መንግሥት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ሰላማዊ ተቃውሞ ለማፈን እየተጠቀመበት ነው ሲል አምነስቲ ከሰሰ

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት “ሰላማዊ የተቃውሞን” ለማፈን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እየተጠቀሙበት ነው ሲል ዓለም አቀፉ የመብቶች ተሟጋቹ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ገለጸ።

አምነስቲ ዛሬ የካቲት 11/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ “የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት መንግሥትን የሚተቹ ታዋቂ ፖለቲከኞችን እና ጋዜጠኞችን በዘፈቀደ በማሰር ሰላማዊ ተቃውሞን ለማፈን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተጠቅመዋል” ሲል ከሷል።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ጨምሮም የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተጠርጣሪዎችን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የማሰር፣ የሰዓት እላፊ ገደቦችን የመጣል፣ የመንቀሳቀስ መብትን የመገደብ እና ሕዝባዊ ስብሰባዎችን የማገድ ሥልጣንን ለመንገሥት ሰጥቷል ብሏል።

የአምነስቲ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ እና ደቡብ አፍሪካ ቀጠናዊ ዳይሬክተር ቲጌሬ ቻጉታህ “የኢትዮጵያ መንግሥት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጆች ሰበብ የቀድሞውን መሠረታዊ መብቶችን የመንፈግ ስልት መጠቀሙን ማቆም አለበት” ብለዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በመላው ኢትዮጵያ እና በተወሰኑ ክልሎች ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገጉ የሚታወስ ሲሆን፣ ካለፈው ዓመት ማብቂያ አንስቶ በአማራ ክልል እና እንደ አስፈላጊነቱ በማለው ኢትዮጵያ ተግባራዊ የሚሆን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተጥሎ ቆይቷል።

በአማራ ክልል ውስጥ የተከሰተውን አለመረጋጋት ተከትሎ ለስድስት ወራት ተብሎ የተደነገገው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ከማብቃቱ በፊት ባለፈው ወር ለተጨማሪ አራት ወራት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲራዘም ተደርጓል።

ዋና ዳይሬክተሩ ቲጌሬ ቻጉታህ አክለውም “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መራዘም እስካሁን በአገሪቱ ነጋሪት ጋዜጣ አልታተመም። ይህ ግልጽነት የጎደለው አሠራር ኢትዮጵያውያን ተግባራቸው የሕግ ጥሰት ስለመሆኑ ወይም ሕጉ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ መሆኑን ማወቅ ባለመቻላቸው መረጃ የማግኘት መብትን እና የሕግ መርህን የሚጻረር ነው” ብለዋል።

አምነስቲ በመግለጫው አምስት ፖለቲከኞች እና ሦስት ጋዜጠኞች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት ያለ ክስ ታስረዋል ብሏል። ድርጅቱ ታስረዋል ካላቸው ፖለቲከኞች መካካል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ሲታወጅ ከመኖሪያ ቤታቸው የተያዙት የፓርላማ አባሉ አቶ ክርስቲያን ታደለ እና አዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አባሉ ዶ/ር ካሳ ተሻገር ይገኙበታል።

የአማራ ክልል ምክር ቤት አባሉ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ደግሞ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ አስር ቀናት በኋላ ነሐሴ መጀመሪያ ላይ በባሕር ዳር መታሰራቸውን ጠቅሷል።

ከሁለት ወር በፊት ከሥልጣን ተነስተው በቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደኣ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩን “በሰው ደም የሚጫወቱ አረመኔ” ካሏቸው በኋላ መታሰራቸውንም አምንስቲ ጠቅሷል።

አቶ ታዬ አባል የሆኑበት ኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ከትላንት እሁድ ጀምሮ ሲያካሂደው በነበረው ጉባኤ የአቶ ታዬን ያለመከሰስ መብት አንስቷል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ባለፈው ጥር ወር መጨረሻ በተራዘመበት ወቅትም በተወካዮች ምክር ቤት የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ተወካዮ ዶ/ር ደሳለኝ ጫኔ መታሰራቸውን አምነስቲ አክሏል።

ከአምስቱ ፖለቲከኞች በተጨማሪም የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያ የሆኑት በቃሉ አላምረው፣ አባይ ዘውዱ እና በላይ ማናየ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መደንገግ በኋላ መታሰራቸው በአምነስቲ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ ወር ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከታወጀ ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል የጅምላ እስሮች መበራከታቸውን አምነስቲ አመልክቶ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባለፈው ሰኔ 30 ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት በሺዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታሰራቸውን እና “ሥልጠና” ከወሰዱ በኋላ ስለመለቀቃቸው መናገራቸው ይታወሳል።

አምነስቲ በዛሬው መግለጫ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ሆነ ከእሳቸው በፊት የነበረው አገዛዝ የአስቸኳይ ጊዜ ሁኔታዎችን መጠቀም ሰላማዊ ተቃውሞን ለማፈን ሲጠቀሙ ቆይተዋል በማለት መንግሥት ይህንን ድርጊት እንዲያቆም ጠይቋል።