የአይኤስ የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮ አዘጋጅና ተራኪው ካናዳዊ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት

የአሜሪካ ፍርድ ቤት ለአይኤስ (ኢስላሚክ ስቴት) የፕሮፓጋንዳ ቪዲዮ ያዘጋጅ እና ይተርክ የነበረውን ካናዳዊ በእድሜ ልክ አስራት ቀጣ።

ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ የተወለደው እና የካናዳ ዜግነት ያለው ሞሐመድ ካሊፍ ጥፋተኛ ሆኖ የተገኘው ለቡድኑ የቁስ ድጋፍ ለማድረግ በማሴር በሚል ነው።

የአሜሪካ ፍትሕ ቢሮ የ39 ዓመቱ ካሊፍን በአይኤስ ውስጥ ተሳትፎ የነበረው እና በሶሪያ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሁለት ወታደሮችን በመግደል በቀጥታ ተሳትፏል ሲልም ከሶታል።

የእስላማዊ መንግሥት ቡድን (አይኤስ) እኤአ በ2017 ኢራቅ ውስጥ በአሜሪካ መራሹ ጦር ሽንፈት ገጥሞታል።

ነገር ግን አሁንም ቡድኑ በኢራቅ፣ በሶርያ፣ በአፍጋኒስታን፣ በአፍሪካ ቀንድ እና በምዕራብ አፍሪካ ይንቀሳሳል።

የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ ካሊፍ በ15 ቪዲዮዎች ላይ በእንግሊዘኛ የእስላማዊ ቡድኑን አሰቃቂ ግድያ እያጎላ እና እያደነቀ ሌሎች ለተጨማሪ ጥቃት እንዲነሳሱ እንዲሁም ወደ ቡድኑ እንዲቀላቀሉ ለመቀስቀስ በሚረዳ መልኩ ተርኳል ሲል ከሶታል።

ካሊፍ በካናዳዋ ከተማ ቶሮንቶ ውስጥ ያደገ ሲሆን በ2013 ወደ ሶርያ በመጓዝ አይኤስን ተቀላቅሏል።

እስከ 2018 ማብቂያ ድረስም ለአይኤስ መገናኛ ብዙኃን ቡድን ሲሰራ ነበር።

ይህ ቡድን በ2014 ብቻ የአሜሪካዊው ጋዜጠኞች ጀምስ ፎሌ እና ስቴቨን ሶትሎፍ እንዲሁም የብሪታኒያ ዜግነት ያላቸው የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች አለን ሄኒንግ እና ዴቪድ ሄይነስ አንገታቸውን ሲቀላ የሚያሳየውን ቪዲዮ ለቋል።

በ2019 ታኅሣሥ ወር ላይ ካሊፍ በአሜሪካ፣ በኩርድ ሚሊሻዎች እና በሶሪያ ዲሞክራቲክ ኃይሎች ጥምረት በቁጥጥር ስር ሊውል ችሏል።

የአሜሪካው ፍትሕ ቢሮ ግለሰቡ ሦስት ቦምቦችን እንዲሁም ኤኬ-47 ጠብመንጃ በመያዝ ለብቻው የሶሪያ ዲሞክራቲክ ኃይሎች ላይ ጥቃት ከፍቷል ሲልም ወንጅሎታል።

በዚህ ጥቃትም ታጣቂዎቹ የሚኖሩበት መጠለያ ላይ የቦምብ ጥቃት በማድረስ በመቀጠልም የተኩስ ልውውጥ ማድረጉን በዝርዝር አስረድቷል።

ካሊፍ ጠብመንጃው እስኪነክስበት እና እጁን እስከሚሰጥበት ድረስ መታኮሱን ክሱ ያስረዳል።

በኋላም ለኤፍቢአይ ተላልፎ ተሰጥቷል።

ካሊፍ በቀረበበት የሽብርተኝነት ክስ ባለፈው ዓመት ኅዳር ወር ላይ ጥፋተኛ ተብሏል።