'አርግዤልሃልሁ' በሚል ማስፈራሪያ ከቀድሞው የቶተነሃም ተጨዋች ገንዘብ የወሰደችው ሴት ተፈረደባት

የእግር ኳሱን ኮከብ ሶን ሄንግ ሚን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሶን ሄንግ ሚን በእስያ ካሉ የእግር ኳስ ኮከቦች አንዱ ሲሆን በአገሩ እና በቀጠናው ተወዳጅነትን አትርፏል።

የደቡብ ኮሪያ ፍርድ ቤት የእግር ኳሱን ኮከብ ሶን ሄንግ ሚንን ያስፈራራችው ሴት ላይ የአራት ዓመታት እስር በየነ።

በ20ዎቹ የእድሜ ክልል የምትገኘው ሴት የቀድሞውን የቶተነሃም አምበል 'አርግዣለሁ' በማለት ገንዘብ እንዲሰጣት በማስፈራራት ወንጀል ጥፋተኛ ሆና በመገኘቷ ነው ፍርዱ የተላለፈባት።

በድርጊቱ ተባባሪ በነበረው የ40 ዓመቱ ግለሰብ ላይም ፍርድ ቤቱ የእስር ፍርድ አስተላልፏል።

ወጣቷ 'የሶንን ልጅ በማሕጸኔ ተሸክሜያለሁ' በማለት ባለፈው ዓመት ተጨዋቹን አግኝታው እንደነበር የሴኡል ዲስትሪክት ፍርድ ቤት መስማቱን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ከዚያም 200 ሺህ ዶላር ገንዘብ እንዲሰጣት እንደጠየቀች እና ይህንን ካላደረገ ጉዳዩን ወደ አደባባይ እንደምታወጣው በማስፈራራት ገንዘብ ተቀብላለች።

ሴትዮዋ ገንዘቡን ቅንጡ ለሆኑ እና ውድ ለሆኑ ቁሳቁሶች ማዋሏን ኤኤፍፒ የዜና ወኪል ዘግቧል።

" ሴትዮዋ ገንዘቡን እንደ ካሳ ተቀብላለች፤ ራሷን ተጎጂ አድርጋ አቅርባለች" ሲሉ አቃቤያነ ሕግ ሰኞ ዕለት ለፍርድ ቤት አስረድተዋል። ሆኖም ያቀረበችው ቅሬታ "ከእውነታው ጋር ሙሉ በሙሉ የተገናኘ አይደለም" በማለት ግለሰቧ ወንጀሉን በማቀነባበር ከሰዋታል።

ገንዘቡን ለማግኘት ሶንን 15 ጊዜ ያስፈራራው የግለሰቧ ተባባሪም የሁለት ዓመት እስር ተበይኖበታል።

ሶን ወደ ፖሊስ ያመራው በዚህ ዓመት ተጨማሪ ገንዘብ መጠየቃቸው ተከትሎ ነበር።

ዳኛው እንዳሉት ግለሰቧ እና ተባባሪዋ ላቀነባበሩት ወንጀል ሲሉ የሶን ዝና ላይ ጥላሸት የቀቡ ሲሆን ጉዳዩ ወደ መገናኛ ብዙኃን ከወጣ በኋላ ሶን ከባድ በሆነ "የአዕምሮ ስቃይ" ውስጥ አልፏል።

ሶን ኅዳር ወር ላይ ከእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ጋር በሚስተካከለው የሰሜን አሜሪካ የእግር ኳስ ሊግ - ሜጀር ሊግ ሶክሰር (ኤምኤልኤስ) ውስጥ ሁለተኛው ከፍተኛ ተከፋይ የእግር ኳስ ተጨዋች ተብሎ ተመርጧል።

የ33 ዓመቱ የቀድሞው የቶተነሃም ተጨዋች ከአስር ዓመት አገልግሎት በኋላ ነሐሴ ላይ የሎስ አንጀለስ የእግር ኳስ ክለብን ተቀላቅሏል። በዚህም በኤምኤልኤስ ታሪክ ውዱን ዝውውር አሳይቷል።

ሶን በእስያ ውስጥ ምርጥ እግር ኳስ ተጨዋች እንደሆነ በስፋት ቢታወቅም በአገሩ እና በቀጠናው እጅግ ዝነኛ ነው።

ከሦስት ዓመታት በፊት ስፐርስ ውስጥ እያለ በየዓመቱ በሚዘጋጀው ሽልማት በሊጉ ውስጥ ጎል በማስቆጠር የፕሪሚየር ሊግ የወርቅ ጫማ ሽልማት በማግኘት ከአህጉሩ የመጀመሪያው ለመሆንም በቅቷል።