ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለሩሲያ ይሰልላል ተብሎ የሚጠረጠረው ዓሳ ነባሪ ኖርዌይ ውስጥ ሞቶ ተገኘ
ለሩሲያ እንዲሰልል ስልጠና ተሰጥቶታል ተብሎ የሚጠረጠረው ቤሉጋ ዓሳ ነባሪ የተባለው የባሕር እንስሳ በኖርዌት ጠረፍ ሞቶ ተገኘ።
ህቫልድርሚር የተሰኘ ቅፅል ስም የተሰጠው ይህ ዓሳ ነባሪ በደቡብ ምዕራቧ ሪሳቪካ ከተማ ሞቶ ሲንሳፈፍ ከተገኘ በኋላ ለምርመራ ተወስዷል።
የሩሲያው “ሰላይ ዓሳ ነባሪ” የሚል ስም የተሰጠው ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት በኖርዌይ ግዛት ከታየ በኋላ ነው። በወቅቱ ዌሉ ጎፕሮ የተባለው ካሜራ ተገጥሞለት የተገኘ ሲሆን ካሜራው “የሴይንት ፒተርስበርግ ንብረት” የሚል ፅሑፍ ይነብበት ነበር።
ይህን ተከትሎ ይህ እንስሳ ሰላይ ሳይሆን አይቀርም የሚሉ ወሬዎች መዛመት ጀመሩ። ባለሙያዎች ከዚህ ቀደም ሰላይ ዌሎች ነበሩ ይላሉ።
ሩሲያ ለዚህ ወሬ ምንም ዓይነት ምላሽ ሰጥታ አታውቅም።
የዌሉን እንቅስቃሴ ላለፉት ዓመታት ሲከታተል የነበው ማሪን ማይንድ የተባለ ድርጅት ነው የእንስሳውን ሞት ያረጋገጠው።
የማሪን ማይንድ መሥራች ሴባስትያን ስትራንድ ለኤኤፍፒ የዜና ወኪል እንደተናገሩት የሞቱ ምክንያት እስካሁን የማይታወቅ ሲሆን የህቫልድርሚር ሰውነት ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አይታይም።
የዌሉ ሬሳ ወደ ቤተ-ሙከራ ተልኮ ምርመራ እንደሚደረግበት የድርጅቱ ኃላፊ ተናግረዋል።
ቤሉጋ ዓሳ ነባሪ የሚባሉት አጥቢ የዓሳ ነባሪ ዝርያዎች እስከ 60 ዓመታት መኖር የሚችሉ ሲሆኑ የህቫልድርሚር ዕድሜ 15 ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
ህቫልድርሚር በአውሮፓውያኑ 2019 ኢኖግያ የተሰኘችው ደሴት አቅራቢያ ነው ወደ ኖርዌያዊያን መርከበኞች ተጠግቶ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው። ይህ ሥፍራ ከሩሲያ ሰሜናዊ ባሕር ኃይል 415 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ነው።
ቤሉጋ ዌሎች በአርክቲክ ውቅያኖስ በደቡብ ጫፍ ብዙም ስለማይታዩ ነበር ይህ ዓሳ ነባሪ መነጋገሪያ የነበረው።
የኖርዌይ የአገር ውስጥ ደኅንነት ኤጀንሲ የዌሉን እንቅስቃሴ ካጠና በኋላ ምናልባት በሩሲያዊያን ሰላይ እንዲሆን ስልጠና ሳይሰጠው አይቀርም ብሎ ነበር። ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ህቫልድርሚር ከሌሎች ዌሎች በተለይ ለሰዎች ቅርብ መሆኑ ነው።
ህቫልድርሚር የተሰኘውን ስሙን ያገኘው ከኖርዌያን ሲሆን ህቫል ማለት ዓሳ ነባሪ ሲሆን ድሚር ደግሞ ከፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ስም የተወሰደ ነው።
ሩሲያ የባሕር ውስጥ አጥቢ እንስሳትን ለወታደራዊ አገልግሎት እንደምታውል ትታማለች። ህቫልድርሚር በሩሲያ ባሕር ኃይል ነው ስልጠና የተሰጠው ስለሚለው ጉዳይ ከሞስኮው አስተያየት ተሰጥቶ አይታወቅም። የባሕር ውስጥ እንስሳትን ለወታደራዊ ጥቅም ታውላለች የሚለውን ሐሳብም ታጣጥላለች።