ከአድዋ ገጠር ተነስታ በፋሽኑ ዓለም እየደመቀች ያለችው ሞዴል መዓርግ-ማጊ

በሞዴሊንግ ሙያዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ከሆኑ እና የተለያዩ ምርቶችን ከሚያመርቱ ኩባንያዎች ጋር ትሰራለች።

መዓርግ ታረቀ (ማጊ) 'ባችለር' ተብሎ በሚጠራው የአሜሪካ ሪያሊቲ ሾው ላይም ተሳትፋለች።

የልጅነት ጓደኞቿ ከሚኖሩባቸው የገጠር አካባቢዎች በባዶ እግራቸው ወደ ትምህርት ቤት ሲመላለሱ ማየት ልቧን ይሰብረው እንደነበር የምታስታውሰው ማጊ፣ ጫማ የሌላቸው ሴቶች መጫሚያ እንዲያገኙ የሚያግዝ ግብረ-ሰናይ ድርጅት በማቋቋም በመስራት ላይ ትገኛለች።

መዓርግ ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ ተነስታ ወደ ዓለም አቀፋዊ መድረክ ስላደረገችው ጉዞ ለቢቢሲ ታሪኳን እነዲህ አካፍላለች።

የልጅነት ጊዜዋ በገጠር ተወልዶ ከሚያድግ ማንኛውም ልጅ የተለየ እንዳልነበረ የምትናገረው ማጊ፣ “ከብቶች እየጠበቅኩ፤ ከልጆች ጋር እየተጫወትኩ፤ በባህልና ወጋችን መሰረት ነው ያደግኩት” ትላለች።

ዕጣ ፈንታዋ ልክ በትውልድ ቦታዋ እንደምታውቀው እና እንደምትሰማው፣ ጋብቻ ሊሆን እንደሚችል ውስጧ ይነግራት ስለነበረ በሆነ አጋጣሚ ከአካባቢዋ በመውጣት ትምህርቷን መቀጠል ምኞቷ ነበረ።

“ወደተሻለ ደረጃ ለመድረስ፣ ዶክተር ወይም ጠበቃ ለመሆን በትምህርት መበርታት እንዳለብኝ ስላመንኩ በትምህርቴ ላይ አተኩሬ ነበር። በመቀለ ከተማ በተካሄደው የክልል ተማሪዎች ውድድርም አድዋን እስከመወከል ደርሻለሁ” ስትል ትናገራለች።

መዓርግ የተወለደችው ትግራይ ውስጥ በአድዋ ከተማ - አዲ ሓቂ በሚባል ቦታ ነው።

ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ዓዲ ማሕለካ ተከታትላለች። ከ9 እስከ 12 ደግሞ በንግሥተ ሳባ ተምራለች።

በአገር አቀፍ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና ጥሩ ውጤት በማምጣት ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ገብታ የመጀመሪያ ዲግሪዋን በፋርማሲ ለማግኘት በቃች።

ጉዞ ወደ አሜሪካ . . .

ማጊ ከተመረቀች በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ በሙያዋ ለመስራት የቻለች ቢሆንም በውስጧ ግን ሁሌም አንድ ነገር ይመላለስ ነበር።

ዕድሉን ካገኘች ወደ ባሕር ማዶ ተሻግሮ ለመማር ትፈልግ ነበር።

“እንደ ዕድል ሆኖ፣ ዲቪ ደርሶኝ ሄድኩ። ወደዚያ ከሄድኩ በኋላ ግን ሁሉም ነገር እንደሚነገረው ቀላል ሆኖ አልጠበቀኝም። ገንዘብ በቀላሉ እንደሚገኝ፤ መኪና እና ቤት በአንድ ዓመት መውስጥ እንደሚኖረኝ፤ ለእናቴም ቤት ለመግዛት ሀሳብ ነበረኝ” ትላለች የጠበቀችውና የጠበቃት በማነፃፀር።

አሜሪካ ስትደርስ ኑሮ ከባድ መሆኑን ተገነዘበች።

“ወደ አሜሪካ ልውጣ እንጂ ሕይወት አስቸጋሪ አይሆንም ብለን ነው የምናስበው። እኔን ያጋጠመኝ ግን እንደዚያ አልነበረም። ልክ እንደሄድኩ ሁለት ቦታ ሥራ ሰርቼ ማታ ላይ እማር ነበር። ቀላል አልነበረም።”

የሞዴሊንግ ሕይወት

መዓርግ በልጅነቷ የፋሽን እና የውበት ሙያ ይስባት ስለነበረ፣ በአሜሪካ የዕለት ኑሮዋን ለማሸነፍ ከምትሰራው ሥራ በተጨማሪ ወደ የሞዴሊንግ ሙያ ገባች።

ይህንንም በትምህርት እና በሥልጠና ለማስደገፍም ሞዴሊንግ እና ትወና በመማሯ በርካታ የሥራ ዕድሎች ተጠሩላት።

“በፋሽን እና የውበት ሞዴሊንግ ዘርፍ ነው የምሰራው። ከብዙ ዓለም አቀፍ አምራች ኩባንያዎች ጋር ሠርቻለሁ፤ ቮግ በመሰሉ ታዋቂ መጽሔቶች ላይም ወጥቻለሁ። ኒትሮጅና እና ሴራቪ ከተባሉ ትልልቅ ካምፓኒዎች ጋርም ሠርቻለሁ” በማለት ትጠቅሳለች።

በዚህ ሙያዋ ወደ ተለያዩ አገራት ከመጓዝ በተጨማሪ፣ በተለያዩ የፋሽን እና ሞዴሊንግ መድረኮች ላይ የክብር እንግዳ እና ዳኛ በመሆን ተሳትፋለች።

እንዲሁም የተለያዩ ትልልቅ መድረኮችና የቴሌቪዥን ትርኢቶችን መርታለች፤ አስተባብራለች።

በአሁኑ ጊዜ የፋርማሲ እና የሞዴሊንግ ሥራዋን በማጣጣም ጎን ለጎን እያስኬደች ትገኛለች።

“የእኔ ጫማ፣ የአንቺ ጫማ ነው”

መዓርግ ከልጅነት ጊዜዋ አንድ ነገር ፈጽሞ አይረሳትም፣ ይህም እሷና ጓደኞቿ የነበረባቸው የጫማ ችግር።

“በልጅነቴ በዓመት የሚገዛልኝ አንድ ጫማ ብቻ ነበረ። አሱም ከፕላስቲክ የሚሰራ ሲሆን ሲቀደድ ብረት በማጋል እየተጠገነ አደርገው ነበረ። እኔ ቢያንስ አንድ ጥንድ ጫማ ነበረኝ፤ ብዙ ጓደኞቼ ግን ጫማ የሚባል አልነበራቸውም” ስትል በልጅነቷ ያስተዋለችውን ታስታውሳለች።

ጓደኞቿ ከሚኖሩበት ገጠር በባዶ እግራቸው ወደ ትምህርት ቤት ሲሄዱ ማየት ለእሷ አሳዛኝ ሁኔታ ነበር። ይህ ሁኔታም 5ኛ ክፍል እያለች የምታስተውላቸውና የምትጨነቅባቸው ነገር እንደነበረ ለቢቢሲ ተናግራለች።

“ወደ ውጭ አገር የመሄድ ዕድል የመሄድ ዕድል ካገኘሁ፣ ሌላ ነገር ማድረግ ብለችል እንኳን በገጠር እና በከተማ ላሉ ሴቶች ጫማ መስጠት ይኖርብኛል ስል ለራሴ ቃል ገባሁ” በማለት ታስረዳለች።

ወደ አሜሪካ ካቀናች በኋላ ብዙም ሳትቆይ የልጅነት ቃሏን ለመጠበቅ፣ ከሰባት ዓመት በፊት ለድሆች ጫማ የመለገስ ሥራ ጀመረች። በእርግጥ ይህንን ተግባር ቀደም ብላ በሃይማኖት አባቷ በኩል ጀምራው ነበር።

“አድዋ በነበርኩበት ጊዜ በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ‘ፋዘር ቲኖ’ የሚባሉ አባት ነበሩኝ። በልደቴ ቀን ገንዘብ ይሰጡኝ ነበር። ወደዚህ አገር ስመጣ ግን ገንዘቡን ጫማ ገዝተው ለተቸገሩ ሴቶች እንዲሰጡልኝ አደረኩ” ትላለች።

በ2015 (እ.ኤ.አ) ደግሞ ‘ዎክ ዊዝ ሚ’ የተባለ የበጎ አድራጎት እንቅስቃሴ በመጀመር በሥራዋ ከምታገኘው ገቢ እና ከሌሎች ለጋሾች በሚገኝ ገንዘብ ጫማ በመግዛት ለተቸገሩ ማድረስ ችላለች።

ብዙም ሳይቆይ ‘ዎክ ዊዝ ሚ’ የሚለው ስያሜ በሌላ የተለየ ሥራ ላይ የተሰማራ ድርጅት ቀድሞ በመመዝገቡ፣ የበጎ አድራጎት ተግባሯን ‘ማይ ሹ ዩር ሹ’ ወደሚል በመቀየር ቀጠለች።

“‘የእኔ ጫማ የአንቺ ጫማ ነው’ የሚለውን ስም በጣም ነው የወደድኩት። ድርጅቱ ለትርፍ ያልተቋቋመ ሲሆን ጫማዎችን እና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶችን በስጦታ መልክ ያቀርባል። ዓላማችን በየትኛውም ድሃ አገር ውስጥ ያሉ የተቸገሩ ህጻናትን መርዳት ነው” ትላለች መዓረግ።

የበጎ አድራጎት ሥራዋን ተወልዳ ባደገችበትና በርካታ ማኅበራዊ ችግሮች በተመለከተችበት አድዋ እና አካባቢው የጀመረችው ማጊ፣ እስከ ደቡብ ክልል በመጓዝ የጫማ ድጋፍ አድርጋለች።

በአጠቃላይ በድሃ አገራት በተለይም በአፍሪካ እና በሕንድ ውስጥ ያሉ ድሆችን ለመርዳት በማቀድ እንቅስቃሴ ብምትጀምርም ሁለት ጉዳዮች ግን ከባድ ፈተና ሆነውባታል።

የምታቀርበውን ዕርዳታ ለማስፋት ከብዙ ለጋሾች ጋር በመነጋገር መሥራት በጀመረችበት ጊዜ፣ በዓለማችን የተከሰተው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና የትግራይ ጦርነት ዋና ተግዳሮቶች ሆነውባታል።

ነገር ግን አሁንም ተስፋ ባለመቁረጥ አቅሟን በማደራጀት እና አጋሮችን በማስተባበር እየሰራች መሆኑን ትናገራለች።

“የእኔ አላማ ጫማ ማቅረብ ብቻ ሳይሆን የትምህርት ቁሳቁስ፣ ምግብ እና መጠለያ ማቅረብ ነው” ስትል ታስረዳለች።

'ዘ ባችለር' (ላጤው)

ይህ በእውነተኛ ድርጊቶች የታጀበ የቴሌቪዥን ትርኢት ሲሆን፣ በአሜሪካ ተዘጋጅቶ በተለያዩ አገራት ከፍተኛ ተመልካች አለው።

የትዳር አጋር ወይም ፍቅረኛ የሌላቸው ግለሰቦች በፕሮግራሙ ላይ ቀርበው አጋር የሚሆናቸውን ሰው ሲመርጡ ይታያል። ታድያ መዓረግም ወደ ውድድሩ የገባችው የትግራይ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ነው።

መዓርግ ታረቀ - ማጊ - ከ 'ዘ ባችለር' የቴሌቪዥን ሪያሊቲ ሾው ተሰናብታ ስትወጣ አድዋ ወደ ሚገኙት ቤተሰቦቿ ስልክ ደወለች።

ተወዳዳሪዎች በውድድሩ ውስጥ እስካሉ ድረስ ተንቀሳቃሽ ስልኮች መያዝ ስለማይፈቀድላቸው እሷም በቆይታዋ ማንኛውንም መረጃ እና የዓለም ክስተቶችን የመከታተል ዕድል እንዳልነበራት ታስታውሳለች።

“ወደ ውድድር ስገባ ለእናቴም ሆነ አገር ቤት ላሉ ሌሎች ዘመዶቼ አልነገርኳቸውም። ከዚያ ስለውድድሩ ልነግራት ስልክ ለመደወል ሞከርኩ ግን አልሰራም። ለወንድሜ እና ለማውቃቸው ሰዎች ሞከርኩኝ የእነሱም አይሰራም። ከዚያም በሁኔታው በጣም ደነገጥኩ” ስትል ሁኔታውን ታስታውሳለች።

በመቀጠል አሜሪካ ወደሚገኙ ጓደኞቿ ስትደውል ትግራይ ውስጥ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን ነገሯት።

“በጣም ደንግጬ ‘ምን እያላችሁ ነው? እንዴት ሊሆን ቻለ?’ አልኳቸው። ልቤ ሊከዳኝ ደረሰ፤ እጆቼ ተንቀጠቀጡ፤ ወደ ሥራ እንኳን መሄድ አልቻልኩም። ዜናውን የሰማሁበት ቀን በሕይወቴ እጅግ የከፋ ቀን ነበር። ለመተንፈስ እስከመቸገርና ምግብ እስካለመብላት ደረስኩ” በማለት በወቅቱ ያጋጠማትን ትገልፃለች።

የጦርነቱ ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ በሄደ ቁጥር የማዓረግ ጭንቀትና ሐዘንም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሄደ። ቤተሰቧን እንደገና ለማየት ዕድሉ ይኖራት እንደሆነ እስከመጠራጠር ደረሰች።

ሥራዋንም በአግባቡ ማከናወን ተቸገረች “በሥራ ቦታ ሳለቅስ ባልደረቦቼ አብረውኝ ይጨነቁ ነበር። በምሽት መባነን የተለመደ ባህሪዬ ሆኗል። ከውድድሩ አዘጋጆች ጋር በነበረኝ ውል መሰረት በማኅበራዊ ድረ ገጽ ሆነ በሚዲያ ቀርቤ ትግራይ ውስጥ ስለሚሆነው ነገር መጻፍ እና መናገር አለመቻሌ ደግሞ ይበልጥ ጎዳኝ” ታለላች።

የቤተሰብ ድምፅ ከትግራይ

መዓርግ የትግራይ ጦርነት በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ከተጀመረ ከሦስት ወራት በኋላ ነበር የቤተሰቦቿን ድምፅ መስማት የቻለቸው።

“ያኔ ታናሽ ወንድሜ ወደ ሱዳን መሰደዱን ተነገረኝ። የጎረቤቶቻችን ልጆች እንደተገደሉ ሰማሁ። የቤተሰቦቼን ድምጽ በመስማቴ ደስተኛ ብሆንም ወንድሜ ራሱን ለማዳን ወደ ሱዳን እንደተሰደደ፣ ረሃብ እንዳለ እና ብዙ ሰው መሞቱን እናቴ ስትነግረኝ በጣም አዘንኩኝ” ትላለች።

አክላም “እናቴን ጠዋት አናግሬ ማታ የማጣት ወይም ማታ አናግሬያት ጠዋት የማጣት ስለሚመስለኝ እጨነቅ ነበር። በስልክ ከቤተሰብ ጋር እያወራሁ የተኩስ ድምጽ እሰማ ነበር። እዚህ የማውቃቸው ወዳጆቼ ስለቤተሰባቸው በአጋጣሚ ከሰሙ ብዙ መርዶ ነው የሚነገራቸው” ትላለች በሀዘን ስሜት ውስጥ ሆና።

መዓርግ የቤተሰቧ ጉዳይ ብቻም ሳይሆን በአጠቃላይ በትግራይ ውስጥ እየሆነው ያለው ሁኔታ እንደሚያስጨንቃቸው ትናገራለች። ይህም ሁኔታም በፋርማሲ እና በሞዴሊንግ ሥራዋ ላይ ከፍተኛ ጫና አሳድሮባታል።

“ሕይወቴ በጣም ተለውጧል። ድሮ ተጫዋች እና ጎበዝ ነበርኩ፤ ዛሬ ግን እንዳዚያ እንዳልሆንኩ ሆኖ ይሰማኛል። በእርግጥ ዛሬም ጠንካራ ነኝ። ይህን ስሜት ለማስወገድ እየታገልኩ ነው። ነገር ግን ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ቀን በቀን የሚሰማው ሐዘንና ጭንቀት በመሆኑ ሕይወቴ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል” ትላለች ማጊ።

ጦርነቱ ባስከተለባት ተጽዕኖ ምክንያት ከሥራዋን እና ከሙያዋ እንድትርቅ የተገደደችበት ወቅት እንደነበረ በማስታወስ “ሥራ አቁሜ ነበር። ነገሮችን ለማሰላሰል ጊዜ ወስዶብኛል። በአምላክ እርዳታ ወደ ሥራ ተመለሻለሁ። ምክንያቱም ለቤተሰቤና በችግር ላይ ላሉ ሰዎች ተስፋ መሆን ካለብኝ እኔ ጠንካራ መሆን እንዳለብኝ ተገንዝቤያለሁ።”