የኳታር አየር መንገድ አውሮፕላን ባጋጠመው መንገጫገጭ 12 ሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ

ከኳታር ዶሃ ወደ አየርላንድ ደብሊን ሲጓዝ በነበረ የኳታር አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ ባጋጠመ መንገጫገጭ 12 ሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰ።

ቦይንግ 787-9 ድሪምላይነር አውሮፕላን በመጥፎ የአየር ጸባይ ምክንያት መንገጫገጩ ያጋጠመው ቱርክ አየር ክልል ውስጥ ሳለ ነበር ተብሏል።

በአውሮፕላኑ መናወጥ 6 መንገደኞች እና 6 የበረራ አስተናጋጆች ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 8 ሰዎች ተጨማሪ የሕክምና ድጋፍ አስፈልጓቸው ወደ ሆስፒታል ተወስደዋል።

አውሮፕላኑ በቱርክ የአየር ክልል ውስጥ ሳለ በሚነቀንቅ የአየር ሁኔታ ውስጥ ቢያልፍም በመዳረሻው ያለ ችግር አርፏል ተብሏል።

የደብሊን አየር ማረፊያን የሚያስተዳድረው ዲኤኤ ቃል አቀባይ የአየር ማረፊያው ሠራተኞች ለኳታር አየር መንገድ እና ለተሳፋሪዎች አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠታቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል።

በአውሮፕላኑ ተሳፍረው የነበሩ መንገደኞች በረራውን እጅግ በጣም አስፈሪ እና የሚያስጨንቅ ነበር ሲሉ ገልጸውታል።

መንገደኞቹ ምግብ እና መጠጥ እየቀረበ ባለበት ወቅት አውሮፕላኑ ለሰከንዶች ድንገት ከአየረ ላይ እየወደቀ ያለ ይመስል ነበር ሲሉ ክስተቱን ገልጸዋል።

ካታል የተባለ መንገደኛ መንገጫገጩ ሲያጋጥም ቀበቷችሁን ታጠቁ የሚለው ምልክት ጠፍቶ እንደነበረ እና ከፊቱ ቀርቦ የነበረው ምግብ መውደቁን ተናግሯል።

“ምግብ እና መጠጥ በየቦታው ወዳድቆ ነበር። ጣራው ላይ፤ መሬት ላይ” ሲል ለአርቲኢ ተናግሯል።

ፖል ሞክ የተባለ መንገደኛ ደግሞ በንቅናቄው ወቅት ቀበቶ አስረው ያልነበሩ መንገደኞች ከአውሮፕላኑ ጣራ ጋር ሲጋጩ ተመልክቻለሁ ብሏል።

“እኔ ቀበቶ ታጥቄ ነበር። ምግብ እየቀረበ ስለነበረ ብዙ የበረራ አስተናጋጆች ተጎድተዋል” ያለ ሲሆን ከክስተቱ በኋላ ሲያነክሱ የነበሩ እና ፋሻ የታሰራላቸው የበረራ አስተናጋጆችን መመልከቱ ተናግሯል።

ሞክ ከክስተቱ በኋላ የበረራ አስተናጋጆች መንገደኞችን ማስተናገድ መቀጠላቸውን ጨምሮ ገልጿል።

ኳታር አየር መንገድ ክስተቱን በተመለከተ ለቢቢሲ በላከው መግለጫ “አነስተኛ ቁጥር ያላቸው መንገደኞች እና የበረራ አስተናጋጆች ቀለል ያለ ጉዳት ደርሶባቸው የሕክምና ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው” ካለ በኋላ ክስተቱን በተመለከተ ምርመራ ይደረጋል ብሏል።

በተመሳሳይ ከጥቂት ቀናት በፊት ከለንደን ወደ ሲንጋፖር ሲጓዝ በነበረ የሲንጋፖር አየር መንገድ አውሮፕላን ላይ ባጋጠመው ከፍተኛ መንገጫገጭ የአንድ ተሳፋሪ ሕይወት ሲያልፍ 140 መንደኞች እና የበረራ አስተናጋጆች መጎዳታቸው ይታወሳል።

ከአምስት ቀናት በፊት ባጋጠመው ክስተት ከተጎዱት መካከል 20 የሚሆኑት አሁንም በጽኑ ሕሙማን ክፍል ክትትል እየተደረገላቸው ነው።