በደቡብ ክልል ሕዝበ ውሳኔ በአንድ ምርጫ ጣቢያ አንድም ድምጽ ሰጪ ሳይገኝ የቀረው ለምንድን ነው?

ጥር 29/2015 ዓ.ም. 12ኛውን የኢትዮጵያ ክልል ለመመስረት በደቡብ ክልል አምስት ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎች ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዷል።

በዕለቱ 3 ሺህ 771 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ነዋሪዎች ድምጽ ሲሰጡ ውለዋል።

አንደኛው የምርጫ ጣቢያ ግን የተለየ ነገር አስተናግዷል።

ጣቢያው በሚጠበቀው ሰዓት ተከፍቶ፣ የምርጫ አስፈጻሚዎች በቦታው ቢገኙም ከንጋት እስከ ምሽት አንድም መራጭ ‘ዝር’ አላለም።

ሦስቱ የምርጫ አስፈጻሚዎች ሰዓቱ ሲገፋ መራጮች ይመጣሉ ብለው ቢጠብቁም የተቀየረ ነገር አልነበረም።

ነዋሪዎች ድምጽ እንዲሰጡ የወረዳው አስተዳዳሪዎች ‘የማግባባት ሥራ’ ሰርተዋል።

ነዋሪዎች ግን በእምቢተኝነታቸው ጸንተዋል። የመጣው ኮሮጆም ባዶውን ተመልሷል።

ይህ የሆነው በቡርጂ ልዩ ወረዳ ዳልኦ ቀበሌ ነው። ዳልኦ በልዩ ወረዳው ካሉት 27 ቀበሌዎች አንዱ ነው።

ነገሩን በዝርዝር እንየው።

ባለፈው ጥር መገባደጃ በኮንሶ፣ በወላይታ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በጋሞ፣ በጌዲዮ እና በጎፋ ዞኖች እንዲሁም በቡርጂ፣ በባስኬቶ፣ በአማሮ፣ በአሌ እና በዲራሼ ልዩ ወረዳዎች ውስጥ አዲስ ክልል ለመመስረት ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዷል።

የሕዝበ ውሳኔው ድምጽ ለመስጠት ከሦስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ 36 ሺህ የሚሆኑት በቡርጂ ልዩ ወረዳ የሚኖሩ ናቸው።

ከዚህ ውስጥ 851 የዳልኦ ቀበሌ ነዋሪዎች በተደረገው ቅሰቀሳ መሠረት ድምጽ ለመስጠት ካርድ ወስደዋል፤ ነገር ግን አንዳቸውም ድምጽ አልሰጡም።

ለመምረጥ የተመዘገቡ ነዋሪዎች “በቀበሌ ውስጥ ያለው ችግር እና ጥያቄን አስተዳደሩ ስላልፈታልን [በሕዝበ ውሳኔው] መሳተፍ አንፈልግም” ብለው መቅረታቸውን በዕለቱ አርባ ምንጭ ላይ መግለጫ የሰጡት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚደቅሳ ተናግረዋል።

ቢቢሲ በምርጫው ለመሳተፍ ለምን አሻፈረኝ አላችሁ? ሲል የዳልኦ ቀበሌ ሦስት ነዋሪዎችነ አነጋግሯል።

በቀበሌው ተወልደው ያደጉና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ነዋሪ “ለዓመታት የዘለቀው ችግራችን ሰሚ በማጣቱ እዚህ ውሳኔ ላይ ደርሰናል” ይላሉ።

እርሳቸው እንደሚገልጹት፣ የቀበሌው ነዋሪዎች በጋራ የሚጠቀሙበትና የተወሰነ የግለሰቦች መሬት፣ በአጎራባች ቀበሌ አስተዳደር ተወስዶባቸዋል።

ይህ በመሆኑ በተለይ የግል የእርሻ መሬት የሌላቸው ሰዎች ለችግር መጋለጣቸውን ይናገራሉ።

“መሬቱ ላይ ከዚህ በፊት ማሽላ እና በቆሎ እንዘራ ነበር። እነርሱ በጉልበት ማሳው ለእኛ ይገባል በሚል ወስደውታል. . . መሬቱ ሰፊ ነው። አሁን መሬቱን ተከልክለናል። ረሃብ ላይ ነው ያለው ነው” ብለዋል።

ይህ ክስ የሚቀርብበት የበኖ ቀበሌ ሲሆን፣ ሁለቱም የቡርጂ ብሔረሰብ አባላት ናቸው።

“ይህንን ችግር የሚፈጥሩት አመራሮቹ ናቸው። ሁለቱም ቀበሌዎች ቋንቋንችንም ጎሳችንም አንድ አይነት ነው። ሕዝቡ ጥል የለውም” ይላሉ።

ከዚህም አልፎ አብዛኛው የቀበሌዎቹ ነዋሪዎች በዝምድና የተሳሰሩ ናቸው። “ልጅ እዚህ አባት እና እናት እዚያ” የሆኑም እንዳሉ ጠቅሰዋል። በተመሳሳይ ስሜ አይጠቀስ ያሉ ሌላ የቀበሌው ነዋሪ ችግሩ ከ15 ዓመት በላይ ያስቆጠረ መሆኑን ይገልጻሉ።

በወቅቱ መሬቱ የበኖ ቀበሌ “ድንበር አልፎ መሬታችንን ሲወስድ ተዉ ስንል ብዙ ሰው ታሰረ” የሚሉት ነዋሪው፣ ችግሩ እየተባባሰ ሄዶ አሁን መሬቱ ላይ ሰዎች መኖሪያ ቤቶችን እንደገነቡ ይናገራሉ።

አሁን አካባቢው በድርቅ መጠቃቱን የነገረን ሦስተኛው ነዋሪ ደግሞ በቀበሌው በቂ የሚታረስ መሬት ባለመኖሩ ችግሩ ይበልጥ አሳሳቢ እንዳደረገው ይናገራል።

በሌላኛው ቀበሌ ተወሰደ የሚባለው መሬት “ውሃ ዳር ነው፣ በጣም ለም ነው” የሚለው ነዋሪው እንደ ሃብሃብ ያሉ ፍራፍሬዎችም ይመረትበታል ሲል ይገልጻል።

ነዋሪው ጉዳዩ በቀላሉ መፈታት ይችላል ብዬ አስባለሁ ካለ በኋላ፣ ነገር ግን በወረዳው አስተዳደር ችላ በመባሉ “እስከ መተኳኮስ ደርሰናል” ሲል አክሏል።

ታዲያ “እጅግ አንገብጋቢ ነው” የሚሉት ይህ ችግር እንዲፈታ ከወረዳው አስተዳደር እስከ ክልል የዘለቀ አድካሚ ሙከራዎችን አድርገዋል።

ለወረዳው ያቀረቡት ተደጋጋሚ አቤቱታ በቂ ምላሽ አላገኘም። ሆኖም የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት መሬቱ እንዲመለስ ወስኖልናል የሚሉት ነዋሪዎች ውሳኔው ግን ሊተገበር አልቻለም ብለዋል።

የቡርጂ ልዩ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳኜ ሂዶ ግን ነዋሪዎች የሚያነሱት ችግር “የተጋነነ እና አንዳንዱም ሐሰት ነው” ብለዋል።

በእርግጥ የቀበሌው ነዋሪዎች ቅሬታቸውን በተደጋጋሚ ማቅረባቸውን አረጋግጠዋል። “የቀበሌውን ወሰን ነዋሪው ነው እንጂ የወረዳው አስተዳደር አያውቀውም” የሚሉት ኃላፊው ችግሩን ለመፍታት “መንግሥት እየሰራ” እንደሆነ ጠቅሰዋል።

የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት “ይዞታው በዳሎ ቀበሌ ስር ይሁን ብሎ አልወሰነም” ሲሉም ያስረዳሉ።

የሆነው ሆኖ የቀበሌው ነዋሪዎች አድሮብናል ያሉትን ቅሬታ ራሳቸውን ከሕዝበ ውሳኔው በማግለል ገልጸውታል።

የደቡብ ክልል ሕዝበ ውሳኔ እና የዳልኦ ቀበሌ ነዋሪዎች

ነዋሪዎች ይህ የቆየና ‘ሰሚ ያጣ’ ችግር ትኩረት እንዲያገኝ “ደቡብ ኢትዮጵያን” ለመመስረት የሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ “ብንጠቀምበት መልካም ነው” የሚል ሃሳብ አመንጪ ከመሃላቸው ብቅ አለ።

በጉዳዩ ላይ ተመካከሩበት እና አንድም ሰው ወደ ምርጫ ጣቢያ እንዳይሄድ ወሰኑ።

“አፍንጫችን ሥር ያለ ችግር ሳይፈታ ክልል ቢመሰረት ምን ይፈይድልናል” ነው የሚሉት።

ነዋሪዎቹ የወረዳው አመራሮች “እንዲህ አይነት ነገር ሲኖር ችግሩ ይፈታል እያሉ ያታልሉናል እንጂ መፍትሄ ሲሰጥ አላየንም” ይላሉ።

ለቢቢሲ አስተያየታቸው ከሰጡት ነዋሪዎች መካከል አንዱ ብልጽግና ያሸነፈበትን የ2013ቱን ምርጫ እንደ አብነት ያነሳሉ።

“ያኔ ከምርጫው በኋላ ጉዳዩን እንፈታለን። ‘ችግር የለም’ ብለው ቃል ገብተው ነበር። ከወረዳው አመራር መጥቶ ሕዝቡን አሳምኖ ነው ምርጫ ያደረግነው። ብዙ ጊዜ ነው የሚያታልሉን” ብለዋል።

ቀደም ባለው ምርጫም ተመሳሳይ ነገር እንደገጠመ ጨምረው ያስታውሳሉ።

“በ2007 ምርጫ አሁን ክልል ያሉ ግለሰብ ‘ከምርጫው በኋላ የእናንተ መሬት ላይ ውሳኔ እሰጣለሁ። ማንም ሳይገባ እኔ ነኝ የምወስነው’ ብለው ሕዝቡ ፊት ቃል ገብተው ነበር። ወደ ክልል ከሄዱ በኋላ ግን ዞር ብለው አላዩንም” ሲሉ ይገልጻሉ።

ለዚህ ነው “ሁሉም የቀበሌ ሕዝብ ተባብሮ፣ አንድ ሆኖ” ራሱን ከሕዝበ ውሳኔው ያገለለው።

በዚያን ቀን የወረዳው የብልጽግና ፓርቲ ኃላፊ በቦታው ተገኝተው ነዋሪዎች እንዲመርጡ መጠየቃቸውን እና ከዚያም አልፎ “የቀበሌውን አመራር አስራለሁ ብለው ሲዝቱ ነበር” ብለዋል።

በተጨማሪም “እናንተ ናችሁ ያስተባበራችሁት” በሚል የአገር ሽማግሌዎች ላይ ማስፈራራት ደርሷልም ብለዋል።

አቶ ዳኜ ሂዶ ግን “ይህ ሐሰት ነው” ብለዋል። ቦታው ላይ ተገኝተው ነዋሪዎች እንዲመርጡ ለማግባበት እንደሞከሩ ገልጸው “ዛቻ የተባለው ግን ሃሜት ነው” ብለዋል።

አቶ ዳኜ የነዋሪዎቹ በሕዝበ ውሳኔው አለመሳተፍ “ይሄን ያህል ተጽዕኖ አይፈጥርም” ያሉ ሲሆን፣ “ሕዝቡ ዲሞክራሲያዊ መብቱን እንዳይጠቅም ያደረገው አካላትን ግን ቼክ ማድረግ ያስፈልጋል” ሲሉ ገልጸዋል።

ኃላፊው በዚህ ሕዝበ ውሳኔም ይሁን በሌሎች ምርጫ ፓርቲው ካለው ችግር ጋር በተያያዘ “ምንም ቃል አልገባም” ሲሉ ገልጸው፣ ይህንን ችግር ለመፍታት ወረዳው ቡድን አዋቅሮ እየሰራ እንደሆነና “ያደረን ጥያቄ” አሁን ይፈታ ማለት አይገባም ብለዋል።

“ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ ተረጋግተን ያዋቀርነው ቡድን ወርዶ ውሳኔ ይሰጣል ብለናቸው ነበር” ብለዋል።

የውዝግብ ምንጭ የሆነው መሬት ጥቅም ላይ እንዳይውል ታግዷል። አቶ ዳኜ ይህ መሆኑ ምንም የፈጠረው ችግር የለም ካሉ በኋላ “በአካባቢው የሚታረስ መሬት ጠፍቶ ነው ወይ?” ሲሉ ይጠይቃሉ።

ኃላፊው ጉዳዩ “ውስጡ ሌላም ነገር አለ” ካሉ በኋላ ምንነቱን ከመግለጽ ግን ተቆጥበዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎችን አሰማርቶ በታዘበው የደቡብ ክልል ሕዝበ ውሳኔ “አሳሳቢ” ሲል ከገለጻቸው ሁኔታዎች አንዱ የዚህ ቀበሌ ነዋሪዎች አለመሳተፋቸው ነው።

በወረዳው አስተዳደር እና በቀበሌው መካከል የተፈጠረው ችግር የተካረረ ይመስላል። የቀበሌው ነዋሪዎች “መሬቱ እጅግ ያስፈልገናል። በፍጥነት መፍትሄ ይሰጠን” ሲሉ ወረዳው “እጃችን ላይ ብዙ ሥራ አለ በሂደት ይፈታል” የሚል መልስ አለው።

ከሕዝበ ውሳኔው በፊት የነበረው ችግር ከዚያ በኋላ ቢቀጥልም የዳልኦ ቀበሌ ነዋሪዎች በኢትዮጵያ ብዙም ባልተለመደ መንገድ ቅሬታቸውን ማሰማታቸው እርግጥ ነው።

ቢሆንም የቀበሌው ነዋሪዎች ከሕዝበ ውሳኔው እራሳቸውን ቢያገሉም ድምጽ ከሰጠው ሕዝብ መካከል የአብዛኛውን ይሁንታ ላገኘው ውሳኔ ተገዢ መሆናቸው አይቀሬ ነው።