የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት የቆቦ ከተማን ለቅቆ መውጣቱ ተገለጸ

የኢትዮጵያ መከላከያ ኃይል በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን ከምትገኘው ቆቦ ከተማ ለቅቆ መውጣቱን መንግሥት አስታወቀ።

የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በትናንትናው ዕለት ነሐሴ 21፣ 2014 ዓ.ም እንዳስታወቀው “የህዝብን ፍጅት ለማስወገድ ሲባል” መከላከያ የቆቦ ከተማን መልቀቁን ገልጿል።

የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው ባወጡት መግለጫ "በጸረ ማጥቃት ዘመቻ" የቆቦን ከተማ መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል።

የመንግሥት ኮሚዩኑኬሽን መግለጫ ህወሃት የቆቦ ከተማን ከውጭ “በብዙ አቅጣጫ” እያጠቃ አንደሆነ ገልጾ “የህዝቡን ደህንነት አደጋ ውስጥ በሚያስገባ መልኩ የከተማ ውስጥ ውጊያ ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ እየፈጠረ ይገኛል” ብሏል።

በዚህም የተነሳ "መከላከያ የቆቦ ከተማን ለቆ ወደ ኋላ መጥቶ ለመከላከል የሚያስችለውን ወታደራዊ ይዞታዎችን ለመያዝ ተገዷል" ብሏል።

የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው ባወጡት መግለጫ” የተከፈተባቸውን ጥቃት ለመከላከል በተደረገ የጸረ ማጥቃት ዘመቻ” የቆቦን ከተማን ጨምሮ ጉጉውዶ፣ ፎኪሳ፣ ዞብል፣ መንደፈራ፣ሮቢት፣ ሽዎች ማርያምና ተኮሎሽ የሚባሉ ስፍራዎችን መቆጣጠራቸውን አስታውቀዋል።

በዚሁ መግለጫ ላይ በኢትዮጵያ መከላከያ፣ አማራ ክልልና ፋኖ መጠነ ሰፊ ጥቃት እንደተከፈተባቸውና እየተከላከሉም እንደሆነ ገልጸዋል።

አዲስ ባገረሸው ግጭት ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎት ማቆሙን ተከትሎ በርካቶች በእግራቸው በአካባቢው ወደሚገኙ የተለያዩ ስፍራዎች እየሸሹ መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለአምስት ወራት ጋብ ብሎ የነበረው የርስበርስ ጦርነት ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. አገርሽቶ ወደ ከፋ ደም አፋሳሽ ግጭት እንዳይገባ ስጋት ፈጥሯል።

ግጭቱን በመጀመር አንደኛው ወገን ሌላኛውን እየከሰሰ ሲሆን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና መንግሥታት የፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ኃይሎች ግጭቱን አቁመው ለድርድር እንዲቀመጡ ጥሪ እያቀረቡ ነው።

በፌደራል መንግሥቱና በትግራይ አመራሮች መካከል ተደርሶ የነበረው የሰብአዊ ተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሶ ከቀናት በፊት የተጀመረው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆምም ጠይቀዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት የአስር ሺዎችን ሕይወት በመቅጠፍ፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብአዊ ቀውስ አድርሷል።

በሁለቱም ወገኖች በኩል የሰብአዊ ተኩስ አቁም አዋጅ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ጦርነቱ ጋብ ቢልም በትግራይ ያለው የምግብና ነዳጅ ዕጥረት እንዲሁም ስልክ፣ ውሃ፣ መብራት፣ ባንክ የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች ተቋርጠው መቀጠላቸው ሕዝቡን ለፈተና እንዳረጉት የረድዔት ድርጅቶች ይገልጻሉ።

ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን የእርስ በእርስ ጦርነት በድርድር ለመቋጨት የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረት እና የተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጥረት እያደረጉ መሆናቸው ይታወቃል።

ሁለቱም ወገኖች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውና ተደራዳሪ ኮሚቴም አዋቅረናል ቢሉም በአሁኑ ወቅት ጦርነት እንደ አዲስ መቀስቀሱ የሰላም ሂደቱን አደጋ ላይ ጥሎታል።