ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኔታኒያሁ እና ፑቲን ዘብጥያ እንዲወርዱ የሚታገሉት ዐቃቤ ሕግ ካሪም ኻን ማን ናቸው?
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር እና የመከላከይ ሚኒስትሩ እንዲሁም የሐማስ መሪዎች ላይ የእሥር ትዕዛዝ እንዲወጣባቸው ጠይቋል።
ችሎቱ እንደሚለው እነዚህ መሪዎች በጦር ወንጀሎች እና ሰብዓዊነት ላይ በተፈፀሙ ወንጀሎች ተጠርጠርዋል።
ይህን ጉዳይ እየተከታተሉ ያሉት የፍርድ ቤቱ ዋና ዐቃቤ ሕግ ካሪም አሳድ አሕመድ ኻን ናቸው። ካሪም ኻን ትውልደ ፓኪስታናዊ ናቸው።
ኻን፤ ለችሎቱ ባቀረቡት ማመልከቻ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ እና በጋዛ የሐማስ መሪ የሆኑት ያህያ ሲንዋር የጦር ወንጀል እና ሰብዓዊነት ላይ ወንጀል እንደፈፀሙ “የሚያሳምንት ተጨባጭ ምክንያት አለ” ብለዋል።
ሁለቱ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ የሐማስ መሪ የሆኑት ኢስማኢል ሃኒየህ፣ ሞሐመድ አል-ማስሪ እንዲሁም የእስራኤሉ መከላከያ ሚኒስትር ዮዋቭ ጋላንት ተጠርጥረዋል።
የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ ዋናው ዐቃቤ ሕግ የእስር ትዕዛዝ እንዲወጣ መጠየቃቸውን ኮንነው፣ ድርጊቱ “የማይመስል እና ሐሰተኛ እርምጃ” ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።
ኔታኒያሁ፤ ዋናው ዐቃቤ ሕግ ሐማስ እና አስራኤልን ማንፃፀራቸው “የተዛባ እውነታ” ነው ብለዋል።
ለመሆኑ ዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት ዐቃቤ ሕግ ካሪም አሳድ አሕመድ ኻን ማን ናቸው?
ከኤደንብራ እስከ አይሲሲ
ካሪም አሳድ አሕመድ ኻን የተወለዱት በአውሮፓውያኑ መጋቢት 30/1970 በስከትላንዷ ኤንደብራ ከተማ ውስጥ ነው።
አባታቸው ዶክተር ሳኢድ አሕመድ ፓኪስታናዊ ናቸው። በ1960ዎቹ ነው ከፓኪስታን ወደ ብሪታኒያ የመጡት። የአሳድ ኻን እናት የብሪታኒያ ዜጋ ናቸው።
በ1992 ከለንደኑ ኪንግስ ኮሌጅ የሕግ ዲግሪ ያገኙት ካሪም ኻን ከተመረቁ በኋላ ወደ ሥራ ገቡ።
የለንደን የሕግ ኩባንያ የሆነው ቴምፕል ጋርደን ቻምበርስ አባል የሆኑት ኻን፣ ከ30 ዓመታት በላይ የዘለቀ ልምድ ያላቸው ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ ባለሙያ እና የሰብዓዊ መብት ጠበቃ ናቸው።
ዐቃቤ ሕግ ሆነውም ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል። በአገር እና ዓለም አቀፍ ደረጃ የተጎጂዎች አማካሪ እና የተከሳሾች ጠበቃም ሆነው ሠርተዋል።
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት፣ ዓለም አቀፉ የሩዋንዳ የወንጀል ችሎት፣ የቀድሞው ዩጎዝላቪያ ዓለም አቀፍ ችሎት፣ የካምቦዲያ ችሎት፣ የሊባኖስ እና የሴራሊዮን ዓለም አቀፍ ችሎት እንዲሁም ሌሎች ችሎቶች ላይም ተሳትፈዋል።
የጋዳፊ ልጅ ጠበቃ
ካሪም ኻን የዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት ዋና ጠበቃ ሆነው ከማገልገላቸው በላይ ከ2016 እስከ 2018 ባለው ጊዜ የቀድሞው የሊቢያ ፕሬዝዳንት ሞአማር ጋዳፊ ልጅ ሳይፍ አል-ኢስላም ጠበቃ ሆነውም ሠርተዋል።
ከ2017 እስከ 2018 የአይሲሲ የጠበቆች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ያገለገሉት ኻን፣ የአፍሪካ ጠበቆች ማኅበር ዓለም አቀፍ አምባሳደር ናቸው።
በ2018 የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ የመጀመሪያው ልዩ አማካሪ እና በኢራቅ የጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀለኞች መርማሪ ቡድን ኃላፊ አድርገው ሾመዋቸው ነበር።
የካቲት 2021 ኻን የዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት አቃቤ ሕግ ሆነው ኒው ዮርክ በተካሄ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ተመረጡ። ሰኔ 2021 ቃለ-መሐላ የፈጸሙ ሲሆን፣ ለዘጠኝ ዓመታት እዚህ መንበር ላይ ይቆያሉ።
በ2002 የተቋቋመው ዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት (አይሲሲ) ሦስተኛው ዐቃቤ ሕግ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።
አይሲሲ የአንድ ኃያል አገር መሪ ላይ የእሥር ትዕዛዝ እንዲወጣበት ሲጠይቅ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
ከአንድ ዓመት በፊት የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የእስር ትዕዛዝ እንዲወጣባቸው ትልቅ ሚና የተጫወቱት ካሪም ኻን ናቸው። ከፑቲን በተጨማሪ በሩሲያ የሕፃናት መብት ኮሚሽነር የሆኑት ማሪያ ሌቮቫ ቤሎቭ በቁጥጥር ሥር እንዲውሉ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል።
ይህ ውሳኔ ከተላለፈ ከጥቂት ቀናት በኋላ ሩሲያ ካሪም ኻን እና ሌሎች ሦስት የአይሲሲ ዳኞች ላይ ምርመራ ከፈተች። ከምርመራው በኋላ በዚህ ውሳኔ ላይ የተሳተፉ የአይሲሲ ባለሥልጣናት “ተፈላጊ ወንጀለኞች” ናቸው ስትል ፈረጀች።
በአይሲሲ የሚፈለጉት ፑቲን በቁጥጥር ሥር እንዳይውሉ በመስጋት ደቡብ አፍሪካ ባዘጋጀችው የብሪክስ አገራት ስብሰባ ላይ ሳይገኙ ቀሩ።
ኔታኒያሁ እና የሐማስ መሪዎች የተፈለጉት ለምንድነው?
ካሪም ኻን እና አጋሮቻቸው ባለፈው መስከረም መጨረሻ የሐማስ ጥቃት ተጎጂ የሆኑ ሰዎችን ካናገሩ በኋላ የሐማስ መሪዎች ጥቃቱን በማቀድ እና በማስፈፀም ተጠያቂ ናቸው ብለዋል።
ኻን እንደሚሉት ሐማስ የፈፀማቸው የጦር ወንጀሎች መሰወር፣ ግድያ፣ አፈና፣ መድፈር እና ማሰቃየትን ያካተቱ ናቸው።
በሌላ በኩል ኔታኒያሁ እና ጋላንት ደግሞ ረሀብን እንደ ጦር መሣሪያ በመጠቀም እንዲሁም ሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት በመፈፀም ተጠርጥረው ነው የሚፈለጉት።
ማስረጃ የተሰበሰበው “ከጥቃቱ የተረፉ ሰዎችን በማናገር፣ የዐይን እማኞችን ቃለ-መጠይቅ በማድረግ እና ቪድዮ፣ ፎቶ እንዲሁም የድምፅ ይዘቶችን በመሰብሰብ” ነው።
የአይሲሲው ዋና ዐቃቤ ሕግ ካሪም ኻን “እስራኤል ሆነ ብላ በተቀነባበረ መንገድ በሁሉም የጋዛ ክፍሎች የሚገኙ ሰላማዊ ሰዎችን መሠረታዊ ፍላጎቶች ነፍጋለች” ይላል።
የዐቃቤ ሕጉ መግለጫ እንደሚለው እስራኤል ራሷን የመከላከል መብቷ የተጠበቀ ሆኖ ነገር ግን “ይህ መብት እስራኤልም ሆነች የትኛውም አገር ዓለም አቀፍ ሕጎችን እንዲጥስ የሚፈቅድ አይደለም” ብሏል።
የቢቢሲው ጄሬሚ ቦዌን እንደሚለው የካሪም ኻን መግለጫ ዋና ዓላማው በግጭት ጊዜ ሁሉም ተሳታፊዎች ዓለም አቀፍ ሕጎችን የማክበር ግዴታ አለባቸው ለማሳሰብ ነው።
“የትኛውም እግረኛ ተዋጊ፣ የትኛውም አዛዥ፣ የትኛውም ሲቪል መሪ - ማንም ይሁን ማን - ከተጠያቂነት አያመልጥም” የሚለው መግለጫ፣ ሕጉ ለአንዱ ሠርቶ ለሌላው የማይሠራበት ምክንያት የለም የሚለውን ያሰምርበታል።
“ማንም ከሕግ በላይ አይደለም”
ከአሜሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲኤንኤን ጋር በቅርቡ ቆይታ ያደረጉት ካሪም ኻን “ዘር ማጥፋት” የሚለውን ለምን እንዳልተጠቀሙት ተጠይቀው ነበር።
“ይህ ምርመራ ገና አልተጠናቀቀም” ያሉት ዐቃቤ ሕጉ አሁን ለዳኛ የቀረበው ክስ ዘር ማጥፋት (ጄኖሳይድ) የሚለውን ሐሳብ የያዘ አለመሆኑን አመልክተዋል።
“ምርመራችን ይቀጥላል። ሁኔታው እጅግ የተወሳሰበ ነው” የሚሉት ኻን ወደ ጋዛ ገብተው ምርመራ ለማድረግ ያቀረቡትን ጥያቄ የእስራኤል ባለሥልጣናት እንዳልፈቀዱላቸው ይናገራሉ።
ቀጣዩ እርምጃ የአይሲሲ ዳኞች ተሰባስበው የእሥር ትዕዛዝ መውጣት አለበት ወይ የሚለውን ውሳኔ የሚያፀድቁበት ነው። ይህ ሒደት ሳምንታት ሊወስድ ይችላል።
ዩናይትድ ስቴትስ እና እስራኤል በአይሲሲ ሕግ አይመሩም።
የእሥር ትዕዛዝ እንዲወጣ መጠየቁ “አሳዛኝ” ነው ያሉት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን “በእስራኤል እና በሐማስ መካከል ምንም ዓይነት ንፅፅር ሊኖር አይገባም” የሚል ሐሳብ አላቸው።
የፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ የእስር ትዕዛዝ እንዲወጣ ለመጠየቅ እየተንደረደሩ ነው የሚለው ወሬ ብቅ ማለት ሲጀምር አስተያየት የሰጡት ኔታኒያሁ አይሲሲ የትኛውም የእስራኤል ባለሥልጣን ላይ የሚያወጣው የእስር ትዕዛዝ “ታሪካዊ ስህተት ነው” ብለው ነበር።
ኔታኒያሁ አክለውም እስራኤል “የራሷ ነፃና ገለልተኛ የሆነ ዓለም አቀፍ ሕጎች መጣሳቸውን የሚመረምር ሥርዓት አላት” ማለታቸው ይታወሳል።
ቤተሰላም የተሰኘው ዋነኛ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት የእስር ትዕዛዝ እንዲወጣ መጠየቁ “እስራኤል በሚገርም ፍጥነት የሞራል ውድቀት እየገጠማት” እንደሆነ ማሳያ ነው ብሏል።
ኔታኒያሁ ስለሰጡት አስተያየት በሲኤንኤን የተጠየቁት ካሪም ኻን “ማንም ከሕግ በላይ አይደለም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።