ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ቱርክ ውስጥ ሊወያዩ መሆኑ ተነገረ
በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ያለመ ንግግር ለማድረግ የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቱርክ መግባታቸው ተነገረ።
ዛሬ ሰኔ 24/2016 ዓ.ም. በሚደረው ውይይት ላይ ለመሳተፍ የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ፊቅ እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ አንካራ መግባታቸው ምንጮች ለቢቢሲ ሶማልኛ ተናግረዋል።
ከስድስት ወራት በፊት ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የባሕር በር ለማግኘት የሚያስችላትን የመግባቢያ ሠነደ መፈረሟ በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ መካከል ከፍተኛ ውጥረት ተፈጥሯል።
የመግባቢያው ሠነድ ኢትዮጵያ ነጻ አገር መሆኗን ላወጀችው ሶማሊላንድ ዕውቅናን የሚሰጥ ሲሆን፤ ሶማሊላንድ በምላሹ ለኢትዮጵያ የባሕር በር እና የባሕር ኃይል ሰፈር የሚውል የባሕር ጠረፍ እንድታገኝ የሚፈቅድ ስለመሆኑ መዘገቡ ይታወሳል።
ይሁን እንጂ ይህ ስምምነት ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ፣ ሞቃዲሾ የአዲስ አበባ እና የሃርጌሳ ስምምነት የሶማሊያን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የሚጥስ ድርጊት ነው ስትል ቆይታለች።
በዚህ ያልተገደበችው ሶማሊያ በሞቃዲሾ የሚገኘቱን የኢትዮጵያን አምባሳደር ከአገር አስወጥታ በአዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሯን መጥራቷ ይታወሳል።
ከዚህ በተጨማሪም የሶማሊያ መንግሥት በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ስር በሶማሊያ በሰላም ማስከበር ሥራ ላይ ተሰማርቶ የሚገኘውን የኢትዮጵያን ሠራዊት ከግዛቷ እንደምታስወጣ አስታውቃለች።
“ድርድር”
ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ የሚያደርጉት ንግግር “ድርድር” እንደሆነ የሶማሊያ የውጪ ጉዳይ ሚስቴር አመልክቷል።
የውጭ ጉዳይ ሚስቴሩ ዘግይቶ ከኤክስ ገጹ ላይ በሰረዘው ጽሑፍ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቱርክ አደራዳሪነት ለሚደረገው ንግግር አንካራ ገብተዋል ብሏል።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትናንት እሁድ ኤክስ ገጹ ላይ ለጥፎት የነበረው ጸሑፍ “የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከልዑክ ቡድናቸው ጋር በመሆን በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል በቱርክ አደራዳሪነት ለሚደረገው ውይይት ወደ አንካራ ቱርክ አቅንተዋል” ብሎ ነበር።
በሁለቱ አገራት መካከል ስለሚደረገው ንግግር ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተሰጠ ማረጋገጫ ባይኖርም የቢቢሲ ሶማልኛ ምንጮች አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ከሶማሊያው አቻቸው ቀደም ብለው ቱርክ መግባታቸውን ተናግረዋል።
ቱርክ ለምን አደራዳሪ ሆነች?
የባሕር በር ስምምነቱን ተከትሎ በሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ አገራት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት አገራት እና ቀጠናዊ ድርጅቶች ውጥረት እንዲረግብ በተደጋጋሚ ሲጠይቁ ነበር።
አዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ አለመግባባታቸውን በንግግር እንዲፈቱ ከጠየቁት መካከል አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ የአፍሪካ ኅብረት፣ ኬንያ እንዲሁም ቱርክ ይገኙበታል።
አንካራ ከሞቃዲሾም ሆነ ከአዲስ አበባ ጋር ጠንካራ የሆነ ምጣኔ ሃብታዊ ቁርኝነት እና ወታደራዊ ትብብሮች አሏት።
ኢትዮጵያ የባሕር በር ስምምነቱን ከሶማሊላንድ ጋር ከፈረመች ከአራት ሳምንታት በኋላ ቱርክ እና ሶማሊያ የመከላከያ እና የምጣኔ ሃብት ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።
የዚህ ስምምነት ሙሉ ዝርዝር ይፋ ባይደረግም በተለይ በመከላከያ ዘርፍ ቱርክ የሶማሊያን ባሕር ኃይል ለማጠናከር እና የአገሪቱን የባሕር ጠረፍ በጋራ ለመጠበቅ ከስምምነት መደረሱ ተነግሯል።
ስምምነቱን ተከትሎ ከጥቂት ወራት በፊት ዓይነቷ ያልተገለጸ የቱርክ ባሕር ኃይል የጦር መርከብ ሞቃዲሾ ወደብ ደርሳ ነበር።
ለመርከቧ ደማቅ አቀባበል በተደረገ ወቅት ፕሬዝዳንት ሐሰን ባደረጉት ንግግር፤ በቱርክ መንግሥት እና ሕዝብ ድጋፍ “ሶማሊያ የባሕር ግዛቷን በራሷ የባሕር ኃይል የምትቆጣጠርበት ጊዜ ሩቅ አይደለም” ብለዋል።
በተመሳሳይ ቱርክ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲሁ ወታደራዊ ስምምነት መፈረሟ ይታወሳል። ከሦስት ዓመታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ አንካራ ተጉዘው ዝርዝሩ ይፋ ያልሆነ የወታደራዊ እና የፋይናንስ ድጋፍ ትብብር ስምምነት ከፕሬዝዳንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን ጋር ተፈራርመዋል።
ከውይይቱ ምን ይጠበቃል?
የቀድሞ የሶማሊያ የነዳጅ እና ማዕድን ሃብት ሚኒስትር ሞሐመድ ሙክራታር ኢብራሂም ለቢቢሲ ሶማልኛ ሲናገሩ ምናልባት ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የደረሰችውን ስምምነት የምትሰርዝ ሆነ አዲስ አበባ እና ሞቃዲሾ በጋራ ተጠቃሚ በሚያደርጋቸው ጉዳዮች ድርድር ሊጀምሩ እንደሚችሉ ይገልጻሉ።
የቀድሞ ሚኒስትር ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ይልቅ የሶማሊያ ወደቦች ልትጠቀም የምትችልበት ስምምነት ሊኖር ይችላል።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም እንዲሁ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወደ አንካራ ማቅናታቸውን በገለጸበት ጽሑፉ ስለ ንግግሩ አጀንዳ በዝርዝር ያለው ነገር ባይኖርም “የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት የግዛት አንድነትን መጠበቅ መርሁ ላይ ቁርጠኛ ነው” ብሏል።
የቀድሞ የነዳጅ እና ማዕድን ሃብት ሚኒስትር ሃሳብን አስተያየትን የሚያጠናክር አስተያየት ከሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ ከጥቂት ቀናት በፊት ተስምቶ ነበር።
ፕሩዝዳንት ሐሰይ ሼክ ሞሐሙድ ሰኞ ሰኔ 17/2016 ዓ.ም. በሞቃዲሾ በተካሄደ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅብረሰብ ስብሰባ ላይ ንግግር ሲያደርጉ ኢትዮጵያ የሶማሊያን የባሕር በሮች እና ወደቦች መጠቀሟን አንቃወምም ብለዋል።
ይሁን እንጂ ፕሬዝዳንቱ ኢትዮጵያ የባሕር በር እንድትጠቀም የምንፈቅደው አዲስ አበባ “ትክክለኛውን ሂደት ስታከብር ነው” ብለዋል።
“ለሶማሊያ ሕዝብ ግልጽ ማድረግ የምፍገው፤ ኢትዮጵያ የሶማሊያን የባሕር በር መፈለጓን በአዎንታዊ እንመለከተዋለን። ነገር ግን ኢትዮጵያ የባሕር በራችንን እንድትጠቀም የምንፈቅደው ኡጋንዳ የኬንያን የባሕር በር እንዲሁም ቡሩንዲ እና ሩዋንዳ የታንዛኒያን የባሕር በር እንደሚጠቀሙት ነው።
“. . . ከዚያ ውጪ ግን በጭራሽ ተቀባይነት አይኖረውም” ሲሉ ፕሬዝዳንቱ በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ በተላለፈ ንግግራቸው ተናግራዋል።
በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ያለው ግንኙነት መሻከሩን ተከትሎ ሶማሊያ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት እና በተባበሩት መንግሥታት የከሰሰች ሲሆን፣ ከፍተኛ ባለሥልጣናቷም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ከሶማሊላንድ ጋር በደረሰችው ስምምነት ምክንያት ሲከሷት ቆይተዋል።
ከአንድ ሳምንት በፊት ደግሞ የኢትዮጵያ ወታደሮች ድንበሯን ጥሰው እንደገቡ በመግለጽ በመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ብትከስም፣ ኢትዮጵያ ግን ክሱም መሠረተ ቢስ ስትል ማጣጣሏ ይታወሳል።