እውቋ ደቡብ አፍሪካዊት ዘማሪ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋች የነበረውን ፍቅረኛዋን አስገድላለች ተባለ

እውቋ ደቡብ አፍሪካዊት ዘማሪ ኬሊ ኩማሎ ፍቅረኛዋ የነበረውን የብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ሴንዞ ሜይዋ ማስገደሏ ተገለጸ።

እአአ በ2014 ከ10 ዓመታት በፊት በመሣሪያ የተደገፈ ዝርፊያ በሚፈጸምበት ወቅት ንዞ ሜይዋ ፍቅረኛውን ለመከላከል ጥረት ሲያደርግ ተገድሎ ነበር።

ይሁን እንጂ መርማሪዎች ግብ ጠባቂው የተገደለው በዘርፊያ ሳይሆን ዘማሪዋ ፍቅረኛዋን ለማስገደል ከገዳዮቹ ጋር ውል ገብታ ነው ሲሉ ለፍርድ ቤት ተናግረዋል።

ይህ ወንጀል ከተፈጸመ ከ6 ዓመታት በኋላ እአአ 2020 ላይ በወንጀል ደርጊቱ የተጠረጠሩ አምስት ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ ሲደረግባቸው ቆይቷል።

ዋና መርማሪ ቦንጋኒ ጊኒንዳ ለጋውቴንግ ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደገለጹት ዘማሪት ኩማሎ የቀድሞ ፍቅረኛዋ “በክፍያ እንዲገደል” አስተባብራለች።

ጉዳዩን በተመለከተ ከቢቢሲ ለቀረበ ጥያቄ የዘማሪዋ ቃል አቀባይ ኩማሎ አስተያየት መስጠት እንደማትችል ነገር ግን “የሕግ ቡድኗ ሁኔታውን እየተከታተለው መሆኑን” ገልጿል።

"በሕጋዊ ሂደቱ ላይ እምነት እንዳላቸውም" ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ብሔራዊ እግር ኳስ ቡድን አምበል እና የኦርላንዶ ፓይሬትስ ግብ ጠባቂ ግድያ በደቡብ አፍሪካ ትልቅ ድንጋጤን ፈጥሮ የነበረ ሲሆን የክስ ሂደቱም የበርካቶችን ቀልብ ስቧል።

እአአ በ2020 ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተከትሎ የፖሊስ ሰነዶች ሾልከው መውጣታቸውን ተከትሎ ነበር ኩማሎ ተጠርጣሪ መሆኗ የታወቀው።

ዘማሪዋ ስለ አምስቱ ግለሰቦች “ምንም እውቀት እንደሌላት” በወቅቱ ጠበቃዋ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።

ጊኒንዳ ለፍርድ ቤቱ እንደተናገሩት ከተጠርጣሪዎቹ አንዱ በሰጠው የእምነት ክህደት ቃል ሜይዋን እንዲገድሉ ኩማሎ መመሪያ እንደሰጠቻቸው ተናግሯል።

መርማሪው አክለውም ኩማሎ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር "የስልክ ግንኙነት" ነበራት።

ብሔራዊ የግድያ ወንጀሎች ምርማሪ ቡድን ባልደረባ የሆኑት ኮሎኔል ላምበርተስ ስቴይን ባለፈው ዓመት እንደገለጹት ሜይዋ ከመገደሉ በፊት ኩማሎ ከተጠርጣሪዎቹ ጋር ቢያንስ ሁለት ጊዜ እንደተገናኘች መስክረዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ኩማሎ በስልኳ ላይ ቦርሳ ውስጥ ያለ ገንዘብ የሚያሳይ ፎቶ የነበራት ሲሆን ተመሳሳይ ምስል ከተጠርጣሪዎቹ በአንዱ ስልክ ላይ ተገኝቷል።

ፍርድ ቤቱ የእምነት ክህደት ቃሉ ተቀባይነት ያለው መሆን አለመሆኑን በማረጋገጥ ላይ ይገኛል። ከተጠርጣሪዎቹ መካከል ሁለቱ የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡት በግዳጅ መሆኑን ተናግረዋል።

ኩማሎ እና ሜይዋ አንድ ልጅ ነበራቸው።

በኋላ ላይ ጥንዶቹ መለያየታቸውን ጊኒንዳ ተናግረዋል ።

ኩማሎ "ትጠላው እና እንዲወገድ ትፈልግ ነበር" ብለዋል።

እአአ በ2013 መጀመሪያ ላይ በኩማሎ እና በእህቷ መካከል በነበረው “የመልዕክት ልውውጥ” እሱን ልታስወግድ እንደምትፈልግ ያሳያል ሲሉም አክለዋል።