ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሶማሊያ እና ግብጽን ወታደራዊ ስምምነት የተቃወሙት የፓርላማ አባል፤ ከልዩ ልዑክ ኃላፊነታቸው ተነሱ
የግብጽ ጦር በሶማሊያ መሰማራቱን የተቃወሙ የፕሬዝዳንቱ ልዩ ልዑክ እና የምክር ቤት አባል ከኃላፊነታቸው ተነሱ።
ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን የግብጽ ሠራዊት ወደ ሶማሊያ መግባቱን የሚቃወም መግለጫ የሰጡት የሳውዝ ዌስት ግዛት የፓርላማ ቤት አባል አብዲረሺድ ሞሃመድ ኑር ጂሌይ፤ በአገሪቱ ፕሬዝዳንት ተሹመውበት ከነበረው “የጤና እና ስነ ምግብ ልዩ ልዑክ” ኃላፊነታቸው ተነስተዋል።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ፤ የልዩ ልዑክ ከኃላፊነት መነሳት ባስታወቁበት መግለጫቸው የአገሪቱ ዜጎች የአገራቸውን ሉዐላዊነት “ለመጠበቅ እንዲነሱ” ጠይቀዋል።
ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ፤ ትናንት እሁድ ነሐሴ 26/2016 ዓ.ም. የጤና እና ስነ ምግብ ልዩ ልዑኩን ከኃላፊነት ማንሳታቸውን ያስታወቁት ከሳውዝ ዌስት ግዛት የተወከሉ የፓርላማ አባላት መግለጫ መስጠታቸውን ተከትሎ ነው።
የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት አባል ከሆኑ ግዛቶች አንዱ የሆነው ሳውዝ ዌስት፤ ከኢትዮጵያ ጋር የሚያዋስን ድንበር አለው።
የፓርላማ አባላቱ በትናንትናው ዕለት ካደረጉት ውይይት በኋላ የሰጡት መግለጫ በዋነኛነት ሶማሊያ እና ግብጽ በገቡት ወታደራዊ ስምምነት ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ሁለቱ አገራት ፕሬዝዳቶቻቸው በተገኙበት በካይሮ ወታደራዊ ስምምነቱን የተፈራረሙት ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር።
ይህንን ስምምነት ተከትከሎም ባለፈው ሳምንት ሁለት የግብጽ የጦር አውሮፕላኖች ጦር መሳሪያዎችን ጭነው ሞቃዲሾ ደርሰዋል።
በትናንትናው ዕለት መግለጫ የሰጡት የሳውዝ ዌስት ግዛት የተወከሉ የፌደራል ፓርላማ አባላት፤ ይህ ስምምት ለፓርላማ አለመቅረቡን በመጥቀስ ተቃውመዋል። የሶማሊያው ፕሬዝዳንት “እርስ በእርሳቸው ከሚቃረኑ አገራት ጋር የተለያዩ ስምምነቶች ገብተዋል” ሲሉ ወቅሰዋል።
የፓርላማ አባላቱ፤ ስምምነቱ “ወደ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ የሚያስገባ ነው” ብለው እንደሚያምኑም ገልጸዋል።
ስምምነቱ “የናይል ጉዳይ” ወደ ሶማሊያ የሚያመጣ እና “በአፍሪካ ቀንድ ላይ ጦርነትን ሊያመጣ የሚችል” እንደሆነ ያስታወቁት የፓርላማ አባላቱ፤ ይህ አይነቱ ግጭት በተለይም በሳውዝ ዌስት ግዛት ህዝብ ላይ ችግር የሚያስከትል መሆኑን ጠቁመዋል።
“የአገሪቱ አመራር ህዝቡን ወደ ግጭት እና ጦርነት ሊያስገባ አይገባም። የሚቃረኑ አገራት እንዲዋጉ ግዛታችን ውስጥ ማስገባት የሚመከር አይደለም” ሲሉም ተቃወመዋል።
ይህንን የፓርላማ አባላቱ መግለጫ ለመገናኛ ብዙሃን በንባብ ያሰሙት የሳውዝ ዌስት ግዛት የፓርላማ አባል የሆኑት አብዲረሺድ ሞሃመድ ኑር ጂሌይ ናቸው። የህክምና ባለሙያ የሆኑት አብዲረሺድ፤ “የጤና እና ስነ ምግብ ልዩ ልዑክ” እንዲሆኑ በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ የተሾሙት በመጋቢት ወር ነበር።
ይህ መግለጫ ከተሰጠ በኋላ ትናንት ምሽት የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ባወጣው መግለጫ ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ፤ የጤና እና ስነ ምግብ ልዩ ልዑኩን ከኃላፊነት ማንሳታቸውን አስታውቋል። መግለጫው አብዲረሺድ ሞሃመድ ኑር ጂሌይ ከኃላፊነት የተነሱበትም ምክንያት አልጠቀሰም።
ይሁንና ፕሬዝዳንቱ፤ ሶማሊያ ያጋጠማትን “የህልውና ስጋት” ለመከላከል የአገሪቱ ዜጎች እና ባለስልጣናት እንዲቆሙ ማሳሰባቸው በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል።
የቪላ ሶማሊያ መግለጫ፤ “የሪፐብሊኩ ፕሬዝዳንት፤ የሶማሊያ አገር ሉዓላዊነት፣ አብሮነት እና አንድነትን በሚጻረር መልኩ ከውጪ [አካላት] የህልውና ስጋት በመጋረጡ ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች እና ባለስልጣናት አገራቸውን የመከላከል ኃላፊነታቸውን ለመወጣት እንዲቆሙ አሳስበዋል” ብሏል።
የሶማሊያ መንግሥት ከግብጽ ጋር የገባው ስምምነት ተቃውሞ የገጠመው ከሳውዝ ዌስት ግዛት ከተወከሉት የፓርላማ አባላት ብቻ አይደለም። ቅዳሜ ዕለት የሳዌዝ ዌስት ግዛት ውስጥ የምትገኘው ሁዱር ከተማ ነዋሪዎች በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮ (አትሚስ) ውስጥ እያገለገሉ ላሉት የኢትዮጵያ ወታደሮች ድጋፋቸውን በመግለጽ ሰልፍ ማድረጋቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ሰልፍ የወጡት ነዋሪዎች፤ በመጪው ዓመት ጥር ወር የሚጠናቀቀውን በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት የሽግግር ተልዕኮን (አትሚስ) በሚተካው አዲሱ የሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ውስጥ የግብጽ ወታደሮች እንደሚሰማሩ መገለጹን እንደተቃወሙም ተዘግቧል።