የየመኑ ሁቲ የጦር ኃይል አዛዡ በእስራኤል ጥቃት እንደተገደሉበት አስታወቀ

የየመኑ የሁቲ ንቅናቄ የጦር ኃይል አዛዡ መሐመድ አል-ገማሪ በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን ገለፀ።

መግለጫው ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም ገማሪ እና ልጃቸው "ከእስራኤል ጋር በተደረገው የጀግንነት ውግያ" ወቅት መሞታቸውን ገልጿል።

ከጋዛ ጦርነት ጋር በተገናኘ የሁቲ ሰው አልባ አውሮፕላን እና የሚሳኤል ጥቃት በእስራኤል እና በቀይ ባህር በሚልቀሳቀሱ መርከቦች ላይ ላደረሱት ጥቃት ምላሽ የእስራኤል ጦር በሁቲ ቁጥጥር ስር በምትገኘው የመን ውስጥ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን ፈጽሟል።

የእስራኤል መከላከያ ሚንስትር እስራኤል ካትዝ ጋማሪ በነሐሴ ወር መገባደጃ ላይ አገራቸው የመን ዋና ከተማ ሰነዓ ላይ በፈፀመችው የአየር ጥቃት ባደረሰው ጉዳት "በደረሰበት ጉዳት የተነሳ ሞቷል" ብለዋል።

በወቅቱ የእስራኤል ጦር በፈጸመው ጥቃት የሁቲ ጠቅላይ ሚኒስትር እና ሌሎች ሚኒስትሮችንም መግደሉን ጠቅሰዋል።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ በሰጡት መግለጫ "እኛን ለመጉዳት ያሰበው የአሸባሪዎች አለቃ የሆነው ሌላ ዋና አዛዥ ከሥልጣኑ ተወግዷል። ሁሉንም እናገኛቸዋለን" ብለዋል።

በኢራን የሚደገፉት ሁቲዎች ከ10 ዓመታት በፊት ዓለም አቀፍ እውቅና ያገኘውን መንግሥት ከሥልጣን ካስወገዱ እና በርካታ የሰሜን ምዕራብ የመን አካባቢዎችን ከተቆጣጠሩ በኋላ ከፍተኛ የእርስ በርስ ጦርነት ተቀስቅሷል።

መስከረም 26 2016 ዓ.ም. ሐማስ እስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት ፈጽሞ በርካቶችን ከገደለ እና ካገተ በኋላ እስራኤል መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ መክፈቷን ተከትሎ ሁቲዎች ከፍልስጤማውያን ጎን መቆማቸውን በመግለጽ ዓለም አቀፍ መርከቦች በሚመላለሱበት ቀይ ባህር ላይ ተደጋጋሚ ጥቃት ፈጽመዋል።

ዩናይትድ ስቴትስ እና ዩኬ በየመን የሁቲ ወታደራዊ ዒላማ ናቸው ያሏቸውን አካባቢዎች ላይ ድብደባ ፈጽመዋል።

ሐሙስ ዐዕለት የወጣው የሁቲ መግለጫ በባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ "ወንጀለኛው የአሜሪካ ጽዮናውያን በአገሪቱ ላይ በፈጸሙት ወረራ" ሲል በጠራው ጥቃት "በርካታ ሰላማዊ ዜጎችን እና ወታደራዊ አባላት፣ ታላላቅ ሰማዕታት" መገደላቸውን አምኗል።

"ሰማዕቱ መሪ ሜጀር ጀነራል መሐመድ አብዱልከሪም አል-ገማሪ ከተወሰኑ ባልደረቦቻቸው እና ሰማዕቱ የ13 ዓመት ልጃቸው ሁሴን ጋር በጅሃድ ሥራቸው እና ሃይማኖታዊ ግዴታቸውን በመወጣት ላይ ሳሉ ሰማዕት ሆነዋል" ሲልም አክሏል።

ቡድኑ እንዲህ ዓይነት ሞት "የኩራት ምንጭ" እንደሆነና የበቀል እርምጃ እንደሚወስድ አስታውቋል።

"ከጠላት ጋር ያለው ጦርነት አላበቃም እናም ጽዮናዊው ጠላት ለፈጸመው ወንጀል ተገቢውን ቅጣቱን ይቀበላል" ሲል አስጠንቅቋል።

የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስቴር በኤክስ ገጹ ላይ ገማሪ "የክፋት ቁንጮ የሆኑትን የተጨናገፉት ጓዶቻቸውን በገሃነም ጥልቅ ውስጥ" ተቀላቅሏል ሲል ጽፏል።

"ጉልህ የሆኑ ስጋቶችን ለማስወገድ በሁቲዎች ላይ ጠንክረን ሰርተናል፤ ወደፊትም ማንኛውንም ስጋት ለመመከት ጠንክረን እንሰራለን" ሲሉም አክለዋል።

እስራኤል ባለፈው ሳምንት ከሐማስ ጋር በጋዛ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ከደረሰች በኋላ የእስራኤል ጦር ምንም ዓይነት ከሁቲ አማፂያን የተተኮሱ የሚሳኤል ወይም ሰው አልባ አውሮፕላኖች ጥቃት ሪፖርት አላደረገም።

የሁቲዎቹ መሪ አብዱል ማሊክ አል-ሁቲ ስምምነቱን ማክበር ካልቻለ ቡድኑ በእስራኤል ላይ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ እንደሚሆን ተናግሯል።