አስከፊው የአውሮፓ ሙቀት እየተስፋፋ ነው

በምዕራብ አውሮፓ የተከሰተው ኃይለኛ የሙቀት ማዕበል ወደ ሰሜን እየተስፋፋ ሲሆን በዛሬውም ዕለት አስከፊ ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል ማስጠንቀቂያዎች እየተሰጡ ነው።

ፈረንሣይ እና ዩናይትድ ኪንግደም በከፍተኛው የሙቀት ምክንያት ማስጠንቀቂያዎች የሰጡ ሲሆን ሰኞ ዕለት በሰሜናዊ ስፔን 43ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት መጠን መዝግቧል።

በፈረንሣይ፣ ፖርቱጋል፣ ስፔን እና ግሪክ የተቀሰቀሰው ሰደድ እሳት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤታቸውን ለቀው እንዲወጡ አስገድዷቸዋል።

ዩናይትድ ኪንግደም ከፍተኛው ሞቃታማ ቀን ታስተናግዳለች ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በአንዳንድ የፈረንሳይ ክፍሎች "አስከፊ ሙቀት” እንደሚገጥማቸው ባለሙያዎች ተናግረዋል።

በርካታ የፈረንሳይ ክፍሎች ከዚህ ቀደም አይተው የማያውቁትን ሙቀት አስመዝግበዋል። በምዕራባዊቷ ናንተስ ከተማ 42ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ መመዝገቡን ብሄራዊው የሜትሮሎጂ ቢሮ አስታውቋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት በተከሰተው ሰደድ እሳት ከ30 ሺህ በላይ ሰዎች ከቤታቸው ተፈናቅለው ወደ መጠለያ ጣቢያዎች እንዲገቡ ተገደዋል።

በጎብኚዎች ተመራጭ የሆነችው የደቡብ-ምዕራቧ ዢሮንድ ክፉኛ ተጎድታለችል። የእሳት አደጋ መከላከል ባለሙያዎች ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ ወደ 17 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ያወደመውን ቃጠሎ ለመቆጣጠር እየሠሩ ነው።

የዢሮንድ ክልል ፕሬዝዳንት ዣን ሉክ ግሌይዝ "ጭንቅላቴ ውስጥ የሚመጣው ሀሳብ ጭራቅ እንደሆነ ነው" ሲሉ ስለእሳቱ ተናግረዋል።

"እንደ ኦክቶፐስ ያለ ጭራቅ ነው። ከፊት እና ከኋላ በሁለቱም በኩል እየተስፋፋ ነው። በሙቀት፣ በነፋስ እና በአየር ውስጥ የውሃ እጥረት ምክንያት ጭራቁን ለመዋጋት በጣም ከባድ ሆኖብናል" ብለዋል።

ሰኞ ዕለት 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ አካባቢ የደረሰው የሙቀት መጠን ማክሰኞ እንደሚቀንስ ተነግሯል። ደረቃማ እና ተለዋዋጭ ነፋሶች እስካሉ ድረስ ግን ይህ ፈጣን እፎይታ ላያመጣ ይችላል ስትል የቢቢሲዋ ሉሲ ዊሊያምሰን በዢሮንድ ዘግባለች።

በዩናይትድ ኪንግደም ታሪክ ሰኞ ዕለት በጣም ሞቃታማ ከሆኑ ቀናት ውስጥ አንዱ ነበር። በምስራቅ እንግሊዝ በሱፎልክ ከፍተኛው 38.1 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሆኖ ተመዝግቧል። ትንበያዎች እንደሚያሳዩት ማክሰኞ ደግሞ ከ 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ እንደሚሻገር ይገመታል። ይህ ከሆነም በሃገሪቱ የተመዘገበው ከፍተኛው የሙቀት መጠን ይሆናል።

በዚህ ምክንያት ጉዞዎች ተስተጓጉለዋል። የባቡር ጉዞዎች የተሰረዙ ሲሆን የለንደን ሉተን አውሮፕላን ማረፊያ በረራዎች የአውሮፕላን ማኮብኮቢያው በከባድ ሙቀት በመመታቱ የጉዞ መስተጓጎል ተፈጥሮ ነበር።

ኔዘርላንድስ የዓመቱን ከፍተኛ ሞቃታማ ቀን ሰኞ ዕለት አስመዝግባለች። በደቡብ ምዕራብ ዌስትዶርፕ ከተማ የሙቀት መጠኑ 33.6 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ደርሷል።

በኔዘርላንድስ ደቡባዊ እና መካከለኛው ክፍሎች የሙቀት መጠኑ ወደ 39C ከፍ እንደሚል በመተንበዩ ማክሰኞ የበለጠ ሞቃት እንደሚሆን ይጠበቃል።

የአየር ሙቀት መጠኑ ወደ ሰሜን እያመራ መሆኑን ባለሙያዎች ገልጸዋል። ቤልጂየም እና ጀርመን በሚቀጥሉት ቀናት 40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሚደርስ የሙቀት መጠን እንደሚያስተናግዱ ይጠበቃል።

በስፔን እና ፖርቱጋል ባለፉት ቀናት ከ1,000 በላይ ሰዎች ከሙቀት ጋር በተያያዘ ለህልፈት ተዳርገዋል።

በፖርቹጋል ያለው የሙቀት መጠን ሐሙስ ዕለት 47 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ደርሶ ነበር። ይህም ለሐምሌ ወር ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቧል። አብዛኛው የሃገሪቱ ክፍል በብሔራዊ የአየር ትንበያ ቢሮ (አይፒኤምኤ) በከፍተኛ የእሳት አደጋ ስጋት ክልል ውስጥ ተካቷል።

የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን የሰሜናዊቷ ሙርካ ማዘጋጃ ቤት 300 ሰዎች በእሳት አደጋ ምክንያት ከአካባቢያቸው አስወጥቷል። ባለስልጣናት በአውሮፓውያኑ 2017 በተከሰተ ሰደድ እሳት 66 ሰዎች ህይወታቸው ያለፈበት ጊዜ እንዳይደገም ስጋት ገብቷቸዋል።

በስፔን ቢያንስ 20 እሳቶች ከቁጥጥር ውጪ እየነደዱ ነው። የፖርቹጋል ድንበር አቅራቢያ ሲጓዝ በነበረ ባቡር የተሳፈረ መንገደኛ ከባቡሩ በሁለቱም አቅጣጫ በነበረ እሳት ምክንያት ጉዞው መስተጓጎሉን የሚያሳይ ቪዲዮ ቀርጾ አሰራጭቷል።

የሰው ልጅ በሚፈጥረው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሙቀት ሞገዶች በጣም ተደጋጋሚ፣ የበለጠ ኃይለኛ እና ረዘም ያለ ጊዜ የሚቆዩ ሆነዋል።

የኢንዱስትሪ ዘመን ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ዓለምበ1.1 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ገደማ ሞቃለች። መንግስታት ከፍተኛ የሆነ የልቀት መጠንን ካልቀነሱ በስተቀር የሙቀት መጠኑ እየጨመረ ይሄዳል።