አሜሪካ ባቀረበችው የዩክሬን የሰላም ዕቅድ ላይ በሚደረገው ንግግር "ከፍተኛ መሻሻል" መታየቱ ተገለጸ

አሜሪካ፤ የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነትን ለመቋጨት ያቀረበችውን የሰላም ዕቅድ በተመለከተ የሚደረገው ንግግር ላይ "ከፍተኛ መሻሻል" መታየቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ተናገሩ።

ሩቢዮ፤ የዩክሬን እና አውሮፓ ተደራዳሪዎች በሲውዘርላድ ጄኒቫ ከተማ ካደረጉት ስብሰባ በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ነገር ግን "አሁንም፤ መከናወን ያለበት የተወሰነ ስራ አለ" ብለዋል።

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ በበኩላቸው "የፕሬዝዳንት [ዶናልድ] ትራምፕ ቡድን [የምንናገረውን] እያደመጠን ስለመሆኑ የሚያመለክቱ ፍንጮች" እንደነበሩ ገልጸዋል።

በአሜሪካ የተዘጋጀው እና ለሩሲያ ያደላ ተደርጎ የታየው የሰላም ስምምነት ዕቅድ ሾልኮ ከወጣ በኋላ ዩክሬን እና አውሮፓውያን አጋሮቿ ስጋታቸውን አሰምተዋል። የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ደግሞ ዕቅዱ ለሰላም ስምምነት "መሠረት" እንደሚሆን ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ፤ ዩክሬን "እጅግ ከባድ ምርጫን ልትጋፈጥ ትችላለች፤ ክብርን ማጣት ወይም ቁልፍ አጋርን የማጣት አደጋ [ያጋጥማታል]" በማለት እቅዱ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ሲገልጹ ተደምጠዋል።

ሩቢዮ፤ እሁድ ምሽት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በጄኔቫ የሚገኙት ተደራዳሪ ቡድኖች "በጣም ጥሩ ቀን" እንዳሳለፉ ተናግረዋል።

የንግግሩ ዋነኛ ዓላማ፤ 28 ነጥቦችን በያዘው የአሜሪካ የሰላም ዕቅድ ላይ የሚገኙ "ክፍት ጉዳዮችን" ለማጥበብ መሞከር እንደሆነ አስረድተዋል። በንግግሩ የተሳተፉ አካላትም ይህንን ግብ "ተጨባጭ በሆነ መልኩ" ማሳካታቸውን አስታውቀዋል።

አንድ ከፍተኛ የአሜሪካ ዲፕሎማት በበኩላቸው የትኛውም የመጨረሻ የስምምነት ሰነድ ወደ ሩሲያ ከመላኩ በፊት በዩክሬን እና አሜሪካ ፕሬዝዳንቶች ስምምነት ላይ ሊደረስበት እንደሚገባ አብራርተዋል። የሰላም ዕቅዱን ዝርዝር በተመለከተ አሁንም ቢሆን ሊሰራባቸው የሚገቡ የተወሰኑ ጉዳዮች እንዳሉም ጠቁመዋል።

አሜሪካ እና ዩክሬን ኋላ ላይ ባወጡት የጋራ መግለጫ፤ ሁለቱ አገራት "የተሻሻለው እና የተስተካከለው የሰላም ማዕቀፍን" በተመለከተ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታውቀዋል። "በመጪዎቹ ቀናት የጋራ ዕቅድ ላይ ከፍተኛ ስራ" እንደሚያከናውኑም ጠቅሰዋል።

በርካታ መገናኛ ብዙኃን በበኩላቸው በዩክሬን እና የአውሮፓ አጋሮቿ በሆኑት ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ጀርመን የተዘጋጀ አማራጭ የሰላም ዕቅድ መመልከታቸውን ዘግበዋል።

ቢቢሲ ይህንን ሰነድ አልተመለከተም፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩቢዮም ይህ ዓይነት ሰነድ መኖሩን አስተባብለዋል።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ፤ አሜሪካ ጦርነቱን ለመቋጨት ላደረገቻቸው ጥረቶች "አንድም ምስጋና" አላሳዩም ያሏቸውን የዩክሬን መሪዎችን እሁድ ዕለት ወቅሰዋል።

አክለውም የኪዬቭ ዋነኛ አጋሮችን የያዘችው አውሮፓ ከሩሲያ ነዳጅ መግዛት ቀጥላለች ብለዋል። ሩሲያ በዩክሬን የምታደርገውን ጦርነት ለማስቀጠል ዋነኛ የገንዘብ ምንጭ የሆናት ከነዳጅ እና ጋዝ ኤክስፖርት የሚገኝ ገቢ ነው።

በጄኔቫ ንግግር እየተደረገበት ያለው ረቂቁ የአሜሪካ የሰላም ዕቅድ፤ የዩክሬን ወታደሮች ራሳቸው ከሚቆጣጠሯቸውም ሆነ በሩሲያ ስር ካሉት የዶኔትስክ ግዛቶች ለቅቀው እንደሚወጡ የሚያደርግ ነጥብ ይዟል። ከሉሃንስክ ግዛት እና ሩሲያ በ2014 ገንጥላ ከወሰደችው የደቡባዊ ክሬሚያ ሰርጥም እንደሚወጡ አስፍሯል።

በከፊል በሩሲያ ቁጥጥር ስር ባሉት ደቡባዊ ኬርሶን እና ዘፖሪዣ ግዛቶች በኩል የሚገኘው ድንበር አሁን ባለው የጦር ግንባር መስመር መሠረት ባለበት እንዲቆይ የማድረግ ሀሳብም በእቅዱ ተካትቷል። በተጨማሪም በአሜሪካ ዕቅድ፤ በአሁኑ ሰዓት 880,000 የሚደርስ ብዛት ያለው የዩክሬን ሠራዊት ቁጥር ከ600,000 እንዳይበልጥ የማድረግ ሃሳብን አቅርቧል።