

“መጀመርያ 1 ሚሊዮን ብር ነበር የጠየቁት። አባቷ ተቀጥሮ የሚሰራ ሹፌር በመሆኑ ተለምነው በ300 ሺህ ብር ተስማሙ” ይላሉ።

ይሁን እንጂ የ300ሺህ ብር ክፍያውም ከሕጻን ኖላዊት ወላጆች እና ከወዳጅ ዘመድ አቅም በላይ ሆኖ በልመና የተገኘው ገንዘብ ግን 200 ሺህ ብር እንደነበር እና 100 ሺህ ብር መጉደሉን ይናገራሉ።

ይሁንና ገንዘቡን አጋቾቹ በባጃጅ (በባለ ሦስት እግር ተሸከርካሪ) መጥተው ቢወስዱም ታዳጊዋን ገድለው ከወላጆቿ መኖሪያ ቤት ጓሮ አስከሬኗን መጣላቸውን በሐዘን ውስጥ ሆነው እኚሁ የቤተሰብ አባል አስረድተዋል።

“ምናልባት 100 ሺህ በመጉደሉ ይሆናል የገደሏት” የሚሉት ግለሰቡ የባጃጁ ሰሌዳ ቁጥር፣እና የሚደውሉበትን ስልክ ቁጥር መያዛቸውን ይናገራሉ።

የታዳጊዋን ግድያ ተከትሎ በጎንደር ከተማ ቁጣ መቀስቀሱን ጭምር ይህ የቤተሰብ አባል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ትናንት ሰኞ አመሻሽ ላይ ወላጅ አባቷ እንዲሁም ሌሎች የከተማዋ ነዋሪዎች የሕጻኗን አስከሬን በመያዝ “ፍትሕ” እየጠየቁ ወደ ከተማዋ አደባባይ ከወጡ በኋላ ከአድማ በታኝ የጸጥታ አካላት ጋር መጋጨታቸውን ተናግረዋል።

በመንግሥት ሰላም አስከባሪ አካላት እና አደባባይ በወጣው ኅብረተሰብ መካከል አለመግባባት መፈጠሩን ተከትሎ ጸጥታ አስከባሪዎች ጥይት ተኩሰው የተጎዱ ሰዎች መኖራቸውንም ጨምረው አስረድተዋል።

ከሕጻን ኖላዊት በተጨማሪ በቅርቡ በጎንደር ከተማ ከእገታ ጋር በተያያዘ የተገደሉ እናትና ልጅ መኖራቸውን የሚናገሩት የከተማዋ ነዋሪ፣ ከአንዴ በላይ የታገቱ፣ በፍራቻ ምክንያት አካባቢውን ለቅቀው የሄዱ መኖራቸውን ይናገራሉ።

በጎንደር እገታ እና ግድያ “ንግድ ሆኗል” የሚሉት እኚህ የቤተሰብ አባል በርካቶች በሀብታቸው ምክንያት ዒላማ በመደረጋቸው ከተማዋን ለቅቀው ለመውጣት መገደዳቸውን ይናገራሉ።

አክለውም አጋቾች “መዋቅር ያለው፣ ጠንካራ፣ ተሽከርካሪ ያላቸው በምሽት የሚንቀሳቅሱ” መሆናቸውን ያስረዳሉ።

ይህ የቤተሰብ አባል እንዲህ ሊሉ የቻሉበትንም ምክንያት ሲያስረዱ ከአጋቾቹ መካከል ሁል ጊዜ የሚደውለው ግለሰብ ደውሎ ገንዘብ እንዲቀንሱላቸው ሲጠየቅ “እኔ ስልክ ደዋይ ነኝ። ሌሎቹ ናቸው ገንዘቡን የሚወስኑት፤ እጠይቅልሀለሁ” የሚል መልስ እንደሚሰጥ ይገልጻሉ።

ሰዎቹን አግተው የሚወስዱ፣ ስምሪት የሚሰጡ፣ ገንዘቡን የሚቀበሉ የተለያየ ግለሰቦች መኖራቸውን እና የተደራጁ መሆናቸውን ስልክ ከደወለው ግለሰብ መረዳታቸውንም ጨምረው ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በእገታ ሰበብ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች መኖራቸውን የሚናገሩት ግለሰቡ “ጡጦ የሚጠባ ሕጻን አግቶ ገድሎ በር ላይ አምጥቶ መጣል ግን ለመጀመርያ ጊዜ የታየ ነው” ይላሉ።

በጎንደር ከተማ በእገታ ወንጀል የተጠረጠሩ 31 ግለሰቦች ፖሊስ በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል::

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ውስጥ የሚከሰቱ እገታዎች ሕዝቡን ሰላም ነስቷል። አልፎ አልፎ በተለያዩ አካባቢዎች ይፈጸም የነበረው እገታ አሁን መልኩን ቀይሮ በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍል ማጋጠሙን የሚገልጹ መረጃዎች እየወጡ ነው።

በተለይ በአማራ እና ኦሮሚያ ክልል ለገንዘብ ሲባል የሚፈጸመው እገታ በርካቶችን ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ምስቅልቅል ዳርጓል።

ታጋቾችን ለማስለቀቅ ከጥቂት ሺህ ብሮች ጀምሮ እስከ ሚሊዮኖች ድረስ ለመክፈል የተገደዱም በርካቶች እንዳሉ ሆነው በአጋቾቻቸው እጅ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች እንዲሁ በርካቶች ናቸው።