ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ የዩክሬንን ጦርነት ለማስቆም የአሜሪካ ዕቅድ ለኪየቭ 'የመጨረሻው'' እንዳልሆነ ተናገሩ
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የሩስያ ዩክሬን ጦርነትን ለማስቆም ባቀረቡት ዕቅድ ላይ የዩክሬን አጋሮች ስጋታቸውን ከገለጹ በኋላ የአሜሪካ ዕቅድም "ሊቀየር ይችላል" አሉ።
ቅዳሜ ዕለት የአውሮፓ፣ የካናዳ እና የጃፓን መሪዎች ዕቅዱ "ፍትሐዊ እና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት አስፈላጊ ነገሮች" እንዳሉት ተናግረዋል፣ ነገር ግን በዩክሬን ጦር ላይ ስለሚደረጉ የድንበር ለውጦች እና ገደቦች ስጋታቸውን በመጥቀስ "ተጨማሪ ሥራ ያስፈልገዋል" ብለዋል።
ዛሬ እሑድ የብሪታንያ፣ የፈረንሳይ፣ የጀርመን፣ የአሜሪካ እና የዩክሬን የደኅንነት ባለሥልጣናት በጄኔቫ፣ ስዊዘርላንድ ይገናኛሉ።
ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘሌንስኪ ቀደም ሲል ዩክሬን ለሞስኮ ተስማሚ እንደሆነ የሚታየውን ዕቅድ እንድትቀበል የተደረገባትን ጫና ተከትሎ "በታሪካችን ውስጥ ካሉት እጅግ አስቸጋሪ ጊዜያት አንዱ" እንደገጠማት አስጠንቅቀዋል።
ትራምፕ ዩክሬን እስከ ኅዳር 18 ድረስ 28 ነጥቦች የያዘውን ዕቅድ እንድትቀበል ቀነ ገደብ ሰጥተዋል፣ የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ደግሞ ይህ ለስምምነት "መሠረት" ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።
ቅዳሜ ዕለት የአሁኑ ረቂቅ ዕቅድ ለዩክሬን የሚያቀርቡት የመጨረሻ ዕቅዳቸው ስለመሆኑ ሲጠየቁ ትራምፕ በዋይት ሀውስ "አይደለም፣ የመጨረሻው አይሆንም" ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
"በአንድ ወይም በሌላ መንገድ [ጦርነቱ] እንዲቆም ማድረግ አለብን፣ ስለዚህ በእሱ ላይ እየሠራን ነው" ሲሉም አክለዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ እና ልዩ ልዑክ ስቲቭ ዊትኮፍ እሑድ ዕለት በጄኔቫ በሚካሄደው ውይይት ላይ ከሚሳተፉት መካከል ይሆናሉ። የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጆናታን ፓውል በእንግሊዝ በኩል ይሳተፋሉ።
ቅዳሜ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን 20 ጉባኤ ላይ የወጣው የጋራ መግለጫው በካናዳ፣ በፊንላንድ፣ በፈረንሳይ፣ በአየርላንድ፣ በጣሊያን፣ በጃፓን፣ በኔዘርላንድስ፣ በስፔን፣ በእንግሊዝ፣ በጀርመን እና በኖርዌይ መሪዎች ተፈርሟል። ሁለት ከፍተኛ የአውሮፓ ኅብረት ባለሥልጣናትም ከፈረሙት መካከል ነበሩ።
መግለጫው እንዲህ ብሏል "ረቂቅ የሰላም ዕቅዱ ተጨማሪ ሥራ የሚፈልግ መሠረት ነው ብለን እናምናለን። የወደፊት ሰላም ዘላቂ እንዲሆን ለማድረግ ለመሳተፍ ዝግጁ ነን። ድንበሮች በኃይል መለወጥ የለባቸውም በሚለው መርሕ ላይ ግልጽ ነን።
"በተጨማሪም በዩክሬን የጦር ኃይሎች ላይ የተጣሉት ገደቦች ያሳስበናል፣ ይህም ዩክሬን ለወደፊት ጥቃት ተጋላጭ እንድትሆን ያደርጋታል።
አክሎም "ከአውሮፓ ኅብረት እና ከኔቶ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን መተግበር በቅደም ተከተል የአውሮፓ ኅብረት እና የኔቶ አባላትን ፈቃድ ይፈልጋል።"
በጆሃንስበርግ እየተካሄደ በሚገኘው የቡድን 20 ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ቅዳሜ ዕለት ከዘሌንስኪ ጋር በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ ትራምፕ ጋርም እንዲሁ በስልክ ተወያይተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት ቃለ አቃባይ ሰር ኪር ከትራምፕ ጋር በነበራቸው የስልክ ንግግር "ዛሬ በቡድን 20 ጉባኤ ላይ በተገኙት የበጎ ፈቃደኞች አጋሮች [የዩክሬን አጋሮች] መካከል የተካሄዱትን ውይይቶች አስተላልፈዋል" ብለዋል።
አክለውም፤ "መሪዎቹ በጄኔቫ በሚካሄደው ስብሰባ ላይ ባለ 28 ነጥብ የአሜሪካ የሰላም ሐሳብ ላይ አብረው ለመሥራት ተስማምተዋል። ነገ እንደገና ለመነጋገር ተስማምተዋል።"
ሰር ኪር ቀደም ሲል በዩናይትድ ስቴትስ ዕቅድ ውስጥ የዩክሬን ወታደራዊ ኃይል ላይ የቀረበውን ገደብ በተመለከተ ስጋት እንዳላቸው ተናግረዋል፣ "ዩክሬን የተኩስ አቁም ስምምነት ከተደረገ ራሷን መከላከል መቻል አለባት" ብለዋል።
ሾልኮ የወጣው የአሜሪካ የሰላም ዕቅድ የዩክሬን ወታደሮች በአሁኑ ጊዜ ከሚቆጣጠሩት ምሥራቅ ዶኔትስክ ክልል እንዲወጡ እንዲሁም በሩስያ ከተያዘችው በዶኔትስክ እንዲሁም በአጎራባችዋ ሉሃንስክ ክልል እና በ2014 በሩሲያ ከተያዘውን የደቡባዊ ክሪሚያ ባሕረ ገብ መሬት እንዲወጡ ሐሳብ ያቀርባል።
አርብ ዕለት ትራምፕ ዘሌንስኪ የአሜሪካን ሐሳብ "መቀበል አለበት" ሲሉ ተናግረዋል፤ አለበለዚያ ዩክሬን እና ሩሲያ ትግላቸውን ይቀጥላሉ ብለዋል።
ቀደም ሲል የዩክሬኑ መሪ አገሪቱ "በጣም አስቸጋሪ ምርጫ ሊያጋጥማት እንደሚችል፤ ክብር ማጣት ወይም ቁልፍ አጋር ማጣት አደጋ ላይ ልትወድቅ እንደምትችል" ለአገሪቱ በግልጽ በማስጠንቀቅ ተናግረዋል።
"ዛሬ በታሪካችን ውስጥ ካሉት በጣም አስቸጋሪ ጊዜያት አንዱ ነው" ሲሉ ዘሌንስኪ አክለውም በዕቅዱ ላይ ከአሜሪካውያን ጋር "በገንቢነት" ለመሥራት ቃል ገብተዋል።