ቢቢሲ የኬንያ መንግስት "ሐሰት" ሲል ያጣጣለውን የህጻናት የወሲብ ንግድ የተመለከተ የምርመራ ዘገባ ተከላከለ

የኬንያ መንግስት ቢቢሲ በሀገሪቱ ውስጥ የሚፈጸምን የህጻናት ወሲባዊ ብዝበዛ በተመለከተ ያስተላለፈውን የምርመራ ዘገባ "ሐሰት" ነው ማለቱን ተከትሎ ተቋሙ ምላሽ ሰጠ።
የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ኪፕቹምባ ሙርኮሜን ረቡዕ በፓርላማው ተገኝነተው ባደረጉት ንግግር፤ በዘጋቢ ፊልሙ ላይ "ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሰዎች ዕድሜያቸው ያልደረሰ ስላልሆኑ ሐሰት ነው" ብለዋል።
አክለውም፤ በቢቢሲ አፍሪካ አይ (BBC Africa Eye) ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ተጐጂዎች "ህፃናት መስለው ቀርበዋል" ሲሉ ተናግረዋል።
ቢቢሲ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ፤ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሴቶች አዋቂዎች እንደሆኑ ነገር ግን "እድሜያቸውን ሳይደርስ በፊት የደረሰባቸውን በደል" እንደሚናገሩ ዘጋቢ ፊልሙ በግልጽ ያሳያል ሲል ተከላክሏል።
የአፍሪካ አይ ምርመራ "የሕዝብ ጥቅም የሚያስጠብቅ ጋዜጠኝነት ወሳኝ አካል ነው" ሲል አክሏል።
ሚኒስትሩ ሙርኮሜን፤ ቢቢሲ በዶክመንተሪው ላይ ለተሳተፉት ሰዎች "የገንዘብ ሽልማት" እንደሚሰጥ ቃል ገብቷል በማለት ተጨማሪ ክስ ውንጀላ አቅርበዋል።
ቢቢሲ ለዚህ በሰጠው ምላሽ፤ ተጎጂዎቹ ታሪኮቻቸውን እንዲናገሩ ምንም አይነት የገንዘብ ማበረታቻ እንዳልተሰጣቸው በአጽንኦት አንስቷል።
"ግልጽ ለማድረግ፤ በዚህ ፊልም ውስጥ የተካተቱት የትኛዎቹም ተሳታፊዎች አልተከፈላቸውም፣ ክፍያ አልቀረበላቸውም ወይም በምንም መንገድ 'ስልጠና' አልተሰጣቸውም" ብሏል።
በተጨማሪም መግለጫው፤ ቢቢሲ በምርመራውን ያገኛቸውን ማስረጃዎች መጋቢት ላይ ለኬንያ ፖሊስ አሳልፎ እንደሰጠ አክሏል።
ቢቢሲ፤ ለአደጋ የተጋለጡ ህፃናት እንዲጠበቁ በበርካታ አጋጣሚዎች ክትትል ማድረጉንም አስታውሷል። በምርመራው የተደረሰባቸው ሁለት ህጻናትን ለወሲብ ንግድ የሚያቀርቡ ሴቶችን የሚያሳዩ ምስሎችን ባለስልጣናት ሚያዝያ ላይ እንዲመለከቱ መደረጉንም ገልጿል።
በወቅቱ በተለይም ህጻናቱን ለመታደግ ፖሊስ እርምጃ እንደሚወስድ ተገልጾለት እንደነበረም ቢቢሲ አስረድቷል።
የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሙርኮሜን በፓርላማው ባደረጉት ንግግር፤ የኬንያ መንግሥት ህፃናትን በመጠበቅ ረገድ ያስመዘገበውን ሪከርድ በመጥቀስ የሀገሪቱ መንግሥት እድሜያቸው ያልደረሰ ህፃናትን ማዘዋወርን የተመለከቱ ጉዳዮችን "በከፍተኛ ደረጃ" እንደሚመለከት ገልጸዋል።
የቢቢሲ ዶክመንተሩ ከሀገሪቱ ብሔራዊ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሞሰስ ዌታንጉላም ትችት ተሰንዝሮበተቃል። አፈ ጉባኤው የዶክመንተሪው ዓላማ ኬንያን "ማጥላላት" መሆኑን በመግለጽ ተችተዋል።
ባለፈው ሳምንት ወጥቶ ዩቲዩብ ላይ ከአንድ ሚሊዮን በላይ እይታን ያገኘው የቢቢሲ የምርመራ ዘገባ፤ በኬንያዋ ማይ ማሂዩ ከተማ ውስጥ እድሜያቸውን እስከ 13 ዓመት የሆኑ ህጻናት እንዴት ለወሲብ ንግድ እንደሚቀርቡ ያሳየ ነበር።
በዘገባው ላይ ሁለት የተለያዩ ሴቶች የሚያከናውኑት ተግባር ህገወጥ እንደሆነ እያወቁ እንኳ እድሜያቸው ያልደረሰ ህጻናትን ለወሲብ እንደሚያቀርቡ ሲያምኑ ይታያል።
የቢቢሲ ድብቅ ቀረጻ ራሷን ኛምቡራ ብላ የምትጠራው አንዲት ሴት እየሳቀች "አሁንም ልጆች ናቸው፤ ጣፋጭ እየሰጡ እነሱን ማታለል ቀላል ነው" በማለት ስትናገር አሳይቷል።
"ማይ ማሂዩ ውስጥ የወሲብ ንግድ ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ ነው። በመሰረቱ የሚያቀጣጥሉት የጭነት መኪና አሽከርካሪዎች ናቸው። እኛም የምንጠቀመው በዚህ መንገድ ነው። በማይ ማሂዩ ውስጥ የተለመደ" ስትል ትደመጣለች። በእርሷ ስር ለስድስት ወራት "የሰራች" የ13 ዓመት ልጅ እንዳለች ስትናገር ዘገባው አሳይቷል።
ዘጋቢ ፊልሙ በህፃናት ላይ ይህንን ወንጀል የሚፈጽሙ ግለሰቦችን እንዲሁም አስቸኳይ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ተጎጂዎችን ለይቶ አቅርቧል።
ዘጋቢ ፊልሙን መውጣቱን ተከትሎ የጠቅላይ አቃቤ ህግ ዳይሬክተር ጽሕፈት ቤት ጉዳዩ ምርመራ እንዲደረግበት ለወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ቢቢሲ ባወጣው መግለጫ፤ በዘጋቢ ፊልሙ ላይ ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው የጉዳት ሰለባዎች የህግ ወኪል ሳይቆምላቸው የኬንያ የወንጀል ምርመራ ዳይሬክቶሬት መርማሪዎች ረጅም ቃለ መጠይቅ እንደተደረገላቸው በመጥቀስ ስጋቱን ገልጿል።
ቢቢሲ፤ ቃለ መጠይቅ ከተደረገላቸው ተጎጂዎች መካከል አንዳቸውም በድብቅ ምርመራው ውስጥ እንዳልተሳተፉ አረጋግጧል።
በምርመራ ዘገባው ላይ ህጻናትን ለወሲብ ንግድ እንደሚያቀርቡ የተጋለጡት ሁለቱ ሴቶች እስካሁን በቁጥጥር ስር አልዋሉም። የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚስትሩ ሙርኮሜን ሁለቱ ሴቶች እንዳልተገኙ ተናግረዋል።















