ተገድዳ ወይስ "ተስማምታ"? - በጋምቤላ የ13 ዓመት ልጅ ላይ ለተፈጸመው ጥቃት የተሰጠው ፍርድ

እጇን ያጣመረች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በጋምቤላ ክልል ቀጥሮ ሲያሠራት በነበረች የ13 ዓመት ልጅ ላይ "የግብረ ሥጋ ድፍረት በደል" የፈጸመ ግለሰብ የሦስት ዓመት ከ11 ወር እስር ተፈረደበት።

ተበዳይ፤ "እንደተደፈረች" ለፖሊስ እና ለፍርድ ቤት የገለጸች ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ መረጃዎች የሚያመለክቱት "ዕድሜዋ ካልደረሰ ልጅ ጋር"፤ "በፍላጎት" ግንኙነት እንደተፈጸመ መሆኑን ተናግሯል።

በጋምቤላ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሲታይ የነበረው ይህ የክስ መዝገብ ውሳኔ የተሰጠበት ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሐምሌ 8/2017 ዓ.ም. ነው።

የ13 ዓመቷ ተበዳይ ወደ ፖሊስ ጣቢያ በሄደችበት ወቅት ሁለት ጊዜ "አስገድዶ መድፈር" እንደተፈጸመባት እንደገለጸች የጋምቤላ ክልል ፖሊስ የሴቶች እና ሕፃናት ጥቃት ምርመራ ኦፊሰር የሆኑት ምክትል ሳጅን ሳሙኤል አስፋው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ፍርድ ቤት ቀርባ ምስክርነቷን ስትሰጥም ይህንኑ እንደተናገረች ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሁለት የጋምቤላ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች አስረድተዋል።

ጉዳዩን የያዘው ዐቃቤ ሕግ በአንጻሩ ክሱን ለፍርድ ቤት ያቀረበው "በአስገድዶ መድፈር" ሳይሆን "በግብረ ሥጋ ድፍረት በደል" ወንጀል ነው። ዐቃቤ ሕግ ክሱን በዚህ መልኩ ያቀረበው ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር "በመሆን የሕግ reasoning" በመጠቀም ጉዳዩን ከተመለከተ በኋላ እንደሆነ ገልጿል።

ዐቃቤ ሕግ በዋነኛነት ያነሳው መከራከሪያ፤ ተበዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ድርጊቱ ከተፈጸመባት በኋላ ወደ ሕግ አልመጣችም የሚል ነው። ዐቃቤ ሕግ "ይህንን ድርጊት ሁለት እና ከዚያ ጊዜ በላይ መፈጸማቸው [የሚያመለክተው] በመሃላቸው የሆነ agreement [ስምምነት] አለ" ብሏል።

ዐቃቤ ሕጉ፤ ይህ ድርጊት ሁለት ጊዜ መፈጸሙ "already ተላምደዋል" የሚለውን እንደሚያመለክት እና በመካከላቸው "ስምምነት [acceptance]" እንዳለ እንደሚያሳይ ተናግሯል።

"በ72 ሰዓት ውስጥ የሕክምና ምርመራ አለመደረጉ" እና ተበዳይ "የልደት ምስክር ወረቀት ማቅረብ አለመቻሏም" ዐቃቤ ሕግ ክሱን በዚህ መልኩ ለማቅረቡ በምክንያትነት የጠቀሳቸው ጉዳዮች ናቸው።

ቢቢሲ ያነገጋራቸው የሕግ ባለሙያዎች ግን እነዚህ ጉዳዮች ክሱን "ከአስገድዶ መድፈር" ወደ "ግብረ ሥጋ ድፍረት ወንጀል" አውርዶ ለማቅረብ ተገቢ ምክንያት የመሆናቸው ጉዳይ ላይ ጥያቄ አንስተዋል።

ፊት ለመከለል የተዘረጋ እጅ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የተፈጠረው ምንድነው?

የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ የሆነው ግለሰብ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው የካቲት 12 እና የካቲት 22/2017 ዓ.ም. እንደሆነ በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የሴቶች እና ሕፃናት ጥቃት ምርመራ ኦፊሰሩ ምክትል ሳጅን ሳሙኤል ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ምክትል ሳጅን ሳሙኤል እንደሚያስረዱት፤ የ13 ዓመት ልጅ የሆነችው ተበዳይ የግለሰቡን እና የባለቤቱን መንታ ሕጻን ልጆች ለመንከባከብ በአንድ ሺህ ብር ደመወዝ ተቀጥራ ስትሠራ ነበር።

በግለሰቡ ቤት በሠራተኝነት የተቀጠረችው ጥር ወር እንደሆነ የሚገልጹት ኦፊሰሩ፤ የመጀመሪያው "የአስገድዶ መድፈር ጥቃት የደረሰባት የካቲት 12 ቀን" እንደሆነ ልጅቷ የሰጠችው መረጃ እንደሚያመለክት አንስተዋል።

"በዚያ ሰዓት ወደ ፖሊስም አልመጣችም፤ ጉዳዩን እዚያው ይዛው ነው የተቀመጠችው። በድጋሚ [የካቲት] በቀን 22 አሁንም ተጨማሪ ጥቃት አድርሶባታል" በማለት አስረድተዋል።

የመጀመሪያው ጥቃት ሲፈጸም የግለሰቡ ባለቤት "ውሃ ለመቅዳት" ወጥታ እንደነበር ተበዳይ መናገሯን የሚገልጹት ምክትል ሳጅን ሳሙኤል፤ "ሁለተኛው፣ በቀን 22 የተፈጸመው፤ ልጆች ታመው [ባለቤቱ] ሆስፒታል አስተኝታ ስለነበር ለልጆቹ ሙቅ እንድታሞቅ ወደ ቤት እንድትሄድ ከተደረገ በኋላ ነው" ብለዋል።

እንደ ምክትል ሳጅን ሳሙኤል ገለጻ፤ ልጅቷ የመጨረሻው ጥቃት ከተፈጸመ ሁለት ቀናት በኋላ ቤቱን ለቅቃ የወጣች ሲሆን፣ ከእህቷ ጋር ወደ ቤቱ በመመለስም ደመወዝ እንዲከፈላት ጠይቃለች።

ግለሰቡ ግን "እቃ ሰብራለች" በሚል ከልጅቷ ደመወዝ ላይ 400 ብር መቁረጡን የሚናገሩት ኦፊሰሩ፤ ተበዳይ እና እህቷ ወደ ፖሊስ ጣቢያ የመጡት ይህንን ሊያመለክቱ እንደነበር አስረድተዋል።

ምክትል ሳጅን ሳሙኤል

የፎቶው ባለመብት, Gambella Police Commission

ወደ ፖሊስ ጣቢያ ከመጡ በኋላ ግን በልጅቷ ላይ የደረሰው ጥቃትም መነሳቱን አክለዋል። የአስገድዶ መድፈሩ ወንጀሉ መፈጸም አለመፈጸሙን ለማረጋገጥ ወደ ሆስፒታል እንደተላከች ጠቅሰዋል።

ምክትል ሳጅን ሳሙኤል፤ "[የሕክምና ምርመራው የተደረገው] በወቅቱ ቢሆን ኖሮ መደፈርን [የሚያመለክት] መድማት፣ የተለያየ ነገር ይኖረዋል። ወደ ሕክምና የሄደችው ጉዳዩ ከተፈጸመው 12፣ 14 ቀን በኋላ ነው። ስለዚህ ያንን የሕክምና ማስረጃው በትክክል ጥቃት መድረሱን፣ መድፈር መደረጉን የሚገልጽ የሕክምና ማስረጃ መጥቷል" በማለት የተገኘውን ውጤት አስረድተዋል።

ፖሊስ ይህንን የሕክምና ማስረጃ እንዲሁም የተበዳይ እና እህቷን ቃል በማደራጀት መዝገቡን መጋቢት 24 ቀን ወደ ዐቃቤ ሕግ መምራቱን ገልጸዋል። "ሰነዱን አደራጅቶ መምራት እንጂ ውሳኔ አሰጣጡ ላይ የእኛ [ሥልጣን] አይደለም" የሚሉት ምክትል ሳጅን ሳሙኤል፤ ክሱን የተመሠረተው እና የተመራው በዐቃቤ ሕግ እንደሆነ አስረድተዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ ጥያቄ ያስነሳው ሌላኛው ጉዳይ ድርጊቱን የፈጸመው ግለሰብ ካደረሰው ጥቃት በተጨማሪ የ13 ዓመቷን ልጅ በሠራተኝነት ቀጥሮ ማሠራቱን በተመለከተ ክስ አለመቅረቡ ነው።

ምክትል ሳጅን ሳሙኤል፤ ይሄ ድርጊት በራሱ "ሌላ የወንጀል ጉዳይ" መሆኑን ቢጠቅሱም ፖሊስ የምርመራ መዝገቡን ያደራጀው ከአስገድዶ መድፈር ጋር በተያያዘ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

ጉዳዩ የተመራለት ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ፤ "መዝገቡ በዚያ አግባብ ተደራጅቶ አልመጣልንም" ብሏል።

የዐቃቤ ሕግ 'አመክንዮዎች'

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጉዳዩን የያዘው የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ዐቃቤ ሕግ፤ ክሱ የተመሠረተው "በአስገድዶ መድፈር የወንጀል ድርጊት ሳይሆን ዕድሜዋ ካልደረሰች ልጅ" ጋር ግንኙነት በመፈጸም ወንጀል እንደሆነ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በ1996 ዓ.ም. የወጣው የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ፤ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ የመድፈር ወንጀሎችን ያስቀመጣቸው ለያይቶ ነው። ከእነዚህ ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው "አስገድዶ መድፈር" ነው።

በሕጉ መሠረት "አስገድዶ መድፈር" ወንጀል "የኃይል ድርጊትን በመጠቀም ወይም በብርቱ ዛቻ" እና ሌሎች መንገዶች "አስገድዶ ከአንዲት ሴት ጋር ግብረ ሥጋ ግንኙነት" መፈጸምን የሚመለከት ነው።

ይህ ወንጀል "ዕድሜዋ 13 ዓመት ሆኖ 18 ዓመት ባልሞላት ሴት ልጅ ላይ" ሲፈጸም የሚጣለው ቅጣት ከአምስት እስከ 20 ዓመት ይደርሳል።

ጋምቤላ ከተማ የተፈጸመው ወንጀል የታየው ደግሞ "የግብረ ሥጋ ድፍረት በደል" በሚል በሕጉ ላይ በተቀመጠው አንቀጽ ነው። ይህ የወንጀል ዓይነት ዕድሜያቸው "13 በሆነ እና 18 ዓመት ባልሞላቸው ልጆች ላይ" የሚፈጸም ነው።

ይህንን የወንጀል ዓይነት "ከአስገድዶ መድፈር" የሚለየው፤ በዚህ አንቀጽ የሚፈጸመው ወንጀል በውስጡ "ማስገደድ" ስለሌለው ነው። አንድ ሰው "በግብረ ሥጋ ድፍረት በደል" ሲከሰስ የሚጠየቀው፤ ዕድሜዋ 18 ዓመት ካልሞላት ልጅ ጋር ወሲባዊ ግንኙነት በመፈጸሙ ነው።

የጋምቤላ ፖሊስ ኮሚሽን የ13 ዓመቷን ልጅ በተመለከተ ያዘጋጀው መዝገብ ወደ ዐቃቤ ሕግ የመራው ተበዳይ "አስገድዶ መድፈር" እንደተፈጸመባት በመግለጽ እንደሆነ ምክትል ሳጅን ሳሙኤል ገልጸዋል።

ይህንን መዝገብ የተቀበለው ዐቃቤ ሕግም በተመሳሳይ፤ "መጀመሪያ [የካቲት] በቀን 12 እንደዚህ ፈጽሞብኛል" ብላ መናገሯን አረጋግጧል።

እንደ ዐቃቤ ሕጉ ገለጻ፤ የፖሊስ የምርመራ መዝገብ ወደ ፍትሕ መምሪያ ከተላከ በኋላ በጉዳዩ ላይ ውይይት ተደርጓል።

ዐቃቤ ሕጉ፤ "መዝገቡን ስናየው፤ 'እቺ ልጅ ይሄ ድርጊት ያለ ፍላጎቷ ከተፈጸመ ለምን [የካቲት] በቀን 13 እና 14 መክሰስ አልቻለችም' በሚል፤ ራሱን የቻለ ቡድን አለን ውይይት አደረግንበት" ሲል ለቢቢሲ አስረድቷል።

ፊት ለመከለል የተዘረጋ እጅ

የፎቶው ባለመብት, GAN CHAONAN

ክሱ፤ "በአስገድዶ መድፈር" ወንጀል ሊመሠረት የሚችለው "አንዲትን ሴት ላይ የኃይል ድርጊት በመጠቀም" ግብረ ሥጋ ግንኙነት ሲፈጸም እንደሆነ አብራርቷል።

ይህንን ጉዳይ የያዘው ዐቃቤ ሕግ፤ "አንደኛ የቀን ልዩነቱ፤ 10 ቀን ሙሉ እዚህ ከተማ ውስጥ ነው ያለችው። ይሄ ድርጊት ያለ ፍላጎቷ የተፈጸመ ቢሆን ኖሮ 10 ቀን መጠበቅ ለምን አስፈለገ?" በማለት ጠይቋል።

ቢቢሲ፤ የመደፈር ወንጀል ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ከአጥቂያቸውም ሆነ ከማኅበረሰቡ በሚደርስባቸው ጫና እና ማስፈራሪያ ምክንያት የተፈጸመባቸውን ድርጊት ወደ አደባባይ ማውጣት እንደሚፈሩ በመጥቀስ፤ "ምክንያቱ ይህ ሊሆን አይችልም ወይ?" የሚል ጥያቄ ለዐቃቤ ሕጉ አቅርቧል።

ዐቃቤ ሕጉ፤ "[ፈርታ ነው] እንዳንል ያደረገን ነገር ምንድነው? ልጅቱ ከታላቅ እህቷ ጋር ሁሌ communicate ያደርጋሉ። አሁን ፍራቻ ነው የሚለው ነገር ቢሆን ኖሮ ደመወዝ ሲቆረጥባት ነው ይህንን ጉዳይ እንደ ሌላ እንትን ያነሳችው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በዐቃቤ ሕግ መከራከሪያ መሠረት፤ የ13 ዓመቷ ልጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ድርጊቱ ሲፈጸምባት ወደ ሕግ አለመምጣቷ የሚያመለክተው "ስምምነት መኖሩን" ነው። ዐቃቤ ሕጉ፤ ድርጊቱ በድጋሚ መፈጸሙ "መላመድን" እና ጉዳዩን "መቀበልን" እንደሚያሳይ የሚያስረዳ መከራከሪያም አቅርቧል።

በተጨማሪም ተበዳይ እንደ የልደት የምስክር ወረቀት ያሉ ማስረጃዎችን ማቅረብ እንዳልቻለች ጠቅሷል። ድርጊቱ በተፈጸመ በ72 ሰዓት ውስጥ የሕክምና ምርመራ ቢደረግ ኖሮ ሊገኙ ይችሉ የነበሩ "መቦጫጨር፣ የሰውየው ፀጉር" የመሳሰሉ ማስረጃዎች እንዳልተሟሉም አክሏል።

"72 ሰዓት ከሞላው በኋላ እንደዚህ ዓይነት ኬዝ ውድቅ ነው። ከ72 ሰዓት በኋላ የሕክምና ማስረጃው ውድቅ ያደርገዋል" ብሏል። ዐቃቤ ሕግ፤ "የልደት ሰርተፊኬት በሌለበት፣ የሕክምና ምርመራ በ72 ሰዓት ባልተደረገበት። ልጅቱ alredy ፍላጎቷን ነው የሚያሳየው" በማለት ተናግሯል።

ክሱ፤ "የግብረ ሥጋ ድፍረት በደል" ወንጀልን በሚመለከተው አንቀጽ እንዲቀርብ የተደረገው፤ የልጅቷ ዕድሜ በዚህ አንቀጽ ላይ የተጠቀሰውን "13 በሆነ እና 18 ዓመት ባልሞላቸው ልጆች" የሚለውን መስፈርት ስለሚያሟላ እንደሆነም ተጠቅሷል።

ይሁን እንጂ በወንጀል ሕጉ ላይ የተቀመጠው "አስገድዶ መድፈር" የሚለው አንቀጽም በዚህ ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆችን እንደሚመለከት ሰፍሯል።

ቢቢሲ፤ የክስ ሂደቱ የተመራበትን መንገድ በተመለከተ ከጋምቤላ ክልል ፍትሕ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዶል ኡኩሪ ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ህጻን ልጅ ከመስታወት ጀርባ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የክስ ሂደት

ቢቢሲ፤ የዚህን ክስ መዝገቦች ከጋምቤላ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እና ከክልሉ ፍትሕ ቢሮ ለማግኘት ያደረጋቸው ጥረቶች አልተሳኩም። ጉዳዩን የተመለከቱት ዳኛ ኒቴንዶ ኦፒዶ እና የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ዶማች ኮክ ግን ስለ ክሱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ተበዳይ ዕድሜዋ 13 ዓመት በመሆኑ ጉዳዩ የታየው በሕጻናት ልዩ ችሎት እንደሆነ ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ ዶማች አስረድተዋል።

በዚህም ምክንያት ልጅቷ እንደ አዋቂ ሰው ችሎት ቀርባ ምስክርነት አለመስጠቷን የሚናገሩት አቶ ዶማች፤ "ልዩ ችሎት ሆኖ ሴት ዳኞች ስላሉ፤ የልጅቷን ቃል በአስረጂነት የተቀበሉት ሴት ዳኞች ናቸው" ብለዋል።

በዚህ ጊዜ ቃሏን ስትሰጥ "አስገድዶ መድፈር" እንደተፈጸመባት መናገሯን ገልጸዋል። የፍርድ ሂደቱን የመሩት ዳኛ ኒቴንዶም ይህንን አረጋግጠዋል።

ዳኛዋ እና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንቱ፤ ክስን የማዘጋጀት እና ክስ የሚቀርብበትን አንቀጽ የመወሰን ሥልጣን የዐቃቤ ሕግ መሆኑን አስረድተዋል። ፍርድ ቤት ጉዳዩን የሚመለከተው ዐቃቤ ሕግ ባቀረበለት የክስ መዝገብ መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

ዳኛ ኒቴንዶ በበኩላቸው፤ ፍርድ ቤት ክሱ እንዲሻሻል ሊጠይቅ የሚችለው ተከሳሹ ላይ የቀረበውን ውንጀላ የማያከብድ ሲሆን እንደሆነ ተናግረዋል።

ዳኛዋ የጠቀሱት ይህ አሠራር በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ላይም ተመላክቷል። ሕጉ፤ ፍርድ ቤት ክሱ "እንዲለወጥ"፣ "እንዲጨመር" ወይም "እንደ አዲስ እንዲዘጋጅ" ትዕዛዝ መስጠት የሚችለው፤ የቀረበው ክስ "ተከሳሹን የሚያሳስት ወይም ያሳተ በመሰለ ጊዜ" እንደሆነ ደንግጓል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሦስት የሕግ ባለሙያዎች እንደሚያስረዱት፤ በዚህ ሕግ ትርጓሜ መሠረት ዳኞች ክሱ እንዲሻሻል ትዕዛዝ መስጠት የሚችሉት ደረጃው ዝቅ ወደ አለ አንቀጽ ነው። ይህ አሠራር ዳኞች፤ ተከሳሽ ላይ የቀረበው ክስ ከፍ ብሎ እንዲሻሻል የማዘዝ ሥልጣን እንዳይኖራቸው እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

የፍርድ ቤት መዶሻ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የ13 ዓመቷን ልጅ በተመለከተ የቀረበውን ክስ የተመለከቱት ዳኛ ኒቴንዶ፤ ዐቃቤ ሕግ ባቀረበው የወንጀል ሕግ አንቀጽ እና የቅጣት እርከን መሠረት ከፍተኛ የሆነውን ቅጣት መወሰናቸውን ተናግረዋል።

በወንጀል ሕጉ መሠረት ዐቃቤ ሕግ ክስ ያቀረበበት አንቀጽ ከሦስት እስከ 15 ዓመት ጽኑ እስራት የሚያስቀጣ ነው። ነገር ግን ዳኞች በአንቀጹ ላይ የተጠቀሰውን የእስር ዓመት እንዲሁ አይወስኑም።

አንድ ወንጀል ምን ደረጃ ላይ ሲሆን ዝቅተኛ ወይም ከፍተኛ ቅጣት ያስወስናል የሚለውን በደረጃ ከፋፍሎ ያስቀመጠው 'የወንጀል ቅጣት አወሳሰን መመሪያ' የተባለው ሕግ ነው።

ዐቃቤ ሕግ የቅጣት አስተያየቱን ሲያቀርብ በደረጃ ሁለት እርከን 17 ቅጣት እንዲጣል ጠይቋል። ይህ እርከን የሚያስቀጣው ከሦስት ዓመት ከሦስት ወር እስከ 3 ዓመት ከ11 ወር ነው።

የጋምቤላ ክልል ከፍተኛ ፍርድ ቤትም በቀረበለት እርከን ጣሪያ የሆነው የ3 ዓመት ከ11 ወር እስራት በተከሳሽ ላይ እንደወሰነ ዳኛዋ እና ምክትል ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።

ዐቃቤ ሕጉ፤ ያቀረበው የቅጣት እርከን ጣሪያው ስለተወሰነለት ይግባኝ የመጠየቅ ዕቅድ እንደሌለው ለቢቢሲ ተናግሯል።

መደፈር እና "የማስገደድ" ድርጊት ውስብስብነት

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የክልሉ ዳኛ የተሰጠው ውሳኔ እንዳላስደሰታቸው ለቢቢሲ ገልጸዋል። ዳኛው፤ መደፈር የሚለው ሃሳብ ውስብስብነት ከግምት ውስጥ መግባት እንዳለበት ይናገራሉ።

"ልጅቷ በመጀመሪያው ጊዜ [ሲፈጸምባት] ባለማቅረቧ ብቻ እንደተስማማች ተደርጎ መወሰዱ ትክክል አይደለም" የሚሉት ዳኛው፤ ልጅቷ አሠሪዋን "ደፍራ መናገር እንደማትችል" ያስረዳሉ።

"ብናገር ያባርረኛል፤ ወይ የሆነ ነገር ያደርገኛል የሚል ነገር አለ። ያንን በሆዷ ይዛ መቆየቷ ተስማምታለች ማለት አይደለም" ይላሉ።

ዳኛው፤ "ማስገደድ" የሚለው ሃሳብ ጉልበት መጠቀምን ብቻ እንደማያመለክት ይገልጻሉ። "አስገድዶ መድፈር ማለት አካላዊ ብቻ ሳይሆን፤ በሥነ ልቦናዊ [መንገድም] ማስገደድ ይቻላል" ሲሉም ያብራራሉ።

"ከሰውየው ጋር ግንኙነት ብትፈጽምም እንኳ ሰውየው አሠሪዋ በመሆኑ መቃወም አትችልም። 'ያባርረኛል፣ ሥራ አጣለሁ' የሚል ፍራቻ ይኖርባታል" የሚሉት ዳኛው፤ ልጅቷ ለድርጊቱ ብትስማማም ጭምር "እሺታው ፈቃደኝነት አይደለም" በማለት አጽንኦት ይሰጣሉ።

የሕግ ባለሙያ እና ጠበቃ የሆኑት አቶ ዳንኤል ፈቃዱም፤ "ማስገደድ" የሚለው ሃሳብ ጉልበት መጠቀምን ብቻ አያመለክትም የሚለውን ይስማሙበታል።

ከዚህ ቀደም ፍርድ የተሰጠበትን አንድ ጉዳይ በማሳያነት በመጥቀስም፤ በተለይም ድርጊቱን የሚፈጽመው ግለሰብ የተጎጂዋ ዕጣ ፋንታ ላይ ለመወሰን የሚያስችል ሥልጣን በሚኖረው ጊዜ፤ ይህ ጉዳይ በራሱ የማስገደጃ መሳሪያ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።