ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አዲሱን ዓመት በምን እንቀበለው?
ሄቦ - ግጭት የሚፈታበት፣ ሰላም የሚሰፍንበት እንዲሁም በድብቅ የተሰሩ ወንጀሎች የሚጋለጥበት ሥርዓት ነው።
ሄቦ - በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከሚገኙ ማኅበረሰቦች አንዱ የየም ማኅበረሰብ ዘመን መለወጫን የሚቀበልበት ሥነ ሥርዓት ነው።
ከትውልድ ትውልድም ማኅበረሰቡ ዘመን መለወጫን በዚህ ሥርዓት ይቀበላል፤ በማኅበረሰቡ ያሉ ግጭቶችን ፈትቶ አዲሱ ዓመት በሰላም እንዲጀመር ያደርጋል።
በተሰናባቹ ዓመት ደም አፋሳሽ በሆነ የርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ባለችው ኢትዮጵያ፣ እንደ ሄቦ ያሉ አገር በቀል የግጭት አፈታት መንገዶች ተግባራዊ ቢሆኑስ? የሚለው ሌላ ጥያቄ ቢሆንም፤ ሞት ተራ በሆነበትና ግጭቶች የተለመደ የሕይወታችን አካል በሆነበት በአሁኑ ወቅት በርካቶች ሰላምን አጥብቀው እየተመኙ ይገኛሉ።
በተለይም አሮጌውን ዓመት ተሰናብተን አዲሱን ዓመት ስንቀበል ብሩሁን መመኘት የሕዝቡ ባህልና ልምድ አካል ከመሆኑ አንፃር በአገሪቱ ሰላም ይስፈን የሚሉ ጥሪዎች በዝተዋል።
ከጦርነት በተጨማሪ ድርቅ ባስከተለው ችግር በረሃብና በጠኔ በሚሰቃዩበት ሁኔታ "መጪው ዘመን፣ 2015 ዓ.ም መልካም ዜና የምንሰማበት ይሁን" የሚሉ ምርቃቶች ከበርካቶች ዘንድ ይሰማሉ።
ያጠላው የጥላቻ ደመና እንዲገፈፍ፣ በርካቶች እንባቸውን የሚያብሱበት፣ የሐዘን ቁስሉ የሚጠግግበት፣ ጠባሳው የሚሽርበት እንደ አገርም አዲስ ተስፋና ህልም የሚሰነቅበት ዘመን እንዲሆንም ምኞታቸውንም እያስተላለፉ ነው።
የዘመን መለወጫ፣ እንቁጣጣሽ የክረምት ወር ተጠናቆ ደመናው የሸፈናት ፀሐይ ሙሉ በሙሉ ብርሃኗ የሚገለጥበት፣ ሜዳዎች፣ ተራራዎችና ሸለቆዎች በአበባ የሚያሸበርቁበትና የሚንቆጠቆጡበት ወቅት ነው።
የወቅቱ መለወጥና ብሩህ መሆን ብቻ ሳይሆን መጪው ዘመን የሰላም፣ የፍቅር፣ የደስታ እንዲሆንም በበርካታ አገራት የሚደረጉ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ ባህላትና ልምዶች አሉ።
የነብር ዘመንን የያዙት ቻይናውያን በዘመን መለወጫ ክፉ መንፈስን ለማስፈራራት፣ ቀይ ወረቀት ያሳያሉ፤ ቀርቀሃ ያቃጥላሉ፤ ሻማ ያበራሉ እንዲሁም ቀይ ልብስ ይለብሳሉ።
የቡድሂስት ዘመንን የሲንሃሌዝ አቆጣጠርን ለሚከተሉ ሲሪላንካውያንም መጪው ዘመን የብልፅግና እንዲሆን ወተት በማፍላት፣ እንዲሁም በካህኖቻቸው አማካኝነት ቅባት ግንባራቸው ላይ ይቀባሉ።
ኢትዮጵያ ውስጥም እርቅ፣ ሰላም፣ ተስፋ፣ ጤና በግልም፣ በቤተሰብም ሆነ በሕዝብ ዘንድ እንዲመጣ በርካታ ልምዶችና ባህሎች ይከናወናሉ።
እነዚህ ልምዶች ከሥፍራ ሥፍራ፣ በዓመታት ውስጥ ተለዋዋጭ ቢሆኑም የተወሰኑትን አመጣጣቸውንና ምክንያታቸውን እንዳስስ።
ጳጉሜ ላይ መታጠብ
ከእንቁጣጣሽ፣ ዘመን መለወጫ በፊት የሚውሉት የጳጉሜ ቀናት፣ መጪውን ዘመን የሚያበስሩ ተደርገው ይታያሉ።
ለዘመናትም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አስራ ሦስተኛዋን ወር፣ ጳጉሜን በመታጠብ ለእንቁጣጣሽ ዝግጅት ይደረግበታል።
ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣው ትውፊት፣ ውሃው ፈውስን እንደሚያመጣና ራስንም ከአካላዊ ብቻ ሳይሆን ከውስጥም ለማንጻት ይጠቅማል ይላሉ።
በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎችም ወደ ወራጅ ወንዝ በመሄድ ለቀናት ይታጠባሉ።
ወንዝ ባይሆንም በየትኛውም ውሃ በመታጠብ ያለፈውን ዓመት ዕድፍ ከአካል አስወግዶ አዲሱን ዓመት በንጻት ይጀምራሉ።
በህመምም ሆነ በእርጅና አልጋ ላይ የዋሉ ቢሆን እንኳን በሸክም ወደ ወንዝ ይወሰዳሉ። ካልሆነ ግን ውሃ እያመጡ እንደሚያጥቧቸው ዶ/ር ሀብተማርያም አሰፋ 'የኢትዮጵያ ታሪክ ጥያቄዎችና ባህሎች' በሚለው መጽሐፋቸው አስፍረውታል።
ሕዝቡ ወንዝ እየወረደ በውሃ እየታጠበ ሲነጣ ከሰነበተ በኋላ የእንቁጣጣሽ ዋዜማ ዕለት የተቀያየሙ ካሉ ይቅር በመባባል ታርቀው ያለ አንዳች ቅሬታ ከቂም በቀል ንጹህ ሆነው ለእንቁጣጣሽ አዲስ ዓመት ይዘጋጃሉ።
መጥፎ መናፍስትና አጋንንት በሰው ላይ አድረው ክፉ ሥራ ስለሚያሰሩ በሽታና ችግርም ያመጣሉ የሚል እምነት ስለነበረም በውሃ እጥበትና እርስ በርስ ይቅር በመባባል ሊወገዱ ይችላሉ የሚል እምነት እንደነበራቸውም ያስረዳሉ።
ከክርስትና ጋር በተያያዘ ደግሞ በበርካታ ደዌ የቆሰለው ኢዮብ የተፈወሰው በዚህ ወቅት በመታጠብ ነው በሚል ያንንም ምሳሌ በማድረግ በርካቶች በመታጠብ ከህመማቸው ለመፈወስም ይረዳናል ይላሉ።
በአንዳንድ አካባቢዎች በተለይም በከተሞች ያሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች ወደ ጸበል የሚሄዱ ሲሆን፣ ህፃናት ደግሞ በበኩላቸው በዝናብ ውሃ በመታጠብና በመንቦራጨቅ ቀናቱን ያሳልፋሉ።
የፌጦ ፍትፍት
መስከረም አንድ ተብሎ ጥዋት ሲበሰር በርካቶች ማልደው ፌጦ መላ ቤታቸውን ይረጫሉ።
ፌጦ ተደቁሶ በውሃ ተበጥብጦ ትንሽ ሎሚ ይጨመርበትና መላው ቤቱን ከመርጨት በተጨማሪ በእንጀራ ተፈትፍቶ በባዶ ሆድ ይጎረሳል።
ለዓመታት ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ እንደመጣ የነገሩን በአምሳዎቹ እድሜ የሚገኙት ወይዘሮ አበባ እንደሚሉት በዋነኝነት የሰው እጅ የተደረገበት ካለ በሆድ ውስጥ ያለውን እጥብ አድርጎ ያስወግደዋል።
በባለፈው ዓመት በምቀኝነትና በጥላቻ የሰው እጅ የዋለበት ካለ "ፌጦ ፍቱን መድኃኒት ነው፤ ይፈታዋል" ይላሉ።
በዶ/ር ሃብተ ማርያም ጽሁፍ ላይ ስለ ፌጦ የተጠቀሰው ደግሞ በየቤቱ ብቻ ሳይሆን በየመንደሩም የሚረጭ ሲሆን፣ ለዚህም ክፉ መንፈሶች ይወገዳሉ የሚል እምነት በሕዝቡ ዘንድ ስለሰፈነ ነው ይላሉ።
ዛር፣ ቆሌና ሌሎች መንፈሶችንም ያስወግዳል በሚል በገጠሪቷ ኢትዮጵያ የተዘራ እህልም ላይ የሚረጭ ሲሆን አውድማው የተረጨበትን ፌጦ የያዘው ዕቃ እህሉ ተወቅቶ ተመርቶ እስኪነሳ ድረስ በዚያው አጠገብ ይቀመጣል።
በዚህም መንደሩ ንጹህ ይሆናል የሚዘራውም እህል በደንብ በቅሎ ለፍሬ እንዲደርስ ለማድረግ ነው።
ሌሎች ደግሞ በዝናብ ወቅት በርካታ በሽታዎች ስለሚስፋፉ ያንን ለማጥፋት ፌጦ እንደ ባህል መድኃኒትነት ስለሚታይ ጥቅም ላይ ይውላል።
ፌጦ ጸረ- ባክቴሪያ ንጥረ- ነገሮች እንዳሉት የምግብ ሳይንስ ባለሙያዎች የሚናገሩ ሲሆን፣ አሁን ባለው በተወሰነ ደረጃ በዐይን የማይታዩ ተህዋስያንን ያጠፋል ይላሉ።
የእንስሳት እርድ
በዘመን መለወጫ ልጃቸውን ለመጠየቅ ውጭ አገር የሄዱ እናት ልጃቸው የዶሮ፣ የበግ ሥጋ ቢገዛላቸውም በአዲስ ዓመት እርድ ሲታረድ ባለማየታቸው ራሳቸውን አሟቸው እንደተኙና ዶሮ ሲታረድ እንደነቁ በወሬ ወሬ ሲነገር ይሰማል።
ይህ ብቻ አይደለም በተለይም በቀድሞ ጊዜ ውጭ አገር የሄዱ ሰዎች፣ አገራቱ በየቤቱ እርድ ማድረግ አይቻልም የሚሉ መመሪያዎች ተላልፈው ሲያርዱ ተገኝተው ታሰሩ ሲባል ይሰማ ነበር።
ተደብቀው የሚያርዱ እንዳሉና አንዳንዶችም ገጠር ሄደው እንደሚያሳርዱ ይወራል።
እነዚህ ወሬዎች እውነትነታቸው ባይታወቅም ምን ያህል እርድ በበዓላት ወቅት ስር የሰደደ መሆኑም ማሳያ ናቸው።
ኢትዮጵያውያን በእንቁጣጣሽ እንደ አቅማቸው ዶሮ፣ በግ ወይም በቅርጫም ቢሆን የበሬ ሥጋቸውን በመጫረት ክብረ በዓሉን ያደምቁታል።
የሽንኩርቱ ቁሌት፣ የቅቤው ሽታ፣ የቡናው መዓዛና የእጣኑ ሽታ በየቤቱ ያውዳል፣ የእርዱ ሁካታ፣ የዘመድ አዝማዱ ሳቅ፣ የአገር ባህል ልብሱ፣ ሙዚቃው የአውደ ዓመቱ መገለጫዎች ናቸው።
መስከረም ሲጠባም በርካቶች ለሥራም ሆነ ለሌላ ጉዳይ በሌሎች ከተሞች፣ በየአገራቱ ያሉ አንድ ላይ ተሰባስበው ማዕድ የሚቆርሱበት ወቅት ነው።
የዶሮው መላላጫ፣ እግር፣ ፈረሰኛ ይቀርባል። ዱለቱንም በቤት ብቻ ሳይሆን ከጎረቤት ጋር ተከፋፍለው ይቋደሳሉ።
በሰሜን ኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች እርድ ከተከናወነ በኋላ ደሙ በየደጃፉ ይቀመጥ እንደነበር አዛውንቶች የሚናገሩት ነው።
ደሙ በር ላይ የሚቀመጥበት ዋነኛው ምክንያት ደግሞ በመፅሀፍ ቅዱስ ታሪክ ግብፆች በጠፉበት ወቅት "ደም ሳንቃችሁ ላይ አድርጉ" ተብሎ የተሰጠው የሙሴ ምልክት ነው።
ከክርስትና መምጣት በፊትም ከጥንት ጀምሮ አማልክቱ የተፈጥሮ ሂደትን እንዲቀይሩ ለመማጸን መስዋዕት በእርድ መልክ እንደሚቀርብ የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ።
የእንስሳት መስዋዕትነት በአብዛኛዎቹ ባህሎች ዕብራውያን፣ ግሪኮች፣ ሮማውያን እንዲሁም በጥንቷ ግብፅ ውስጥ ነበር። የእንስሳት መስዋዕትነት ለጸሎትና በሰው ልጅና በአማልክቶች መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ተብሎ ይታመናል።
በዶ/ር ሃብተ ማርያም መጽሃፍ ላይ የእንቁጣጣሽ በዓል በሚከበርበት ጊዜ በአክሱም በወደቀውና አሁን ቆሞ በሚገኘው ሃውልት ሥር ከተነጠፈው የተጠረበ ድንጋይ የእንስሶች እርድ የሚፈፀምበት የተጠረቡ ጉድጓዶች እንደሚገኙም ይገልጻል።
በኢትዮጵያ በርካታ እርዶች ከሚፈጸምባቸው በዓላት አንዱ አዲስ ዓመት ሲሆን ለቤት ብቻ ሳይሆን፣ አሁን በከተሞች ብዙ ባይታይም የታረዱ ዶሮዎች በየሰፈሩ ተጥለው በአንዳንድ አካባቢዎች መታየት እንዲሁም የታረዱ እንስሳትን ደም መሸጋገር ለዘመናት የበዓሉ ድምቀት ሆኖ ቆይቷል።
የሚታረዱት ዶሮዎችን ቀለምንም በተመለከተ በርካቶችም ሶራ (ቀይና ጥቁር የተቀላቀለ)፣ ገብስማ፣ ቀይ ፣ ነጭ ይመርጣሉ።
በአንዳንድ ቦታዎች ጥቁር ሆኖ ነጭ ነጠብጣብ ያላቸው እንስሳት ጥቁሩ ያለፈውን የከፋ ዘመን የሚያሳይ ነጬ መፃኢው ዓመት ብሩህ እንደሚሆን በመታመኑ ለእርድ ይቀርባሉ።
ጥቁር በግ ወይም ዶሮ ማረድ፣ የተመገበው ሰው መጥፎ ነገር እንደሚደርስበት በማመን "እርም አለብኝ" ሲሉም ይሰማል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በተለም በገጠሩ ኢትዮጵያ የጥቁር በግና ዶሮ ዋጋ እንደሚያሽቆለቁልም ይሰማል።
አንዳንድ የእንስሳት ክፍሎችን አለመብላት፣ የእንስሳትን ቀለም፣ ዕድሜ መምረጥ ከኦሪት እምነት ጋር የተያያዘ እንደሆነም መረዳት ይቻላል።
አንዳንድ የታሪክ አጥኝዎች እነዚህ ክብረ በዓላት ጥንታዊ አምልኮ፣ የኦሪትና ክርስትናን ያጣመረ ነው ይላሉ።
እንቁጣጣሽ
እንቁጣጣሽ የሚለው ቃል ንግሥት ሳባ የንጉሥ ሰለሞንን ጥበብ ለማየት ኢየሩሳሌምን የጎበኘችበት አፈ ታሪክ ጋር የሚያገናኙት እንዳሉ ዶ/ር ሃብተ ማርያም በጽሁፋቸው ያስረዳሉ።
ንጉሥ ሰለሞን እንቁ- ለ- ጣጣሽ (ለችግርሽ) ብሎ እንቁዎች እንዳበረከተላት በመጥቀስ በዓመቱ ወደ መናገሻዋ ስትመለስ እንቁ- ለ-ጣትሽ እያሉ ህፃናት እንደተቀበሏትና ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው ይላሉ።
ይህም ልምድ ቀጥሎ በርካታ ህፃናት አበባ ቀንጥሰው ወይንም አበባ ስለው እንቁጣጣሽ በማለት ለቤተሰብ፣ ለዘመድ አዝማድና ለጎረቤት ይሰጣሉ።
ስጦታ የተበረከተለት ቤተሰብ፣ ዘመድ፣ ጎረቤትም "በየዓመቱ ያምጣችሁ" በሚል ልብስና ጫማ ቃል የሚገባበትና ለከርሞ ይሄንን እናበረክትላችኋለን በሚልም የትውልድ ትውፊትነት ተሻግሯል ይላሉ።
የእንቁጣጣሽ በዓል አጀማመር መቼ እንደተጀመረ በእርግጥ በትክክል ባይታወቅም ንግሥት ሳባ ወደ እየሩሳሌም ሄደች የሚባለው ከክርስቶስ ልደት 1000 ዘመን በፊት ሲሆን፣ የዘመን መለወጫም በዚያን ወቅት ሲከበር እንደነበር ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ አፈ ታሪኮችን በማጣቀስ ዶክተር ሃብተማርያም አሰፋ ያስረዳሉ።
መስከረም አንድስ ለአዲስ ዓመትነት እንዴት ተመረጠች? ለሚለው ዶ/ር ሃብተ ማርያም - ዘትንሳኤ የተባለውን ጽሁፍ ዋቢ አድርገው እስራኤል ዘመን የሚለውጡት በየዓመቱ በመስከረም ወር ነበር ይላሉ።
ኢትዮጵያም ከጥንት ጀምሮ የኦሪትን ሕግ በመቀበሏ የዘመን መለወጫም በዚሁ በክረምት ማለቂያ እንደሆነም ያስረዳሉ። ሌሎች ደግሞ የክረምት ማለቂያ በመሆኑ መስከረም እንደተመረጠች ይጠቅሳሉ።
ደመራ በአንዳንድ አካባቢዎች
በጥንት ጊዜ በአንዳንድ አካባቢዎች ከዘመን መለወጫ ጋር ደመራ አብሮ ይከበር እንደነበርና በኋላም ለሁለት እንዲከፈል እንደተደረገ የዶክተር ሃብተ ማርያም ጽሁፍ ያትታል።
ሴቶችና ወንዶች ለዘመን መለወጫ አጥቢያ ሌሊቱን ወንዝ ወርደው ይታጠባሉ። ፀሐይ ሰትወጣ ችቦ እሳት ያቀጣጥላሉ እንዲሁም አበባ ለቅመውና አስጊጠው ስጦታ ያበረክታሉ።
በጥንት ዘመን እንዲሁም በአሁኑም ወቅት በአንዳንድ አካባቢዎች በዘመን መለወጫ ሲነጋጋ የመንደሩ ሕዝብ በየቤቱ ችቦ አቀጣጥለው ሆያ ሆዬ እያሉ እየዘፈኑ በእልልታና ደስታ ወደ ደመራው ቦታ ይሄዳል። ፀሐይ ብልጭ ስትልም በአደይ አበባ ያጌጠ ደመራው ይለኮሳል።
ደመራው ከተቃጠለ በኋላ ከሚገኘው አመድ ግንባራቸውን ይቀባሉ ወደየቤታቸውም ይዘው ይሄዳሉ።
ሌሎች ልምዶች
በበዓላት ወቅት ቡና ማፍላት፣ ዕጣን በማጤስ፣ ፈንዲሻ በመቁላት እንዲሁም ቄጠማና ሳር በመጎዝጎዝ ይከበራል።
የዘመን መለወጫም ከዚህ የተለየ አይደለም።
ቄጠማና ሳር የወቅቱን ለምለምነት ለማሳየት እንዲሁም መጪው ጊዜ ለምለም እንዲሆን ለመመኘት ይጎዘጎዛል።
በአንድ አካባቢዎች ቄጤማና ሳር ከመጎዝጎዝ በተጨማሪ በተጎዘጎዘው ላይ ፈንዲሻ፣ ጠላና ጠጅ የመርጨት ልምድ አለ። ይህም የሰው ዓይን እንዳይበላውና መጥፎ ዐይንንም ለመከላከል ይረዳል የሚል እምነት ይዟል።
ጥቂት ስለ ሄቦ
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ከሚገኙት ማኅበረሰቦች ውስጥ አንዱ የየም ማኅበረሰብ አዲስ ዘመን መለወጫን ሄቦ በተሰኘ ሥነ ሥርዓት ያከብረዋል።
ሰላምን ማስጠበቂያ፣ ግጭቶችን ለመፍታት እንዲሁም ከመንግሥት ሕጎች ወሰን በላይ የሆኑና በድብቅ የተሰሩ ወንጀሎች የሚጋለጥበት እንደሆነ ለማ ንጋቱና ማንደፍሮ ፈንታ በአውሮፓውያኑ 2019 በጻፉት "ሄቦ፡ ኒው ይር ሪቹዋል ኦፍ የም ፒፕል ኢን ሳውዝ ኢትዮጵያ" አስፍረዋል።
ሥርዓቱ ከጥንት ጀምሮ ከትውልድ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ ባህልም ነው። ሄቦ ከያዛቸው መካከል ካማ ኬሳ የተሰኘ የእርቅ ባህል ግጭቶችን ለመፍታት የሚጠቀሙበት እና የማኅበረሰቡን ሰላም ማስጠበቂያ ነው።
ሌላኛው ጫሎ የተሰኘው የፍትህ ባህል ሥርዓት ማንነታቸው ሳይታወቅ የተፈጸሙ ሌብነቶች ወንጀሎችና እና የተሳሳቱ ድርጊቶች ፍንትው ብለው ይፋ የሚወጡበት ነው።
ሌሎች አገራትስ አዲስ ዓመትን እንዴት ይቀበሉታል?
- ስፔናውያን አዲሱን ዓመታቸውን የሚጀምሩት 12 የወይ ፍሬ በመብላት ሲሆን ይህም እያንዳንዱን የሰዓት ምልክት ያመላክታል። አዲሱ ዓመት ከመግባቱ በፊት በጥቂት ሰኮንዶች 12 ወይኖች መበላት የሚኖርባቸው ሲሆን መጥፎ መንፈስን አስወግዶ አዲሱ ዓመት የብልፅግና እንዲሁም ብሩህ ይሆናል ተብሎ ይታመናል።
- በሕንድ አንድ ሸምገል ያለ ሰው ሐውልት ይሰሩና ተሰብስበው እኩለ ሌሊት ያቃጥሉታል። ይህም አሮጌ ዓመቱን የሚያሳይ ሲሆን ቅሬታዎችን ረስቶ በአዲስ ዓመት አዲስ ሕይወት ለመውለድ ቦታ ይሰጣል።
- ጃፓናውያን ሶባ የተባለ ኑድልስ በመብላት አዲሱን ዘመን ይጀመራሉ። ረዣዥምና ቀጫጭን የሆኑት ኑድሎች ጠንከር ያሉ ነገር ግን ለመብላት ቀለል ያሉ ስለሆኑ እነሱን መመገብ ከአሮጌው ዓመት መራቅን ያሳያል።
- በሄይቲ ጁሙዎ የተባለ የዱባ ሾርባ የሚመገቡ ሲሆን በቅኝ ግዛት ወቅት ጥቁሮች መመገብ አይፈቀድላቸውም ነበር። የዱባ ሾርባው አዲስ ዓመትን ከቅኝ ግዛት ቀንበር መላቀቅን፣ ነጻነትን፣ አይበገሬነትን ወደፊት ማለትን የያዘ ነው።
- ዴንማርካውያን ደግሞ አሮጌ ሳህኖችን በመወርወር አዲሱን ዘመን 'ሀ' ብለው ይጀምሩታል።
- ግሪካውያን በበኩላቸው የቀይ ሽንኩርት ራሶች በበር ላይ በማንጠልጠል በመጪው ዘመን ወልደው የሚከብዱበት እድገት የሚመጣበት ዘመን ነውም በማለት ከቤተ ክርሰቲያን መልስ ያንጠለጥሉታል።
- በኮሎምቢያ አጉዌሮ በተሰኘ ባህላቸው በአዲስ ዓመት ዋዜማ በእያንዳንዱ የቤተሰብ አባል አልጋ ሥር አንድ የተላጠ፣ አንድ ያልተላጠ እና በከፊል የተላጠ ሦስት ድንቾች ያስቀምጣሉ። እኩለ ሌሊትም ላይ ዓይናቸውን ጨፍነው አንዱን መምረጥ የሚኖርባቸው ሲሆን በተመረጠውም ድንች መጪው ዓመት ጥሩ እድል፣ የገንዘብ ችግር የሚገጥምበት ወይም ችግርና መልካም ነገር የተቀላቀለ ዓመት ሊሆን ይችላል የሚለውን ይተነብያል።
- በአየርላንድ ዳቦ በቤቱ ግድግዳዎች በበሮች ጋር በማጋጨት መጥፎ መናፍስትን ለማባረር እንዲሁም ጤናማ እና የበለጸገ አዲስ ዓመት እንዲሆንም ያከናውናሉ።
በአሁኑ ወቅት በበርካታ ከተሞች ዘመን መለዋጫ አዲስ ግብን ለወደፊቱ ለማሳካት የሚታቀድበትም ነው።