በኦሊምፒክ የፍልስጤምን ሰንደቅ ዓላማ ለመጀመሪያ ጊዜ ያውለበለበው እና በጋዛ ጦርነት የሞተው አትሌት

ወቅቱ የአውሮፓውያኑ 1996 ነበር።

በአሜሪካዋ የአትላንታ ሴንተኒያል የኦሊምፒክ ስታዲየም ፍልስጤማዊው ማጅድ አቡ ማራሄል የፍልስጤምን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርጎ እያውለበለበ ይዞ ገባ።

ለመጀመሪያ ጊዜ ሰንደቅ ዓላማዋ ስትውለበለብ በርካቶች በደስታ አነቡ።

በዚህ የኦሊምፒክ ውድድር መክፈቻ ላይ ከማጅድ በፊት በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍልስጤም የሚል ባነር የያዙ አዘጋጆችም ነበሩ።

በስታዲየሙ የነበሩ 80 ሺህ ተመልካቾች እንዲሁም በቤታቸው የነበሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህችን ታሪካዊ ዕለት ተመለከቱ።

“ይህች ለፍልስጤም ታሪካዊ ዕለት ነበረች። በስፓርታዊ እንቅስቃሴ ብቻ ሳይሆን እንደ አገር ግዛቷን እንዲሁም የዕውቅናዋን ጥያቄ ወደፊት በማምጣት ትልቅ ምዕራፍ ነበረች። ፍልስጤም የሚለውም ስም በሁሉም የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ታየ” ሲሉ በአውሮፓ ዩኒቨርስቲ የኦሊምፒክ ጥናት እና ምርምር ፕሮፌሰር ሃቪዬር ዴል ካስቲሎ ለቢቢሲ ሙንዶ ተናግረዋል።

“ያች ቅጽበት የፍልስጤም ሕዝብ እንደ አገርነት ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘት የሚያደርገውን ትግል የሚያሳይ ምልክት ነበር” ይላሉ።

በዚህች ታሪካዊ ዕለት ፍልስጤምን በዓለም መድረክ ለማስቀመጥ ሰንደቅ ዓላማውን እያውለበለበ የገባው ማጅድ በጋዛ ጦርነት ሕይወቱ አልፏል።

ለሩብ ክፍለ ዘመን ያህል ማጅድን የሚያውቁት የታሪክ ምሁሩ ሳን ቻርለስ ሄዳድ “ማጅድ ከአፉ መጥፎ ቃል የማይወጣው። የሚያውቁት ሁሉ በበጎ የሚያነሱት ነበር” ይላሉ።

ማጅድ በማኅበረሰቡ የተከበረ ሰው ነበር የሚሉት ምሁሩ ለፍልስጤማውያን ብቻ ሳይሆን “ዓለም አንድ ልዩ ሰው አጥታለች” ብለዋል።

“የወርቅ ሜዳሊያውን አሸንፈናል”

ማጅድ በኦሊምፒክ ውድድሩ ላይ የ10 ሺህ ሜትር ርቀት ሩጫ ተሳታፊ ቢሆንም ውድድሩን ማሸነፍ ወይም ሜዳሊያ ማግኘት እንደማያስጨንቀው ማርክ ሸርማን የተባለ ጋዜጠኛ ለአትላንታ ጆርናል ጽፎ ነበር።

የ32 ዓመቱ ፍልስጤማዊ ዋነኛ ዓላማው የነበረው በስታዲየሙ በሰዓቱ ተገኝቶ የማጣሪያ ውድድሩን ማለፍ እና በፍልስጤም ሰንደቅ ዓላማ ሥር ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ መወዳደር ነበር።

“እዚህ በመሆናችን የወርቅ ሜዳሊያውን አሸንፈናል” ብሎ እንደነበርም ጋዜጠኛው ጽፏል።

ማጅድ ከጋዜጠኛው ጋር በነበረው ቆይታ ከእስራኤል ጦር የተተኮሰበት ጥይት የጣለበትን ጠባሳም አሳይቶት ነበር።

አትሌቱ የፍልስጤማውያን በአትላንታ መገኘት “ህመምን የሚሽር እንዲሁም አንዳንድ መራር ትዝታዎችን የሚያስረሳ ነው” ብሎ ያምን ነበር።

በኦሊምፒክ እስራኤል እና ፍልስጤማውያን ሲገናኙ የሰላም መሆን አለበትም ብሎ ነበር።

በኒው ዮርክ ታይምስ ላይ በሰፈረ ጽሁፍ እንዲሁ “ለፍልስጤሙ ሯጭ ሰንደቅ ዓላማውን ማውለብለቡ ድል ነበር” በሚል አስነብቧል።

ማጅድ ባደረገው የማጣሪያ ውድድር 21ኛ ሆኖ አጠናቀቀ።

የቀን ሠራተኛው ማጅድ

ማጅድ የተወለደው በጋዛ ኑሴይራት የስደተኞች መጠለያ ካምፕ በአውሮፓውያኑ 1963 ነው። ወላጆቹ ቤርሳቤህ ከተሰኘችው የአሁኗ ደቡባዊ እስራኤልም ሸሽተው ነው ወደዚህ መጠለያ ካምፕ የገቡት።

ታዋቂው የስፖርት ፀሐፊ ዱድሊ ዶውስ የማጅድን ታሪክ ለመጻፍ ወደ ጋዛ ሰርጥ አቅንቶ ነበር።

በእስራኤል ውስጥ በቀን ሠራተኛነት ተቀጥሮ ይሠራ ነበር ፍልስጤማዊው አትሌት ማጅድ።

በየቀኑም በጋዛ ከሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ኢሬዝ ወደተሰኘው የድንበር የፍተሻ ኬላ ያለውን 20 ኪሎሜትር በሩጫ ነበር የሚጓዘው። አትሌቱ በአንድ የስፖርት ፌስቲቫል ላይ የሩጫ ውድድር አሸነፈ።

በወቅቱ የነበሩት የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዚዳንት ያሲር አረፋት ሽልማት ከሰጡት በኋላ በምን እንደሚተዳደር ጠየቁት።

በእስራኤል ውስጥ በሚገኝ የአበባ እርሻ እንደሚሠራ እና ችግር በሚገጥምበት ወቅት “በፍጥነት ሮጦ አስተማማኝ መጠለያ አገኛለሁ” ሲል መለሰላቸው። አራፋት ፈገግ አሉና ከዚህ በኋላ “በጋዛ የግል ጠባቂዬ ትሆናለህ” አሉት።

ከዚያ በኋላ ማጅድ ከያሲር አረፋት የግል ጠባቂዎች አንዱ ሆነ። በአንድ ወቅትም “ከዚህ ሥራ በጣም የምወደው ነገር ለሥልጠና ጊዜ ማግኘቴ ነው” ሲል ገልጾ ነበር።

ሩጫን እንደ ህክምና

ማጅድ ስፖርትን አጥብቆ ይወድ ነበር

“መሮጥ ይወድ ነበር። እንደ ህክምናም ነበር የሚያየው” ይላሉ የታሪክ ምሁሩ ሃዳድ።

የማጅድ የስፖርት ሕይወት የተጀመረው አልዛይቱን ለተሰኘ የእግር ኳስ ክለብ በመጫወት ነው።

“በወረራ እና በጦርነት ውስጥ ቢያድግም ለአትሌቲክስ ልዩ ፍቅር ነበረው። በጋዛ ጎዳናዎች ላይ ነገሮች ባልተሟሉበት ሁኔታ በትዕግስት እና በጽናት የላቀ ውጤት ማምጣት ችሏል” የሚሉት ደግሞ ጎንዛሌዝ ደል ካስቲሎ ናቸው።

በየዕለቱም ሳያቋርጥ በባሕር ዳርቻዎች ይሮጣል። በአገር ውስጥ ውድድሮች በማሸነፍም ፈጣኑ ሯጭ ሆኖ ነበር።

ጋዜጠኛው ሸርማን በአትላንታ የሚገኙ የስፖርት ተቋማት በጋዛ ሰርጥ ከሚገኙት ጋር ሲወዳደሩ ምን ያህል ልዩነት አላቸው ብሎም ሲጠይቀው ማጅድ “የሰማይ እና የምድር ያህል” ሲል መልሷል።

ማጅድ አሠልጣኝ ኖሮት እንደማያውቅ እንዲሁም ተገቢ የሆነ የሩጫ ጫማም እንዳልነበረው ተዘግቧል።

የማጅድ ታሪክ ከፍልስጤማዊ አባት እና ከአሜሪካዊ እናት ለተወለዱት የታሪክ ምሁሩ ሃዳድ ከፍተኛ መነሳሳትን የፈጠረላቸው ነው።

ከሯጭ በላይ

ማጅድ የፍልስጤምን ሰንደቅ ዓላማ በኦሊምፒክ መድረክ የማውለብለብ ሚና ታሪካዊ ጠቃሜታውን እንደተረዳው የታሪክ ምሁሩ ይናገራሉ።

ማጅድ ሰንደቅ ዓላማውን እንዲይዝ የተመረጠው ከስፖርተኝነቱ በተጨማሪ ሌሎች መስፈርቶች ተካተው እንደሆነ ሃዳድ ያስረዳሉ።

“ትሁት፣ ታማኝ ሰው ነበር። በፓርቲው ውስጥ ራሱን በሥልጣን እርከን ለማሳደግም የሚጠቅም አልነበረም” ይላሉ።

የታሪክ ምሁሩ የሚጠቅሱት ፓርቲ በ1950ዎቹ በያሲር አራፋት የተመሠረተውን ፋታህ የተባለውን የፖለቲካ ድርጅት ነው።

የፍልስጤም ሰንደቅ ዓላማ እንዲህ መውለብለብ በቀላሉ የመጣ አይደለም፣ ረዥም እና ውስብስብ መንገዶችን ያለፈ ነው።

ከአውሮፓውያኑ 1970ዎቹ ጀምሮ የፍልስጤም አመራሮች ለፍልስጤም ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) እውቅና እንዲሰጥ እየጠየቁ ነበር። ኮሚቴው እውቅና ያገኘው በአውሮፓውያኑ 1993 ነው።

“በኦሊምፒክ ውድድሮች ላይ ሰንደቅ ዓላማችን ሲውለበለብ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። በደስታ አነባን” ሲሉም በወቅቱ የኮሚቴው ዋና ፀሐፊ ኦማር አሊ በኤቢሲ ስፖርት ለቀረበው ዘጋቢ ፊልም ተናግረው ነበር።

“ያለ ጥርጥር የፍልስጤም ማንነት የተረጋገጠባት እንዲሁም ለአረቡ ዓለምም ታሪካዊ ዕለት ነበረች” ሲሉ በካይሮ በሚገኘው የአሜሪካ ዩኒቨርስቲ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ፕሮፌሰር ኢብራሂም አዋድ ይናገራሉ።

የአሠልጣኝነት ሕይወት

የማጅድ በአትላንታ መገኘት መጪውን የፍልስጤም ልጆች እና ወጣቶች የስፖርቱን ፈለግ እንዲከተሉ አነሳስቷቸዋል ይላሉ ጎንዛሌዝ ደል ካስቲሎ።

ማጅድ ከኦሊምፒክ ተሳትፎው በኋላ በፍልስጤም ታዳጊዎችን በማሠልጠን፣ ፍልስጤማውያንን በዓለም አቀፍ ውድድሮች ላይ በማስተዋወቅ በአጠቃላይ ለአትሌቲክሱ ስፖርት እድገት ከፍተኛ ሚና መጫወቱን ነው ካስቲሎ የሚናገሩት።

በአውሮፓውያኑ 2008 እና 2012 ለተደረጉ ኦሊምፒኮችም አትሌቶችን አዘጋጅተዋል።

“የማጅድ አሻራ በፖለቲካ ጭቆና እና ወታደራዊ ግጭት ውስጥ ላሉት ፍልስጤማውያን አቅም እና ቁርጠኝነትን ማስታወሻ ነው” ሲሉ ይገልጹታል።

በአውሮፓውያኑ 1998 የፍልስጤም የውሃ ቀዘፋ ፌዴሬሽንን የመሠረቱት የታሪክ ምሁሩ ሃዳድ፣ ማጅድ አትሌቶቹን በጋዛ ከተማ በሚገኝ የስፖርት ሜዳ ላይ ለሩጫ ይወስዳቸው እንደነበር ያወሳሉ።

እዚያም ከማጅድ ጋር ተገናኙ።

“በአትሌቶች በጣም የተወደደ ነበር። ሲያሠለጥን እና መመሪያ ሲያስቀምጥ በአክብሮት ነው። ድምጹንም ከፍ አድርጎ የሚያሰማ ሰው አልነበረም” ይላሉ።

“ልጁ ከዚህ ቀደም ከነበሩት በአንዱ የጋዛ ጦርነቶች ሲጎዳ ደወልኩለት። ስለተከሰተው ነገር ወይም ስለ እስራኤላውያን መጥፎ ቃል አልወጣውም። በቁጣም የሚናገር ሰው አልነበረም” ብለዋል።

የፍልስጤም የኦሊምፒክ ኮሚቴ በበኩሉ ማጅድ አዳዲስ አትሌቶችን የማብቃት ሥራዎችን እንዲሁም ለአሠልጣኞች፣ ለዳኞች እና ለባለሥልጣናት ሥልጠናዎችን ያዘጋጅ እንደነበር ለቢቢሲ ሙንዶ ገልጿል።

ኮሚቴው ማጅድ ምን ያህል ለሥራ ትጉህ እንደነበር፣ በሥነ ምግባር የታነጸ፣ ትብብርን ዓላማ ያደረገ ግለሰብ እንደነበር አስታውሷል።

የማጅድ መጨረሻ

በኦሊምፒክ መድረክ ላይ የፍልስጤምን ሰንደቅ ዓላማ በማውለብለብ ታሪክ የሠራው ማጅድ ሰኔ ወር ላይ በ61 ዓመቱ ይህችን ዓለም ተሰናብቷል።

እስራኤል በሙሉ ከበባ ውስጥ ባስገባቻት ጋዛ ከዚህ ቀደም የጤና ችግር ያልነበረው ማጅድ በምግብ እጥረት ምክንያት ህመም ላይ ወደቀ።

ይህ ብቻ አይደለም ከመኖሪያው አል ኑሴይራት የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ተፈናቀለ።

“ይህም ሁኔታ ኩላሊቱን ከጥቅም ውጪ አደረገው፤ ህክምና ጋዛ ውስጥ ባለመኖሩ ሊታከም አልቻለም። ለአጭር ጊዜ ቢያገግምም ህመሙ እየተባባሰ ሄዶ በመጨረሻም በሚያሳዝን ሁኔታ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል” ብሏል ኮሚቴው።

እስራኤል በጋዛ ውስጥ እየፈጸመችው ባለው ጥቃት ከ38900 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን እንዲሁም ከ70 ሺህ በላይ መቁሰላቸውን ከጋዛ የጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያሳያል።

ከእነዚህም ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች እና ህጻናት መሆናቸውንም በሐማስ አስተዳደር ሥር ካለው የጤና ሚኒስቴር የወጣው መረጃ አመልክቷል።

ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ውስጥ በፈጸመው ጥቃት 1200 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ 253 ሰዎች ታግተው ተወስደዋል።