ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በደቡብ ክልል የሚካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ምን አይነት ለውጥ ይዞ ሊመጣ ይችላል?
በመጪው ጥር ወር መጨረሻ በደቡብ ክልል ስር በሚገኙ 6 ዞኖች እና 5 ልዩ ወረዳዎች ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ ይካሄዳል።
ሕዝበ ውሳኔው ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ የቆየውን የደቡብ ክልልን በማክሰም፣ በምትኩ አንድ አዲስ ክልል እንዲመሰረት እና “ነባሩ” በአዲስ ቅርጽ እንዲዋቀር ያደርገዋል።
ይህም በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የፌደራል መንግሥቱ አባላ የሆኑትን ክልሎች ብዛት ወደ 12 ከፍ ያደርገዋል።
በቀዳሚነት የሲዳማ ክልል ተከትሎም የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል እስኪመሰረቱ ድረስ የደቡብ ክልል በስሩ 13 ዞኖች 8 ልዩ ወረዳዎች እና 22 ከተሞችን ይዞ ነበር።
የደቡብ ክልል በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የሚገኙበት እና ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ከሚኖሩባቸው ክልሎች መካከል አንዱ ነበር።
ባለፉት አራት ዓመታት በክልሉ የሚገኙ ልዩ ወረዳዎች ወደ ዞን፣ ዞኖች ደግሞ ወደ ክልል እንዲቀየሩ ሲነሱ የቆዩ ጥያቄዎችን ተከትሎ በተነሳ ግጭት ሞት፣ የአካል ጉዳት፣ መፈናቀል እና የንብረት ውድመት ደርሷል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ፣ በክልሉ 13 የነበሩት ዞኖች ወደ 17 አድገዋል ብዙም ሳይቆይ 2 አዳዲስ ክልሎችም ተመስርተዋል።
ጥር 29/2015 ዓ.ም. የሚደረገው ሕዝበ ውሳኔ ደግሞ ክልሉን ሙሉ በሙሉ ወደ ታሪክነት ይቀይረዋል።
የአዲሱ ክልል ምሥረታ እና ሕዘበ ውሳኔው
በመጪው ጥር ወር መገባደጃ በኮንሶ፣ በወላይታ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በጋሞ፣ በጌዲዮ እና በጎፋ ዞኖች እንዲሁም ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አማሮ፣ አሌ እና ዲራሼ ልዩ ወረዳዎች ወስጥ የሚከናወነው ሕዝበ ውሳኔ፣ ነዋሪዎች በአዲስ ክልል ለመደራጀት ወይም በነባሩ ክልል ለመቀጠል ድምጽ የሚሰጡበት ነው።
ይህንን ሕዝበ ውሳኔ ለማስፈጸም 410 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደሚደረግ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቢቢሲ ገልጿል።
ቦርዱ በስድስት ዞኖች እና በአምስት ልዩ ወረዳዎች ስር ሕዝበ ውሳኔውን ለማከናወን 31 ማስተባበሪያ ማዕከላትን እና 3 ሺህ 752 የምርጫ ጣቢያዎችን ማደረጀቱንም ጠቅሷል።
በተጨማሪም ተፈናቃዮች በሚገኙባቸው አካባቢዎች 4 ልዩ የምርጫ ጣቢያዎችን አቋቁሟል።
በሕዝበ ውሳኔውን ከ11 ሺህ 400 በላይ አስፈጻሚዎች የሚሳተፉበት ሲሆን፣ የመራጮች ምዝገባም ከታኅሣሥ 11 እስከ 26 ባሉት ቀናት ይከናወናል።
በሕዝበ ውሳኔው የቀረቡት አማራጮች በነጭ እርግብ እና በጎጆ ቤት [በደቡብ ክልል ሰንደቅ ዓላማ ላይ ያለው ዓርማ ዓይነት] የተወከሉ ሲሆን በአዲስ ክልል መደራጀት ደግሞ በነጭ ርግብ ተወክሏል።
አዲሱን ክልል “አልደግፍም” የሚለው አማራጭ ቀደም ብሎ በነጭ ላም ተወክሎ የነበረ ቢሆንም፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ወደ ጎጆ ቤት መቀየሩን ምርጫ ቦርድ ገልጿል።
የአዲሱ ክልል ምሥረታ እና የነባሩ ክልል ዕጣ ፈንታ
በስድስት ዞኖች እና በአምስት ልዩ ወረዳዎች የሚያቋቁመው ክልል “ደቡብ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ ይሰጠዋል።
ነባሩ ክልል የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የሚለው መጠሪያ ወደ “ማዕከላዊ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ ለመቀየር መታቀዱተሰምቷል።
ሁለቱን ሥራዎች ለማከናወንም፣ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምሥረታ እና ነባሩን ክልል በአዲስ የማደራጀት ተግባር ማስፈጸሚያ የሚል ስያሜ ያለው ጽህፈት ቤት ተከፍቷል።
በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው፣ በደቡብ ክልል ለረጅም ጊዜ በኮሚዩኒኬሽን ባለሙያነት የሰሩት እና አሁን መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጀት ውስጥ የሚሰሩት አቶ ዳያሞ ዳሌ፣ የሚደራጁት ክልሎች እንደ ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አንድ ዋና ከተማ ላይኖራቸው ይችላል ይላሉ።
ለዚህም መነሻ ከሕዝበ ውሳኔው በኋላ በሚደራጀው እና ከኬንያ ድንበር እስከ ወላይታ የሚያካልለው አዲሱ ክልል እንደ ርዕሰ መስተዳደር ጽ/ቤት ያሉ “ወሳኝ” ተቋማት በአርባ ምንጭ ከተማ ላይ ሊመሰረት እንደሚችል “አዝማሚያው ያሳያል” ብለዋል።
ወላይታ ሶዶ፣ ሳውላ እና ጂንካም ቁልፍ መንግሥታዊ ተቋማትን በስራቸው ሊይዙ እንደሚችል ያነሱ ሲሆን፣ ልዩ ወረዳዎችም “አንዳንድ መሥሪያ ቤት ይድረስን” የሚል ጥያቄ እንዳላቸው “ጉምጉምታ አለ” ብለዋል።
ከውስጡ ሦስተኛ ክልልን ሊመሰረት የተቃረበው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም ሕዝበ ውሳኔው ሳይካሄደበት እንደ አዲስ ይደራጃል።
በስሩም ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ሀላባ፣ ሃዲያ፣ ከንባታ ጠምባሮ ዞኖች እና የየም ልዩ ወረዳን የሚያጠቃልል ይሆናል።
ይህንንም ለማድረግ፣ ክልሉ ሕገ መንግሥቱ ላይ ለውጥ ለማድረግ ተዘጋጅቷል።
የጉራጌ ዞን ምክር ቤት በክላስተር የመደራጀት ሃሳብን ውድቅ በማድረጉ እዚህ ውሳኔ ላይ ተደርሷል።
ክልሉም ለአስርት ዓመታት ከነበረበት ሐዋሳ ከተማ በ“ማዕከላዊ ኢትዮጵያ” ስር ወደሚካተቱ ከተሞች የሚሸጋገር ይሆናል።
ክልሉ ከአንድ በላይ ዋና ከተማ ሊኖረው እና የርዕሰ መስተዳድሩ መቀመጫም ሆሳዕና ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ስለሕዝበ ውሳኔው በጥቂቱ
- በስድስት ዞኖች (በኮንሶ፣ በወላይታ፣ በደቡብ ኦሞ፣ በጋሞ፣ በጌዲዮ እና በጎፋ) እንዲሁም በ5 ልዩ ወረዳዎች (በቡርጂ፣ በባስኬቶ፣ በአማሮ፣ በአሌ እና ዲራሼ) ይካሄዳል
- ሕዘበ ውሳኔውን ለማካሄድ 410 ሚሊዮን ብር ወጪ ይደረጋል
- በ31 ማስተባበሪያ ማዕከላት እና በ3 ሺህ 752 የምርጫ ጣቢያዎች ይከናወናል
- ለተፈናቃዮች 4 ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ይቋቋማሉ
- ከ11 ሺህ 400 በላይ አስፈጻሚዎች ይሳተፉበታል
- የሚመሰረተው ክልል “ደቡብ ኢትዮጵያ” የሚል ስያሜ ሊሰጠው ይችላል
- ነባሩ ክልል “ማዕከላዊ ኢትዮጵያ” በሚል ስያሜ እንደ አዲስ ይደራጃል
- “ማዕከላዊ ኢትዮጵያ” ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ሀላባ፣ ሃዲያ፣ ከንባታ ጠምባሮ ዞኖች እና የየም ልዩ ወረዳ የሚመሰሩት ነው
- “ማዕከላዊ ኢትዮጵያ” ሕዝበ ውሳኔ ሳይካሄድ በክልሉ ሕገ መንግሥት በሚደረግ ማሻሻያ ይደራጃል
የክልል ምሥረታ ምን ለውጥ ያመጣል?
አቶ ዳያሞ የመንግሥት ባለሥልጣናት ወደተወለዱበት አካባቢ እየሄዱ “ነጯን እርግብ ምረጡ” የሚል ቅስቀሳ እያካሄዱ ስለመሆናቸው ይናገራሉ።
ይህም ሕዝበ ውሳኔው በሕዝብ ተቀባይት እንዲኖረው ለማድረግ እንደሆነ የጠቀሱ ሲሆን፣ የአዲስ ክልል መደራጀት ከነዋሪዎች ሕይወት አኳያ ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት የላቸውም።
“ምክንያቱም ክልሉን ሲያስተዳድሩ የነበሩት ተመሳሳይ ፓርቲ እና ባለሥልጣናት ናቸው። ስለዚህ ከተማ ወደ እኛ ቀረበ ከሚል በስተቀር ብዙም ለውጥ ያመጣል የሚል ግምት የለኝም። መሠረታዊ ለውጥ የሚጠበቀው ወይ ፖሊሲ ወይ ፓርቲ ሲቀየር ነው” የሚሉት አቶ ዳያሞ ለውጥ ለማምጣት ክልል መመስረት የግድ አይደለም ይላሉ።
“ከታች ላለው ሕዝብ መሠረታዊ አገልግሎት ያለው ወረዳ እና ቀበሌ ላይ ነው። እዚያ ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ እና ሙስናን መከላከል ነው እንጂ ክልል ስለተፈጠረ ለውጥ አይኖርም” ሲሉ ይከራከራሉ።
የክልል መመሥረት እና የዋና ከተሞች ለዜጎች ቅርብ መሆንን ብዙም ለውጥ አያመጣም የሚሉት አቶ ዳያሞ፣ በዋናነት ለወረዳ አስተዳዳሪዎችና ካድሬዎች አመቺ ሁኔታን ከመፍጠር በስተቀር ለተራው ሕዝብ ጥቅሙ እምብዛም ነው ይላሉ።
“አርሶ አደሮች እና አርብቶ አደሮች ወደ ክልል ከተማ የሚያመላልሳቸው ጉዳይ የለም። ክልል ከሕዝብ አገልግሎት አንጻር ሩቅ እርከን ነው። ትክክለኛው አገልግሎት ለሕዝቡ የሚቀርበው በወረዳ እና በቀበሌ ነው።”
በሌላ በኩል አንድ ክልል ለመመሥረት ከተዘጋጁት 6 ዞኖች እና 5 ልዩ ወረዳዎች መካከል ጌዲዮ ዞን ከተቀሩት አካባቢዎች ጋር ምንም የየብስ ግንኙነት የለውም።
ዞኑ በደቡብ እና በምሥራቅ ከኦሮሚያ ክልል ጉጂ ዞን ጋር የሚዋሰን ሲሆን፣ በሰሜን በኩል ደግሞ ከሲዳማ ክልል ጋር ይወሰናል። ይህ ማለት በጌዲዮ ዞን እና በአማሮ ልዩ ወረዳ መካከል ከ50 ኪሎ ሜትር በላይ የሚሸፍን እና በኦሮሚያ ክልል ስር ያለ አካባቢ አለ።
አካባቢው በፀጥታ ችግርም የሚፈተን ነው።
ይህንን ውሳኔ በጌዲዮ ዞን ካሉ የተቃዋሚ ፓርቲ ፖለቲከኞች ቢቃወሙትም የዞኑ ምክር ቤት ይሁንታን ሰጥቶታል።
ሲዳማ ክልል እስኪ መሰረት ድረስ የየም ልዩ ወረዳ ከቀሪው የደቡብ ክልል ጋር በየብስ የማይተሳሰር ብቸኛው አካባቢ የነበረ ሲሆን በሲዳማ ክልል መመስረት ምክንያት ጌዲዮ ተመሳሳይ ዕጣ ገጥሞታል።
እነዚህን ሁኔታዎች በቀጣይ የሚመሰረቱት ክልሎች መፍትሄ ይፈልጉለታል ተብሎ ይጠበቃል።