ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አሜሪካ፡ የምትመሳሰላትን ሴት ማንነት ለመስረቅ የግድያ ሙከራ የፈጸመችው ግለሰብ ተፈረደባት
በአሜሪካ ኒውዮርክ ከተማ አንዲት ሩሲያዊት የምትመሳሰላትን ሴት ማንነት ለመስረቅ በሚል በፈጸመችው የመግደል ሙከራ የ21 ዓመታት እስር ተፈረደባት።
ቪክቶሪያ ናሲሮቫ የተባለችው ይህች ግለሰብ በውበት ሳሎን የምትሰራውን ባለሙያ የስራ ፈቃድና ፓስፖርቷን ከመስረቋም በፊት የተመረዘ የቺዝ ኬክ ሰጥታለች። ኦልጋ ቲስቪክ የተባለችው ግለሰብ የግድያ ሙከራም የተፈጸመባት በአውሮፓውያኑ 2016 ነው።
የእስር ቅጣት እንደሚበይንባት እጣ ፈንታዋን የተረዳችው የ47 አመቷ ቪክቶሪያ በኩዊንስ ግዛት በሚገኘው ፍርድ ቤትም ዳኛ ላይ ዘለፋ አቅርባለች።
አቃቤ ህጉም “ጨካኝና አጭበርባሪ” ሲሉም ጠርተዋታል።
“ለግል ጥቅም ስትል ግለሰቧን ለመግደል በመሞከሯ ለረጅም ጊዜም እስር ቤት ትቆያለች” ሲሉ የኩዊንስ አውራጃ አቃቤ ህግ ሜሊንዳ ካትዝ ረቡዕ እለት በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ቪክቶሪያ የግድያ ሙከራውን በፈጸመችበት በዚያች ዕለት ኩዊንስ ወደሚገኘው ኦልጋ ቺዝ ኬኮችን ኬክ ይዛ የሄደች ሲሆን ሁለት ኬክ ከበላች በኋላ ሶስተኛውንና የተመረዘውን ኬክ ለ35 ዓመቷ ተጎጂ መስጠቷንም ችሎቱ ሰምቷል።
ኦልጋም ኬኩን ከበላች በኋላም ማስመለስ እንደጀመረችና ልታርፍም ሌላ ክፍል ውስጥ ገባች። በመርዙም ምክንያት ቅዠት ያሰቃያት የነበረ ሲሆን በልብ ድካምም ልትጠቃ ተቃርባ ነበር ተብሏል።
በማግስቱም የኦልጋ ጓደኛ ራሷን ስታ ያገኛት ሲሆን በወቅቱም ከዳንቴል የተሰራ የውስጥ ልብስ ለብሳ እንደነበርና ህይወቷን ለማጥፋት እንደሞከረች የሚያስመስል እንክብሎች ወለሉ ላይ ተበታትነው ተገኝተዋል።
ከሆስፒታል ቆይታዋም ወደ ቤቷ ስትመለስ የዩክሬን ፓስፖርቷ፣ የአሜሪካ የስራ ፈቃድ እንዲሁም ጌጣጌጥ እና 4 ሺህ ዶላር ጠፍቷት አገኘች።
በወቅቱ ኦልጋና ቪክቶሪያ ጥቁር ጸጉር፣ ተመሳሳይ የቆዳ ቀለም ስለነበራቸው ከመመሳሰል በተጨማሪም ሁለቱም የሩሲያ ቋንቋ የሆነው ሩስኪ ተናጋሪዎች ናቸው ተብሏል።