የዊልያም ሩቶ ፕሬዝዳንትነት በኢትዮጵያ እና በኬንያ ግንኙነት ላይ ለውጥ ያመጣ ይሆን?

ኬንያ በነሐሴ ወር መጀመርያ ላይ ባካሄደችው አገራዊ ምርጫ አዲስ ፕሬዝዳንት አግኝታለች።

ይህ ምርጫ አገሪቱ በ1963 ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት ጊዜ ጀምሮ ሲቆጠር ለአምስተኛ ጊዜ የተካሄደ ነው።

በዚህ ምርጫ ጠንካራ ተፎካካሪ የነበሩትን ራይላ ኦዲንጋን በማሸነፍ ዊሊያም ሩቶ የፕሬዝዳንትነት መንበሩ ላይ ተቀምጠዋል።

ከ2013 (እኤአ) ጀምሮ ለአስር ዓመት ያህል ኬንያን ሲያስተዳድሩ የቆዩት ኡሁሩ ኬንያታ የፕሬዝዳነትነት ዘመናቸውን አጠናቅቀው የፕሬዝዳነትነት መንበሩን ለአዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ነገ፣ ማክሰኞ ያስረክባሉ።

ዊሊያም ሩቶ ስልጣናቸውን የሚረከቡት የትግራይ ኃይሎች በአፍሪካ ሕብረት መሪነት የሚደረገውን ድርድር በተቀበሉበት ማግስት ነው።

ለመሆኑ የሩቶ ፕሬዝዳንትነት በኢትዮጵያ እና በኬንያ መካከል ያለው ግንኙነት ላይ ለውጥ ያመጣ ይሆን?

የኢትዮ ኬንያ ግንኙነት

ኬንያ እኤአ በ1963 ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣች ጀመሮ ሁለቱ አገራት ጠንካራ የፀጥታ እና የምጣኔ ሃብት ግንኙነት አላቸው።

ኢትዮጵያ ከኬንያ ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነት የጀመረችው በ1945 እኤአ በናይሮቢ የቆንስላ ቢሮ በመክፈት እንደሆነ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዚህ ዙሪያ የሰሩት መለሰ ዘለቀ ይናገራሉ።

አቶ መለሰ በጥናታዊ ጽሁፋቸው ላይ የሁለቱ አገራት ግንኙነት በሰላምና ፀጥታ ዙሪያ ላይ ያነጣጠረ ነበር።

የምስራቅ አፍሪካ ጉዳዮች ተንታኝ የሆኑት አብዱላሂ ቦሩ፣ ደግሞ “ሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ከሌሎች አገራት ይልቅ በጣም ጠንካራ ነው” ይላሉ።

በተመሳሳይ ሁኔታ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት ባጫ ደሌ፣ ሁለቱ አገራት ጣልያን ኢትዮጵያን ከወረረችበት ጊዜ ጀምሮ ጠንካራ ግንኙነት አላቸው ብለዋል።

“ከኬንያ ጋር ልዩ የሆነ ግንኙነት አለን። ይህንን ግንኙነት የጀመሩት አባቶቻችን ናቸው። በንጉስ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግሥት አርበኞቻችን የሸሹት ወደ ኬንያ ነው።”

“እነርሱም ደግሞ የእኛን አርበኞች አስተናግደው፣ አስታጥቀው ወደ ኢትዮጵያ ሸኙ። ኬንያኖችም ከቅኝ ግዛት ለመላቀቀቅ በሚያደርጉት ትግል ውስጥ የእኛ መንግሥትም አግዟቸዋል። ስለዚህ የሁለቱ አገራት ግንኙነት ልዩ ነው።” ይላሉ አምባሳደር ባጫ።

አብዱላሂ ቦሩ በበኩላቸው ኬንያ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት ጊዜ በኋላ ከኢትዮጵያ ጋር በፍጥነት የጦርነት እና የሰላም ጉዳዮችን በሚመለከት ስምምነት እንዳደረገች ይናገራሉ።

ሁለቱ አገራት ይህንን ስምምነት ያደረጉት ከሶማልያ በኩል የጋራ የደህንነት ስጋት ስለነበራቸው ነው።

በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩ እና አሁን ደግሞ በውጪ ጉዳይ ሚኒስትር የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ዳይሬክተር የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ “የኢትዮጵያ እነ የኬንያ ግንኙነት ታሪክ ለብዙ ዓመታት የቆየ ነው” ይላሉ።

ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር ከሶማልያ፣ ኤርትራ፣ እና ሱዳን ጋራ በተለያየ ደረጃም ቢሆን ግጭት ውስጥ አልፋለች።

ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር እስከ 2018 በግጭት ውስጥ ነበረች።

በ1977 የዚያድባሬ መንግሥት ኢትዮጵያን ሲወር ከሶማሊያ ጋር ጦርነት ውስጥ ገብታ ነበር።

ከሱዳንም ጋር ቢሆን ከፍተኛ ጦርነት ውስጥ ባይገቡም በድንበር እና በአባይ ግድብ ምክንያት መለስተኛ ግጭቶች እና ኩርፊያ አለ።

ኬንያ እና ኢትዮጵያ ግን በድንበር አካባቢ ያሉ ሕዝቦች አልፎ አልፎ ከሚጋጩት በስተቀር በአገር ደረጃ ጠብ ውስጥ ገብታ እንደማታውቅ አምባሳደር ዲና ይናገራሉ።

በኬንያ ናይሮቢ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለቤተ መንግሥቱ ያለው ቅርበት

በኬንያ ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ኬንያ ውስጥ ከተከፈቱ የአገራት ኤምባሲዎች መካከል ቀደምት የሚባለው ነው።

ይህ ብቻም ሳይሆን ኬንያ ውስጥ ከሚገኙ ኤምባሲዎች ለኬንያ ቤተ መንግሥት በጣም ቅርብ የሆነው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ብቻ ነው።

ይህ የሆነው ዝም ብሎ ሳይሆን፣ ታስቦበት እንደሆነ አምባሳደር ዲና ይናገራሉ።

“ጆሞ ኬንያታ እርስዎ ከእዚህ መራቅ የለባችሁም እዚሁ አጠገባችን መሆን አለባችሁ ብሎ ቤተመንግሥቱ አጠገብ የኢትዮጵየ ኤምባሲ እንዲሆን ቦታ ሰጡ” ይላሉ አምባሳደር ዲና።

እርሱ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያ አምባሳደር መኖርያ ቤት እዚያው ቤተ መንግሥት አጠገብ የሚገኘው ኤምባሲ ግቢ ውስጥ ይገኛል።

ኬንያ ከቅኝ ግዛት ነጻ ከወጣችበት አንስቶ የኬንያው የመጀመርያ ፕሬዝዳንት ጆሞ ኬንያታ ንጉስ ኃይለ ስላሴ ቅርብ ጓደኛሞች ነበር።

የቀድሞው የአፍሪካ ሕብረት የአሁኑ የአፍሪካ አንድነት በ1963 እኤአ፣ ሲመሰረት የሁለቱ አገራት መሪዎች ድርሻቸው ከፍተኛ ነበር።

“ጆሞ ኬንያታ እና ኃይለ ስላሴ ጥሩ ግንኙነት ነበራቸው። አብረው ይገናኛሉ፤ ይመካከራሉ። ከእነርሱ በኋላ የመጡ የሁለቱ አገራት መሪዎች እስካሁን ድረስ ጥሩ ግንኙነት ነው ያላቸው” ይላሉ አምባሳደር ዲና።

በኬንያ አዲስ ፕሬዝዳንት መመረጥ

በኬንያ የዊሊያም ሩቶ ፕሬዝደንት ሆኖ መመረጥ ለኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚ መሆኑን አንዳንዶች ይናገራሉ።

ህወሓት በአፍሪካ ህብረት መሪነት የሚደረግ ድርድርን እንደሚቀበልና በአስቸኳይ ጦርነት ቆሞ ወደ ድርድር ለመግባት መዘጋጀቱን አስታውቋል።

 ህወሓት ቀደም ሲል የአፍሪካ ሕብረትን አደራዳሪነት ገለልተኛ ስላልሆነ አልቀበልም ብሎ ነበር።

በምትኩም ተሰናባቹ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ እንዲያደራድሩት ሲጠይቅ ቆይቷል።

ኢትዮጵያ የኬንያን አሸማጋይነት ትታ የአፍሪካ ሕብረትን መምረጧ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ግንኙነት ጥሩ አለመሆኑን ያሳያል የሚሉ አሉ።

ስለዚህ በኬንያ ዊሊያም ሩቶ አዲስ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው ጥሩ አጋጣሚ ነው ይላሉ።

የአፍሪካ ቀንድ ተንታኝ የሆኑት አብዱላሂ ቦሩ ግን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም።

“ዊሊያም ሩቶ ፕሬዝዳንት መሆናቸው በሁለቱ አገራት ግንኙነት ላይ ምንም ለውጥ አያመጣም።” አክለውም

“የኬንያ የውጪ ግንኙነት ዲፕሎማሲ አንድ ሰው ፕሬዝደንት መሆን እና አለመሆን ላይ የሚመሰረት አይደለም። ኬንያ በውጪ ግንኙነት ፖሊሲ ውስጥ በአገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አትገባም” ይላሉ።

የአፍሪካ ሕብረት አልያም የኡሁሩ ኬንያታ አሸማጋይነትን አስመልክቶም “ህወሓት ኬንያ ለማንም እንደማታዳላ ስለሚያውቁ ኡሁሩን ይመርጣሉ። የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ የአፍሪካ ሕብረትን ማሳመን ስለሚቀለው አፍሪካ ሕብረትን መረጠ እንጂ ከኬንያ ጋር ቁርሾ ውስጥ ስለገቡ አይደለም” ይላሉ አቶ አብዱላሂ።

አምባሳደር ዲና በበኩላቸው ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ድርድሩን እንዲመራ መጠየቋ ኦባሳንጆ አንደጀመሩ ይጨርሱ ማለቷ እንጂ ኡሁሩ ኬንያታ ተጨማሪ ሆነው ቢመጡ ምንም ችግር እንደሌለባት ይናገራሉ።

“ኢትዮጵያ ከኬንያ ይልቅ የአፍሪካ ሕብረትን መምረጧ የሆነ ግርታ ፈጥሮ ካልሆነ በስተቀር በግልጽ የፈጠረው ችግር ምንም የለም።”

ፕሬዝዳነት ኡሁሩ ኬንያታ አገራችው ባደረገችው ፕሬዝዳነታዊ ምርጫ ወቅት የራይላ ኦዲንጋ ደጋፊ ነበሩ።

ነገር ግን ፕሬዝዳነት ኡሁሩ እንደተመኙት ሳይሆን ተቀናቃኛቸው ዊሊያም ሩቶ አሸንፈዋል።

“የኡሁሩ ምርጫ የሆነው ኦዲንጋ በምርጫ መሸነፋቸው ምናልባት፣ የኡሁሩ ኬንያታ አሸማጋይነት ላይ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል” ይላሉ አብዱላሂ ቦሩ።

“ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ በኡሁሩ አሸማጋይነት ላይ ጥያቄ ሊኖራቸው ይችላል። ይሁን እንጅ የሁለቱ አገራት ግንኙነት በተለመደው መልኩ በሰላም እየሄደ ነው” ይላሉ አቶ አብዱላሂ።

በናይሮቢ ዩኒቨርስቲ የሚያስተምሩት ፕሮፌሰር ፒተር ፓጉዋንጃ በበኩላቸው ኬንያ አዲስ ፕሬዝደንት ማግኘቷ በሁለቱ አገራት ላይ የሚያመጣው ለውጥ አለመኖሩን ይናገራሉ።

አዲስ የተመረጡት ዊሊያም ሩቶ “ለ10 ዓመታት የኡሁሩ ምክትል ሆነው ስላገለገሉ የኬንያ የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ የሚያመጡት ምንም ለውጥ አይኖርም” ይላሉ ፕሮፌሰር ፒተር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይን እና ኡሁሩ ኬንያታ

ዊሊያም ሩቶ አምስተኛ የኬንያ ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ ቀድመው የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ከላኩ አገራት መካከል አንዷ ኢትዮጵያ ነች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ዊሊያም ሩቶ ፕሬዝዳንት መሆናቸው ሲነገር የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት መላካቸው ሌላ ትርጉም አለው ወይስ የአጋጣሚ ነው ስንል የምስራቅ አፍሪካ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ተንታኙን ጠይቀናቸው ነበር።

አብዱላሂ ቦሩ ዐብይ ያደረገው መልካም ግንኙነት ያላቸው የሚያደርጉትን እንጅ የተለየ ነገር እንዳልሆነ ይናገራሉ።

“ይሁን አንጂ ሁለቱ መሪዎች የወንጌላውያን አማኞች ስለሆኑ ግንኙነታቸውን እንዲያጠናክሩ ዕድል ይከፍትላቸዋል” ሲሉ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

“በሁለቱ መሪዎች ደረጃ መልካም ግንኙነት ካለ ኢትዮጵያ በኬንያ አሸማጋይነት ላይ ያላት ጥርጣሬ እንዲቀንስ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያም መልካም ነው” ሲሉ ያክላሉ አቶ አብዱላሂ።

ፕሮፌሰር ፒተር በዚህ ሃሳብ የሚስማሙ ሲሆን፣ ኬንያ ለአሸማጋይነት ምቹ መሆኗንም ይጨምራሉ።

“ኬንያ የተመድ ፀጥታው ምክር ቤት አባል ስለሆነች እና የምዕራባውያን ዲፕሎማሲ ድጋፍ ስላላት ይህንን የሰላም ድርድር ለማሸማገል ብቁ ነው የምትሆነው።”

አምበሳደር ዲና ግን “ እኛ ጉዳያችን እዚሁ በአፍሪካ ሕብረት እንጨርሳለን። ጉዳዩ የተጀመረው በአፍሪካ ሕብረት በመሆኑ በእርሱ ይለቅ ብለን እንጂ ከኬንያ ጋር ምንም ችግር የለብንም” ይላሉ።

ፕሮፌሰር ፒተር ሁለቱ የሚዋጉ ኃይላት በኬንያም ሆነ በዊሊያም ሩቶ እምነት ስላላቸው ናይሮቢ ድርድሩን ለመመምራት አቅም አላት።