ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
4 አሳ አስጋሪዎች ባሕር ላይ ያገኙት መጠጥ አልኮል መስሏቸው ጠጥተው ተመርዘው ሞቱ
በስሪ ላንካ አራት አሳ አስጋሪዎች ባሕር ላይ ያገኙት መጠጥ አልኮል መስሏቸው ከጠጡ በኋላ ተመርዘው ሞቱ።
የአካባቢው ባለስልጣናት በጠርሙስ ታሽጎ የነበረውን ምንነቱ ያልታወቀ መጠጥ የጠጡ ሁለት ተጨማሪ ሰዎች ለሕይወት አስጊ የሆነ የጤና መቃወስ ገጥሟቸዋል ብለዋል።
የስሪ ላንካ ባሕር ኃይል ይፋ እንዳደረገው ከሆነ ግለሰቦቹ አሳ ለማጥመድ የባሕር ላይ ጉዞ ሲያደርጉ ያገኙት መጠጥ አልኮል መስሏቸው ጠጥተውታል ብሏል።
አሳ አስጋሪዎቹ ከባሕር ጠረፍ እርቀው ስለነበረ አስቸኳይ የሕክምና እርዳታ በአገሪቱ የባሕር ኃይል ለመስጠት ቢሞክረም የአራቱን ሰዎች ሕይወት ማዳን አልተቻለም።
የአገሪቱ የአሳ ሃብት መስሪያ ቤት ኃላፊ ሱሳንታ ካሃዋቱ በጠና የታመሙ አሳ አስጋሪዎችን እና የሟቾችን አስክሬን ይዞ እንደሚመለስ ተናግረዋል።
ሱሳንታ ካሃዋቱ ጨምረው እንደተናገሩት አሳ አስጋሪዎቹ ያገኙትን ምንነቱ ያልታወቀ መጠጥ ከራሳቸው አልፎ በአካባቢው ለነበሩ ሌሎች አሳ አስጋሪዎች አካፍለዋል ብለዋል።
በዚህም የአካባቢው ባለስልጣናት ሌሎች ሰዎች ምንነቱ ያልታወቀውን መጠጥ እንዳይጠጡ ማሳሰቢያ አድርሰናል ብለዋል።
ባለስልጣናትን የመጠጡን ይዘት ምንነት በማጣራት ላይ ናቸው ተብሏል።