አዲሱን የዋይት ሐውስ የሰላም ዕቅድ የተቃወሙት ዜሌንስኪ፤ ዩክሬን የአሜሪካን ድጋፍ ልታጣ እንደምትችል ተናገሩ

የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎድሚር ዜሌንስኪ በአዲሱ የአሜሪካ የሰላም ዕቅድ ላይ ያላቸው ልዩነት ዋና አጋራቸው የሆነችው ዋሽንግተንን ድጋፍ ሊያሳጣቸው እንደሚችል ተናገሩ።

ሾልኮ የወጣው የአሜሪካ የሰላም ዕቅድ ዩክሬን ወታደሮች ሩሲያ ገንጥላ ከወሰደችው የክሬሚያ ሰርጥ እና ሌሎች የአገሪቱ ክፍሎች ለቅቀው እንደሚወጡ ይገልጻል።

ዜሌንስኪ አርብ ዕለት ለአገሪቱ ዜጎች ባስተላለፉት ንግግር ዩክሬን "እጅግ ከባድ ምርጫን ልትጋፈጥ ትችላለች፤ ክብርን ማጣት ወይም ቁልፍ አጋርን የማጣት አደጋ [ያጋጥማታል]" ብለዋል። አክለውም፤ "ዛሬ ታሪካችን ውስጥ ካሉ አስቸጋሪ ጊዜያት አንዱ ነው" ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን ያሉት አሜሪካ ጦርነቱን ለመቋጨት አቅርባዋለች የተባለ እና ዩክሬን ከዚህ ቀደም ውድቅ ያደረገቻቸውን የስምምነት ነጥቦች የያዘ የአሜሪካ የሰላም ዕቅድ ሾልኮ ከወጣ በኋላ ነው።

በሰፊው በተሰራጨው ዕቅድ ውስጥ ከተካተቱ ነጥቦች ውስጥ የዩክሬን ወታደሮች በአሁኑ ሰዓት ከሚቆጣጠሩት የአገሪቱ ምሥራቃዊ ግዛት ዶኔትስክ እንዲሁም በሩሲያ ቁጥጥርሥር ካሉት የግዛቱ ክፍሎች ለቅቀው ይወጣሉ የሚለው ይገኝበታል።

በተጨማሪም ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2014 ከዩክሬን ገንጥላ ከወሰደችው የደቡባዊ ክሬሚያ ሰርጥ ለቅቀው እንደሚወጡ አስፍሯል። ሉሃንስክ ተባለው ግዛትንም አሳልፎ መስጠት የሚል ነጥብ በዕቅዱ ላይ ተጠቅሷል።

በአሜሪካ የተዘጋጀው ዕቅድ፤ የዩክሬን ሠራዊት ቁጥር በከፍተኛ መጠን ቀንሶ ከ600,000 ሺህ እንዳይበልጥ የማድረግ ሀሳብን አካትቷል። የአውሮፓውያን ተዋጊ ጄቶችም በአጎራባቿ ፖላንድ እንዲሰፍሩ ይደረጋል።

በምላሹ ኪዬቭ "እውነተኛ የደህንነት ማረጋገጫ" እንደሚሰጣት በዕቅዱ ላይ ተጠቅሷል። ሰነዱ አክሎም፤ ሩሲያ ጎረቤቶቿን አትወርም ተብሎ "እንደሚጠበቅ" እንዲሁም ኔቶ ይዞታው እንደማያሰፋ ዘርዝሯል።

ሩሲያ "ወደ ዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ መልሳ እንደምትቀላቀል" ዕቅዱ ይጠቁማል። ይህም የሚደረገው በሩሲያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን በማንሳት እና የዓለም ኃያላን አገራት ስብስብ ወደሆነው ጂ7 ተመልሳ እንድትቀላቀል በማድረግ እንደሆነ ይጠቅሳል።

የእነዚህ የስምምነት ነጥቦች በእጅጉ ወደ ሩሲያ ፍላጎት ያጋደሉ ተደርገው ተወስደዋል። የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዕቅዱ ለሰላም "መሠረት" ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።

ፑቲን አርብ ዕለት ከካቤኔ ጽሕፈት ቤት ኃላፊያቸው ጋር ባደረጉት ስብሰባ ወቅት ሞስኮ ይህ ዕቅድ እንደደረሳት ገልጸዋል። በዕቅዱ ዝግጅት ሂደት ውስጥ የሩሲያ መንግሥት አልተወያየበትም ተብሏል።

ሩሲያ በጉዳዩ ላይ "መለሳለስ ለማሳየት" ፈቃደኛ እንደሆነች፤ በተቃራኒውም ለመዋጋት ዝግጁ እንደሆነች ተናግረዋል።

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ዜሌንስኪ ዕቅዱን "ሊወድደው ይገባል" ብለዋል። አለበለዚያ ዩክሬን እና ሩሲያ ውጊያውን እንደሚቀጥሉ አክለዋል።

ሩሲያ በአውሮፓውያኑ 2022 የፈጸመችውን ሙሉ ወረራ ጀምሮ ከሞስኮ ጋር ጦርነት ውስጥ ያለችው ዩክሬን፤ የውጊያ አቅሟ በከፍተኛ መጠን የተመሠረተው በላቁ አሜሪካ ሠራሽ መሣሪያዎች ላይ ነው። ዋሽንግተን ከባዱን የሩሲያ አየር ጥቃት መቀልበስ የሚያስችል የአየር መከላከያ ስርዓት እንዲሁም የስለላ መረጃ ለዩክሬን አቅርባለች።

ዜሌንስኪ በዋና ከተማዋ ኪዬቭ በሚገኘው የፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት ቆመው ባደረጉት የ10 ደቂቃ ንግግር፤ ዩክሬን "ከፍተኛ ግፊት" ሊያጋጥማት እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል። ይህ ግፊት "እኛን ለማዳከም፣ ለመከፋፈል [የሚደረግ ነው]" ያሉት ዜሌንስኪ፤ "ጠላት እየተኛልን አይደለም" ሲሉ ተደምጠዋል።

ዩክሬናውያን በአንድነት እንዲቆሙ ያሳሰቡት ፕሬዝዳንቱ፤ የአገሪቱ "ብሔራዊ ጥቅም ከግምት ውስጥ መግባት አለበት" ሲሉም በአጽንኦት ተናግረዋል።

"በተረጋጋ ሁኔታ ከአሜሪካ እና ከሁሉም አጋሮች ጋር እንሰራለን ... [ለሰላም ዕቅዱ] አማራጭ እናቀርባለን" ብለዋል።

ዜሌንስኬ፤ ከዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር፣ ከፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኤማኑኤል ማክሮን እና ከጀርመን ቻንስለር ፍሬድሪክ ሜርዝ ባደረጓቸው የስልክ ንግግሮች የአገራቱ ድጋፍ እንደሚቀጥል ማረጋገጫ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል።