በኳታር የዓለም ዋንጫ ስታዲየሞች ቢራ እንዳይሸጥ ታገደ

ቢራ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዓለም ዋንጫ ውድድሮች በሚካሄድባቸው የኳታር ስታዲየሞች ቢራን ጨምሮ ማንኛውም የአልኮል መጠጦች እንዳይሸጥ ታገደ።

ፊፋ ውድድሩ ሊጀመር ሁለት ቀናት ሲቀረው ፖሊሲውንም ቀይሮ የአልኮል ሽያጭን አግዷል።

የአልኮል ሽያጭ በሙስሊም አገራት ውስጥ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ቢሆንም “በስታዲየሞች ውስጥ በተመረጡ ቦታዎች” እንዲቀርብ ተወስኖ ነበር።

የዓለም ዋንጫ ውድድር ኅዳር 11/2015 ዓ.ም. የሚጀመር ሲሆን፣ በመክፈቻው ዕለትም አስተናጋጇ ኳታር ከኢኳዶር ጋር ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

የፊፋ ዋነኛ ስፖንሰር የሆነው ቡድዌይዘር የተባለው የቢራ ጠማቂው ድርጅት ኤቢ ኢንቤቭ ስር ሲሆን በዓለም ዋንጫ ላይ ቢራ የመሸጥ ብቸኛ መብት ነበረው።

“በአዘጋጇ አገር ባለሥልጣናት እና በፊፋ መካከል የተደረገውን ውይይት ተከትሎ የአልኮል መጠጦች ሽያጭ በፊፋ የደጋፊዎች ፌስቲቫል፣ በሌሎች የደጋፊዎች መዳረሻዎች እና ፍቃድ በተሰጣቸው ቦታዎች ላይ ብቻ እንዲሆን ውሳኔ ተላልፏል።

“የቢራ ሽያጭ በኳታር የዓለም ዋንጫ ስታዲየሞችም ሆነ ግቢው ውስጥ አይቻልም” ይላል የዓለም እግር ኳስ አስተዳዳሪ አካል መግለጫ።

ሆኖም በሁሉም የኳታር የዓለም ዋንጫ ስታዲየሞች ላይ የቢራ ጣዕም ያለውና አልኮል የሌለው በድ ዜሮ ሽያጭ እንደተለመደው ይከናወናል ተብሏል።

መግለጫው አክሎም “የአስተናጋጇ አገር ባለሥልጣናት እና ፊፋ ስታዲየሞች እና አካባቢዎቻቸው ለሁሉም ደጋፊዎች አስደሳች እንዲሆኑ ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ” ብሏል።

“የውድድሩ አዘጋጆች በኳታር በሚደረገው የዓለም ዋንጫ 2022 ሁሉንም ደጋፊዎች ባማከለ መልኩ ለምናደርጋቸው የጋራ ውሳኔዎች ኤቢ ኢንቤቭ ተረድቶ የሚያደርገውን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ያደንቃሉ” ብሏል።

ቡድዌይዘር በበኩሉ በዛሬው ዕለት በትዊተር ገጹ “ይህ ትንሽ ያሳፍራል” የሚል መልዕክት ቢለጥፍም ወዲያውኑ ሰርዞታል።

የእግር ኳስ ደጋፊዎች ማኅበር (ኤፍኤስኤ) ለአብዛኞቹ ደጋፊዎች የቢራ ሽያጭ የተከለከለበትን ጊዜ ተችቷል።