ደማቁ የፓሪስ ኦሊምፒክ መክፈቻ

የ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ በደማቅ ሁኔታ ትናንት ተጀምሯል።

በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ አትሌቶች ሲን ወንዝን ተሻግረዋል።

በወንዙ ዳርቻ እንዲሁም ወንዙን በሚያቋርጠው ድልድይ ላይ የተለያዩ ትርዒቶች ቀርበዋል።

በምድር ላይ “ታላቁ” የሚባለውን የኦሊምፒክ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ፓሪስ በስቴድየም ሳይሆን በወንዝ ዳርቻ አስጀምራለች።

የመክፈቻው ሥነ ሥርዓት አራት ሰዓት ገደማ የወሰደ ነው።

ጁዶ የሚጫወተው ፈረንሳዊ ቴዲ ሪነርና አትሌቷ ማሪ-ዦሴ ፔሬክ ትልቁን የኦሊምፒክ መብራት አብርተዋል።

ወደ ሰማይ ከፍ ብሎ ሲበራም ታይቷል።

ሰማያዊ፣ ነጭና ቀይ ርችት በኦስተርሊትዝ ድልድይ ከተተኮሰ በኋላ 6,800 አትሌቶችና 205 ተወካዮች በጀልባ ሆነው በፈረንሳይ ዝነኛ አካባቢዎች ተጉዘዋል።

ሌዲ ጋጋ በመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ከዘፈኑ አንዷ ናት። በሕመም ምክንያት ከሙዚቃ ርቃ የነበረችው ሴሊን ዲዮንም አቀንቅናለች።

በፈረንሳይ ፈጣን ባቡሮች ላይ የእሳት ቃጠሎ ጥቃቶች ተፈጽመው ነበር ቀኑ የተጀመረው።

ምሽት ላይ የዘነበው ዝናብም የመክፈቻውን ሥነ ሥርዓት ዕቅድ አዛብቷል። የሥነ ሥርዓቱ አርቲስቲክ ዳይሬክተር ቶማስ ጆሊ ዕቅድ የነበረው የፓሪስ ፀሐይ ወንዙ ላይ ሲያርፍ የሚፈጥረውን ነፀብራቅ ማሳየት ነበር።

አትሌቶች የዝናብ ኮትና ጥላ ይዘው ገብተዋል። የፈረንሳይን ታሪክ ከሚያሳየው ጉዟቸው ግን አልተስተጓጎሉም።

ወደ 2,000 የሚጠጉ ድምጻውያን፣ ደናሾችና ሌሎችም አርቲስቶች ተሳትፈዋል።

በመጨረሻዎቹ ሁለት መርከቦች የገቡት አሜሪካ እና ፈረንሳይ ናቸው።

አሜሪካ የሎስ አንጀለስ 2028 ኦሊምፒክ አዘጋጅ ናት።

ጀልባ ቀዛፊዋ ሔለን ግሎቨርና ዋናተኛው ቶም ዴሊ ዩናይትድ ኪንግደምን ወክለው ተገኝተዋል።

ፓሪስ 33ኛውን የኦሊምፒክ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ያከናወነችው ፈረንሳይ በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ፖለቲካም ቀውስ ውስጥ ባለችበት ወቅት ነው።

የዓለም አቀፉ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት ቶማስ ባክ አትሌቶቹ “ዓለምን በሰላም የሚያስተሳስር ሥነ ሥርዓት አካል” እንደሆኑ ገልጸዋል።

በ32 ስፖርቶች ከ10,500 በላይ አትሌቶች ይወዳደራሉ። የፊታችን ሐምሌ 11 ይጠናቀቃል።