በአሜሪካ የፍርድ ቤት ማዘዣ ለመስጠት የሞከሩ ሶስት ፖሊሶች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Kentucky Police Department
በአሜሪካ የኬንታኪ ግዛት ሶስት ፖሊሶች በቤት ውስጥ ሁከት ፈፅሟል ተብሎ በተከሰሰ ግለሰብ ላይ የፍርድ ቤት ማዘዣ ለመስጠት ሲሞክሩ በተተኮሰባቸው ጥይት ተገደሉ።
ፖሊስ የ49 ዓመቱን ተጠርጣሪ ከከፈተው ተኩስ በኋላ በቁጥጥር ስር አውሎታል።
የፍሎይድ ግዛት ፖሊስ ኃላፊ ጆን ሃንት እንደተናገሩት ፖሊሶቹ የተጠርጣሪው ቤት ሲደርሱ የገጠማቸው “ሲኦል” የሚባል ነው ሲሉ ገልጸውታል።
ክስተቱ ያጋጠመው በምስራቅ ኬንታኪ ተራራማ የምትገኘው አሌን የተባለችው ትንሽ ከተማ ነው። ከተማዋ 166 ህዝብ ብቻ የሚኖርባት ሲሆን አራት ሰዎች ቆስለዋል ተብሏል።
በያዝነው ሳምንት ሐሙስ እለት በተተኮሰባቸው ጥይት የሞቱት ፖሊሶች ካፒቴን ራፍል ፍሬዠር፣ ምክትል የፖሊስ ኃላፊ ዊልያም ፔትሪ እና ጃኮብ ቻፊንስ ናቸው።
በዚህ ጥቃት ሟቹ ፖሊስ ጃኮብ ይዞት ከነበረው የፖሊስ ውሾች አንዱ ኬ9 ድራጎ ሞቷል።
ካፕቴን ፍሬዠር በፕሬስተንበርግ ኬንታኪ ፖሊስ ቢሮ ለ39 አመታት አገልግሏል
“እስከ ህልፈቱ ድረስ በክብር እና በታማኝነት” እንዳገለገለም መስሪያ ቤቱ ተናግሯል።
ፖሊሶቹ አመሻሹ ከምሽቱ አንድ ሰዓት በፊት ተጠርጣሪው ቤት ሲደርሱ የተኩስ እሩምታ ውስጥ እንደደረሱ ተገልጿል።
ተኩሱም ለሶስት ሰዓታት ያህል የቀጠለ ሲሆን በመጨረሻም ተጠርጣሪው ላንስ ስቶርዝ ከቤተሰቡ አባላት ጋር በተደረገ ድርድር እጁን ሰጥቷል።
ግለሰቡ በፖሊስ ግድያ ሁለት ክሶች፣ በግድያ ሙከራ አምስት ክሶች እና ሌሎችም ተደራራቢ ክሶች ቀርበውበታል።
“ይህች ጥዋት ለሁላችንም ፈታኝ ናት ሲሉ የኬንታኪ ግዛት አስተዳዳሪ አንዲ በሼር በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ላይ አጋርተዋል።
"የፍሎይድ ግዛት እንዲሁም ጀግና ፖሊሶቻችን በትናንትናው እለት በአሳዛኝ ሁኔታ አጥተናቸዋል” ብለዋል።
የኬንታኪ ግዛት ፖሊስ በጥቃቱ ላይ ምርመራ ከፍተዋል።












