ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የፌደራሉ መንግሥት እና የትግራይ አመራሮች በመቀለ በምን ጉዳዮች ላይ ተወያዩ?
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራው የመንግሥት ከፍተኛ የባለሥልጣናት ቡድን ትናንት ሰኞ ታኅሣሥ 17/2015 ዓ.ም. በመቀለ ተገኝተው ነበር።
የፌደራሉ መንግሥት ልዑካን አሉላ አባነጋ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የትግራይ አመራሮች እና የሃይማኖት አባቶች አቀባበል እንዳደረጉላቸው የክልሉ መገናኛ ብዙኃን ዘግቧል።
በፓርላማው አፈ ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ የተመራው ይህ የልዑካን ቡድን የኢትዮጵያ መንግሥት ተደራዳሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሑሴን እና የፍትህ ሚኒስትሩ አቶ ጌዲዮን ጢሞቴዎስን ጨምሮ ሰባት ሚኒስትሮችን እንዳካተተ የትግራይ ተደራዳሪ አምባሳደር ወንድሙ አሳምነው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በተጨማሪም የኢትዮቴሌኮም እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚዎች፣ የኢትዮጵያ መብራት ኃይል ኃላፊን ጨምሮ የባንክ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችም የተገኙ ሲሆን፣ ቁጥራቸውም አርባ እንደሚሆንም ተገልጿል።
በዚህ ደረጃ የፌደራሉ መንግሥት ልዑካን መላኩ “የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላም ሂደቱ ተፈጻሚነት እና ስምምነቱን ተግባራዊ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነት ያሳያል” ሲሉም አምባሳደር ወንድሙ ተናግረዋል።
መሠረታዊ አገልግሎቶችን በትግራይ የመመለስ ጉዳይ
በክልሉ ለረዥም ጊዜ ተቋርጠው የነበሩ የባንክ፣ የመብራት፣ የስልክ እና የትራንስፖርት አገልግሎቶችን ወደነበሩበት ለመመለስ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶችንም በተመለከተ ውይይት ተደርጓል።
የስልክ አገልግሎትም ለመጀመር በጦርነቱ የተጎዱ የፋይበር መስመሮች እየተጠገኑ ሲሆን፣ እስካሁን ባለውም 900 ኪሎሜትር መጠገኑን እና በቅርቡም እንደሚጠናቀቅ ልዑካኑ እንደነገሯቸው አቶ ወንድሙ አስረድተዋል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ የባንክ አገልግሎት እንደሚጀመር የገለጹት አምባሳደሩ፣ የባንክ አገልግሎቱንም ለማስጀመር 18 ያህል ባለሙያዎች በመቀለ ቀርተዋል ብለዋል።
ከቴሌኮሙዩኒኬሽን በተጨማሪ በረራዎችን የማስጀመሩ ሂደት ላይ ውይይት የተደረገ ሲሆን የልዑካኑ ጉዞ አላማም ተቋርጠው የነበሩ አገልግሎቶችን የመመለስ ተግባርን የማፋጠን ነው ብለዋል።
አምባሳደሩ በትግራይ በኩል የሰላሙ ስምምነት ላይ ያላቸውን እምነት እንደገለጹላቸውም ተናግረዋል።
መሠረታዊ አገልግሎቶችን የመመለስ የባለስልጣናቱ ዋነኛ የውይይት አጀንዳ ቢሆንም፣ በትግራይ ውስጥ አሁንም ያለው የኤርትራ ጦር የመውጣቱንም ጉዳይ መወያየታቸውን ገልጸዋል።
የኤርትራ ጦር መውጣትን በተመለከተ
ልዑካኑ በትግራይ የአገር ሽማግሌዎች እና የሃይማኖት አባቶችም ጋር በተነጋገሩበት ወቅት ያላቸውን ስጋት አንስተውላቸዋል ብለዋል።
“የኤርትራ ጦር እስካልወጣ ድረስ ዘላቂ ሰላም አይታሰብም። ይህንንም ተግባራዊ እንዲያደርጉም ነግረናቸዋል” ብለዋል።
የፌደራሉ መንግሥት ልዑካን ከትግራይ ክልል ፕሬዚዳንት ዶክተር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል ጋር በተወያዩበት ወቅት የኤርትራ ጦር እና የአማራ ክልል ኃይልን መውጣት አስፈላጊነትንም አጽንኦት ሰጥተው መናገራቸውን ጠቅሰዋል።
“ዋነኛው ጉዳያችን፣ የኤርትራ ኃይል፣ የአማራ ክልል ታጣቂዎች ናቸው። ብዙ ጉዳት፣ ግፍ እያደረሱ ነው። ተኩስ አቁሙ አላችሁን፣ የት አለ ታዲያ? ሙሉ አድርጉት። የውጭ ኃይል፣ የውጭ ወራሪ በትግራይ እየጨፈጨፈ ነው ያለው። ነገር ግን በበጎ ፈቃድ የመጣ ስለሆነ ህመም የሚፈጥር ነገር ነው። ማፍጠን አለብን። እንደዚህ ሆኖ መቀጠል አይቻልም። በሕዝባችንም ሆነ በሠራዊታችን ቁጭት አለ። ስምምነቱን ላለማበላሸት በሚል መስዋዕትነት እየከፈልን ነው” ሲሉ መናገራቸው በትግራይ ቴሌቪዥን በተላላፈው ዜና ተሰምተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራን እንዲሁም የአማራን ኃይል በቅርቡ እንደሚያስወጣም እምነታቸው መሆኑንም ገልጸዋል። ጉዳዩም ናይሮቢ ላይ በነበረው ውይይትም መነሳቱንም አምባሳደር ወንድሙ ጠቅሰዋል።
የትግራይ ኃይሎች ትጥቅ የመፍታት ጉዳይ
በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት እና በናይሮቢው የትግበራ ሰነድ መሠረት የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሣሪያ ማውረድ የሚካሄደው የውጭ እና የፌደራሉ መከላከያ ሠራዊት ያልሆኑ የክልል ኃይላት ከትግራይ በተመሳሳይ ወቅት ሲወጡ እንደሆነ ተጠቅሷል።
ይህንንም አስመልክቶ ትጥቅ የመፍታቱ ሂደት በምን ሁኔታ ላይ ነው? ሲል ቢቢሲ አምባሳደር ወንድሙን ጠይቋቸዋል።
እሳውም የእነዚህ ኃይሎች መውጣት ከትጥቅ መፍታት ጋር የተያያዘ አይደለም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
የትግራይ ኃይሎች የከባድ መሳሪያዎች በአንድ ስፍራ ተሰብስቦ ታዛቢዎች እንዲመለከቱት ይደረጋል። ቀላል መሳሪያዎችን (ትጥቅ መፍታትን) በተመለከተ አሁንም እየተነጋገሩ እንደሚገኙም ገልጸዋል።
ከባድ መሳሪያዎቹ የኤርትራ ጦር እና የአማራ ኃይል መውጣት ሲጀምር በተዘጋጀው ቦታ እንደሚያስቀምጡት የገለጹት አምባሳደሩ፣ ይህንንም በናይሮቢ ተወያይተናል ብለዋል።
ስለዚህ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እንደሚጀመር ቢያምኑም መዘግየቱንም ገልጸው፣ ከልዑካኑም ጋር እንደተወያዩ እና በቅርብም ተፈጻሚ እንደሚሆን መናገራቸውንም አስረድተዋል።
“የዘገየበትን ዝርዝር ምክንያቶች ያውቃሉ፤ እኛም የተወሰነውን እናውቃለን። ለሚዲያ ባናሳውቀው ይሻላል” ያሉት አምባሳደሩ ምክንያቱን ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል።
ሆኖም የኢትዮጵያ መንግሥት እነዚህን ኃይሎች በአስቸኳይ እንዲያስወጣቸው ጠይቀው “በቆዩ ቁጥር ከፍተኛ ጥፋቶች እየፈጸሙ ነው” ብለዋል።
ሆኖም ለአምባሳደሩ የልዑካኑ በመቀለ ያደረጉት ጉበኝት “የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲጀመሩ፣ የኤርትራ ጦር እና የአማራ ኃይል ለቀው እንዲወጡ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት የሚያረጋግጥ ነው ብለን እናምናለን። ተስፋም አድርገናል” ብለዋል።
መሠረታዊ አገልግሎቶችን መመለስ ለምን ዘገዬ?
በፕሪቶሪያ የተደረገው በዘላቂነት ግጭት የማስቆም ስምምነት ከተፈረመ ሁለት ወር ሊሞላው ተቃርቧል። በስምምነቱም መሠረታዊ አገልግሎቶች እንዲመለሱ እና የሰብዓዊ እርዳታም ያለ ገደብ እንዲገባ መደረግ ቢኖርበትም መዘግየቱ ተዘግቧል።
ቢቢሲም ለዚህ መዘግየት ምክንያቱ ምን እንደሆነና የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮች የሰጡት ምላሽ ምን እንደሆነ አምባሳደሩን ጠይቋቸው ነበር።
አምባሳደሩም “ችግሩ ግልጽ ነው። ደም አፋሳሽ በሆነ ጦርነት ለሁለት ዓመታት ያህል ቆይተናል። ይህንን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለማስቆም እና ወደ መደበኛ ግንኙነታችን ለመመለስ ስንሞክር ሂደቱ ቀላል ይሆናል ብለን አልጠበቅንም” ብለዋል።
ከስምምነቱ በኋላም የተቋረጡ መሠረታዊ አገልግሎቶች በተቻለ ፍጥነት እንዲጀመርም ፍላጎት እንደነበራቸው ጠቅሰው የተለያዩ ምክንያቶች አደናቅፈውታል ብለዋል። እንደ ምክንያትነት የጠቀሱት አንደኛው ጉዳይ ቴክኒካል ጉዳይ ነው።
ለምሳሌ የስልክ አገልግሎትን በመጥቀስ በጦርነቱ ምክንያት የወደመ ፋይበር መስመር እንዳለ እንደነገሯቸውና፣ ይህንንም በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርዝመት ያለውን መስመር ለመጠገን ጊዜ እንደሚወስድም እንደሚረዱም ገልጸዋል።
የስልክ አገልግሎቱም ካልተስተካከለ በስተቀር የባንክ አገልግሎቱ መጀመር እንደማይችል ገልጸው “ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት በሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች መዘግየቱ ምክንያታዊ ነው ብለን አናምንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በቅርቡም የፌደራሉ መንግሥት በሚቆጣጠራቸው በሽረ፣ በአላማጣ እና በኮረም ከተሞች የባንክ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታውቋል።
በእነዚህ ከተሞች የሚሰጠው አገልግሎት ከውጭ አገር እና ከአገር ውስጥ የሚላኩ ገንዘቦችን መቀበል እንደሆነና ከቁጠባ ገንዘብ ማውጣትም ሆነ ከሂሳብ ወደ ሂሳብ ማንቀሳቀስ እንደማይቻልም ተገልጿል።
ለዚህም መጀመሪያ ኦዲት መደረግ እንዳለበት እንዳብራሩላቸው አምባሳደር ወንድሙ ይናገራሉ። አጠቃላይ ያለው ሂደት ኦዲት ከተደረገ በኋላ ሰዎች ያላቸው ገንዘብ ተጣርቶ ሙሉ አገልግሎቱ እንደሚጀመርም ጠቅሰዋል።
ለባንክ አገልግሎት መጀመር ዋናው ጉዳይ ስልክ ሲቀጠል መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ነዋሪዎች እርዳታ ጠባቂ በሆኑባት ትግራይ ክልል ሰብዓዊ እርዳታ በተሻለ መንገድ እየገባ እንደሆነም ጠቅሰዋል።
ነገር ግን አሁንም ቢሆን ለክልሉ አፋጣኝ በሆነ ሁኔታ መግባት እንዳለበት የሚነገረው መድኃኒት በተገቢው መንገድ እየገባ እንዳልሆነ ጠቀሰዋል። ይህንንም ለልዑካኑ ማስረዳታቸውን ገልጸዋል።
ከመድኃኒት እጦት የተነሳ በርካታ ህፃናት እየሞቱ እንደሆነ በቅርቡ ቢቢሲ መዘገቡ ይታወሳል።