ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሳዑዲ አረቢያ የየመን ተፋላሚ ኃይል በሪያድ ለድርድር እንዲቀመጡ ጥሪ አቀረበች
የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሳዑዲ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን በቀጥታ ያፋጠጠ ሁነት መከሰቱን ተከትሎ የደቡባዊ የመን ተፋላሚ ኃይሎች በሪያድ ንግግር ላይ እንዲገኙ ጥሪ አቅርቧል።
ሁለቱ የገልፍ ኃያላን ዓለም አቀፍ እውቅና ባለው የየመን መንግሥት ስም በረጅሙ የእርስ በእርስ ግጭት እየተሳተፉ ቢሆንም አገራቱ በሚደግፏቸው የተለያዩ ተቀናቃኝ ቡድኖች ምክንያት አጋርነታቸው እየተፈተነ ነው።
ከቡድኖቹ መካከል አንዱ የሆነው ደቡባዊ የመንን በመገንጠል ነፃነት ለማወጅ እየተቃረበ ነው።
አርብ ዕለት በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሚደገፉት ኃይሎች "ጦርነት" መጀመሩን ያሳወቁ ሲሆን፤ የሳዑዲ አረቢያ የምድር ጦር በአየር ጥቃቶች ታግዞ ጥቃት እንደፈፀመባቸው ተናግረዋል።
በማኅበራዊ የትስስር ገፅ ላይ በተለጠፈው የሳዑዲ አረቢያ ጥሪ "ሁሉም የደቡብ የመን አንጃዎች መፍትሄ ለማበጀት በሪያድ ሁሉን አቀፍ ጉባኤ" እንዲሳተፉ አሳስቧል።
ሪያድ ንግግሩን የየመን መንግሥት እንዳቀረበው አሳውቃለች።
የየመን የእርስ በእርስ ጦርነት እ.አ.አ በ2014 የፈነዳ ሲሆን፤ ጦርነቱ አገሪቱን ደም አፋሳሽ ግጭት ውስጥ እና የዓለማችን እጅግ አስከፊ የረሃብ ቀውስም ፈጥሯል።
ጦርነቱ ሲጀመር በኢራን የሚደገፉት የሁቲ አማፂያን ዋና ከተማዋን ሳናን ጨምሮ አብዛኛውን የሰሜን የመን ክፍል ከመንግሥት በመንጠቅ ተቆጣጥረዋል።
እ.አ.አ በ2015 ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን ጨምሮ የአረብ አገራት ጥምረት መንግሥታዊ አስተዳደርን ለመመለስ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈታቸውን ተከትሎ ግጭቱ ተፋፍሞ ቀጥሏል።
በቅርብ ዓመታት ከሁቲ ታጣቂዎች ጋር የተደረሰ የተኩስ አቁም ስምምነት የጦርነት ግንባሮችን ያዝ በማድረግ ጦርነቱ እንዲረግብ አድርጓል።
ይሁን እንጂ የተለያዩ ፀረ ሁቲ የሆኑ አንጃዎችን አንድ ለማድረግ በ2022 የተመሰረተው እና በሳዑዲ የሚደገፈው ፕሬዝዳንታዊ ምክር ቤት የተዳከመ ነው።
በተመሳሳይ ጊዜ አብዛኘው የደቡብ የመን በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በሚደገፈው ተገንጣዩ የደቡብ የሽግግር ምክር ቤት የተያዘ ነው። ይህ ምክር ቤት የፀረ ሁቲ ጥምረቱ አካል ነው።
ደቡብ የመንን የመገንጠል ፍላጎት ያለው የደቡባዊ የሽግግር ምክር ቤቱ ባለፈው ወር በምስራቅ የየመን ክፍል ትልቅ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈቱን ተከትሎ ግጭቱ ተባብሷል።
ምክር ቤቱ በሳዑዲ ድንበር አቅራቢያ በነዳጅ ወደ በለፀገው ሀድራማዋት ግዛት እየገሰገሰ ነው።
ውጥረቱ ሳዑዲ መር ጥምረቱ የአየር ድብደባዎች መፈፀሙን ተከትሎ ተባብሷል።
ባለፈው ማክሰኞ በሙካላ ወደብ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ሁለት መርከብ ወታደራዊ መሣሪያዎችን በአየር ጥቃት ተደብድቧል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ክሱን በማስተባበል መርከቦቹ መሣሪያ እንዳልጫኑ እና ተሽከርካሪዎቹ በኤምራቲ ኃይሎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ የተላኩ ናቸው ብሏል።
የአየር ጥቃቱን ተከትሎ የየመን ፕሬዝዳንታዊ ምክር ቤት ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ጋር የነበረውን የመከላከያ ስምምነት መሰረዙን አስታውቆ፤ ኤምሬትስ የመንን በ24 ሰዓታት ውስጥ ለቅቃ እንድትወጣ ትዕዛዝ አስተላልፏል።
የሳዑዲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እርምጃውን በመደገፍ ተገንጣዩ የደቡብ ሽግግር ምክር ቤት ወደ ሳዑዲ ድንበር እንዲገሰግስ እያበረታታች ነው ሲል ወቅሷል።
ኤምሬትስ ምክር ቤቱን የምትደግፈው ቁልፍ የወደብ ለማግት እንደሆነ ይታመናል።