ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሃሳብ ሙግቶች ወደ ግጭት እንዳያመሩ ለመከላከል የሚረዱ ሦስት ነጥቦች
አለመግባባት በሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ የሚያጋጥም ክስተት ነው። ልናስቀረውም አንችልም፤ ምክንያቱም ሁላችንም አንድ ዓይነት አይደለንም።
በሃሳብ አለመግባባት በጽሑፍ መልዕክት አሊያም በኦንላይን በምናደርጋቸው የመልዕክት ልውውጦች ወይም በፊት ለፊት ንግግሮች ወቅት ሊያጋጥም ይችላል።
በጽሑፍ የምናደርጋቸው ክርክሮችን አርትኦት [ኤዲት] ማድረግ ስለሚቻል ወደ ግጭት የማምራታቸው ዕድል አነስተኛ ቢሆንም፣ ፊት ለፊት ተገናኝተን 'አንገብጋቢ' በሆኑ ጉዳዮች ላይ መከራከር ወደ ግጭት ሊያመራ ይችላል።
በተለይ ከቤተሰቦቻችን፣ ከሥራ ባልደረቦቻችን እና ጓደኞቻችን ጋር በሰፊው በምንገናኝበት ወቅት ያጋጥማል። ይህም ደስ የማይል ሁኔታን ከመፍጠር ባለፈ ግንኙነትን ለጊዜውም ሆነ እስከ መጨረሻው ሊያበላሽ ይችላል።
ታዲያ በኦንላይንም ሆነ ፊት ለፊት የምናደርጋቸው ቀላል ክርክሮች ወደ የተባባሰ ግጭት ከማምራታቸው በፊት እንዴት መከላከል እንችላለን?
በሎውቦሮው ዩኒቨርሲቲ የማኅበራዊ ሥነ ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ጄሲካ ሮብልስ፣ በክርክር ወቅት ግጭት ሊያስከትል በሚችል መንገድ ምላሾችን ከመስጠትዎ በፊት ሌሎች "ምን እንዳሉ እና እንዴት እንዳሉት" ትኩረት መስጠት ወሳኝ ነው ይላሉ።
ፕሮፌሰር ጄሲካ አለመግባባቶች ወደ የከፋ ግጭት ከማምራታቸው በፊት ለመከላከል የሚያስችሉ ሦስት ምክሮችንም ለግሰዋል።
1. ክርክሩ እንዳይባባስ መቆጣጠር
ከሆነ ሰው ጋር ካልተግባባችሁ ቀጥታ ያልተገቡ ቃላትን ከመወራወር ተቆጥባችሁ ፍሬያማ ንግግር ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች ሰዎችን ወደ የባሰ ውዝግብ ውስጥ ከሚያስገቡ እንደ ወቀሳ፣ ቅሬታ እና ማላገጥ ካሉ ድርጊቶች መቆጠብ ይገባል።
ይልቁኑ በሃሳቡ ላይ እና ያኛው ሰው በትክክል ያሰበው ምንድን ነው? የሚለው ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል።
ክርክሩ ስለምንድን ነው? አለመረዳዳት ነው? አንድ ሰው በነገሩ ላይ ባለው አድልዎ ወይም የተለየ ዓላማ ምክንያት የተፈጠረ ግላዊ ጉዳይ ነው? የሚለውን ለመረዳት መሞከርም ወሳኝ ነው።
2. አእምሯችሁን ክፍት ማድረግ
አንዳንድ ጊዜ አንድ ሰው የተናገረው ነገር በጣም መጥፎ ላይሆን ይችላል። በመሆኑም አንድ ሰው ሲናገር ሁለት ነገሮችን አስቡ።
መጀመሪያ ሁላችንም የምንናገረው ነገር አንድ ትርጉም ብቻ የለውም ብላችሁ አስቡ። በርካታ ትርጉሞች ሊኖሩት ይችላል። በመሆኑም ክርክሩ በተጋጋለበት ቅፅበት መጀመሪያ ወደ አእምሯችሁ በመጣው ነገር ላይ ተመሥርታችሁ መልስ ለመስጠት አትሞክሩ።
በክርክር ወቅት ትንሽ ጊዜ መውሰድ እና ሌሎች ሊሆኑ የሚችሉ ትርጉሞችን ከግምት ማስገባትም ወሳኝ ነው። ትንሽ ጊዜ መውሰድ አሊያም እየተባባሰ ከመጣው ሁኔታ እንድትወጡ መረጋጋት መልካም ነው።
ሁለተኛው ለመረዳት ሞክራችሁ፤ ነገር ግን ያ ሰው የተናገረው ነገር አሉታዊ እንደሆነ ከተሰማችሁ ተጨማሪ እንዲያብራራላችሁ ጠይቁ። በእርግጥ ይህ ቀላል ላይሆን ይችላል። ሆኖም ብዙውን ጊዜ ሰዎች ሃሳባቸውን በሚያብራሩበት ጊዜ ምን ለማለት እንደፈለጉ ይጋለጣሉ።
ሲያብራሩላችሁ እየሰማችኋቸው እንደሆነ እንዲሰማቸው ካደረጋችሁም ደግሞ ነገሮች እንዳይባባስ እና ወዳላስፈላጊ አቅጣጫ እንዳይሄዱ ይረዳል።
3. ትኩረት ማድረግ
በክርክር ወቅት በጥንቃቄ ማለት ያለባችሁን ምረጡ እንዲሁም በሌላው ሰው ዘንድ የምትፈጥሩትን ምሥል ከግምት አስገቡ። በክርክር ወቅት እናንተም ሆናችሁ ሌላ ሰው የምትፀፀቱበትን ነገር ልትናገሩ ትችላላችሁ።
በመሆኑም ይህንን ለማስወገድ የሚረዳው አንደኛው ዘዴ በውይይቱ ላይ ለመሳተፍ እና እንዴት እንደምትሳተፉ ጊዜ ወስዶ ማሰብ ነው።
ይህ ውጤታማ ውይይት እንድታደርጉ ይረዳል። ለምሳሌ ንግግሩ በአንድ ውስን ነገር ላይ ብቻ እንዲያተኩር መጠየቅ ትችላላችሁ።
ሆኖም ይህ ንግግራችሁ በሌላው ሰው ዘንድ የተለየ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል። 'ዘብዛባ ናችሁ አሊያም በአንድ ሃሳብ ላይ አታተኩሩም' እንደማለት ሊወሰድባችሁ ይችላል።
ይህ ከሆነ የገባችሁበትን ክርክር ለመቋጨት ይቅርታ መጠየቅ አሊያም ሌላኛው ሰው 'ያለአግባብ እየተከራከርክ ነው' በሚል እየወቀሳችሁኝ ነው ብሎ እንዳያስብ ድምጸታችሁን [የድምጽ ቶን] መቀነስ ያስፈልጋል።
ይህንን ዘዴ ለመጀመሪያ ጊዜ ስትጠቀሙ ካልሠራላችሁ መጥፎ ነገር እንዳይሰማችሁ። አብራችሁ ከምትከራከሩት ሰው ጋር ተመሳሳይ እሴቶች ላይኖራችሁ ይችላል።
ሰዎች ለመከራከር ብለው አይከራከሩም። እንድንከራከር የሚያደርገን ዋነኛው ምክንያት ከሌሎች ተቃራኒ የሆነ አቋም ስለምንይዝ ነው። በመሆኑም በተመሳሳይ አቋም ላይ ነን? ተመሳሳይ እሴቶችስ አሉን? ብሎ መጠየቅም ወሳኝ ነው።
ክርክሮች ከማንነታችን ጋር ይያያዛሉ። ጤናማ ያልሆኑ ክርክሮችም ጠንካራ የሆኑ ስሜቶችን ይፈጥራሉ። በአመለካከታችን ምክንያት በሌሎች እንደምንፈረጅ እና ሌሎችም በምላሹ እነሱን እንደምንፈርጃቸው ያስባሉ።
በመሆኑም እርስ በእርስ መፈራረጅ ነገሮችን በቀላሉ ያባብሳሉ። ይህም አጠቃላይ ግንኙነታችንን ጊዜያዊ ወደ ሆነ መለያየት ወይም ጭራሽኑ ወደ መቆራረጥ ሊወስደው ይችላል።
በመሆኑም ይህ እንዳይሆን የሚፈልግ ሰው ብዙ ጊዜ ማሰብ የሚገባው መፍትሄ ስሜትን ወደ ጎን ብሎ "በሃሳቦች ላይ ብቻ ለመነጋገር" መሞከርን ነው።