የዩቲዩብ ተመልካች ለማግኘት ሲል ሆን ብሎ አውሮፕን እንዲከሰከስ ያደረገው አሜሪካዊ

ብዙ ተመልካች ለማግኘት ሲል ሆን ብሎ አውሮፕላን ወድቆ እንዲከሰከስ ያደረገው ዩቲዩበር ምርመራ በማደናቀፍ ጥፋተኛ መሆኑን ለማመን መስማማቱን የአሜሪካ ዐቃቤ ሕግ ገለጸ።

ግለሰቡ አደጋው እንዲከሰት ካደረገ በኋላ የመንግሥት ባለሥልጣናት የአደጋውን ምክንያት እንዳይመረምሩ ለማድረግ ማስረጃዎችን አውሮፕላኑ ከወደቀበት ስፍራ ማጥፋቱም ተገልጿል።

ቴሬቨር ጃኮብ የተባለው የ29 ዓመት ግለሰብ አውሮፕላኑ በአደጋ የወደቀ በማስመሰል የቀረጸውን ቪዲዮ ከሁለት ዓመት በፊት ዩቲዩብ ላይ አቅርቦ እስካሁን ከ2.9 ሚሊዮን በላይ ዕይታን አግኝቷል።

ጥፋቱን ለማመን ከዐቃቤ ሕግ ጋር በደረሰው ስምምነት መሠረት ግለሰቡ ቪዲዮውን የቀረጸው አንድ ምርትን ለማስተዋወቅ በደረሰው ስምምነት መሆኑን አመልክቷል።

ግለሰቡ በድርጊቱ አስከ 20 ዓመታት የሚደርስ እስር ሊጠብቀው ይችላል።

ፓይለት እና ከአውሮፕላን ላይ በፓራሹት ዘላይ የሆነው ቴሬቨር ጃኮብ የፌደራል መንግሥቱ በወደቀው አውሮፕላን ዙሪያ ምርመራ እንዳያካሂድ መረጃዎችን በመደበቅ እና በማጥፋት ወንጀል ጥፋተኛ መሆኑን በፍርድ ቤት ለማመን መስማማቱን የአሜሪካ ፍትሕ መሥሪያ ቤት አስታውቋል።

ግለሰቡ ቴሬቨር ጃኮብ ከሁለት ዓመት በፊት ከካሊፎርኒያ ሳንታ ባርባራ አየር ማረፊያ ብቻውን በሚያበራት አውሮፕላን ላይ ካሜራዎችን ገጥሞ የተነሳ ሲሆን፣ እራሱም ካሜራዎችን ይዞ አውሮፕላኗ አየር ላይ እንዳለች በፓራሹት ዘሎ በመውጣት ስትከሰከስ የሚያሳየውን አጠቃላይ ሂደት ቀርጿል።

አውሮፕላኗ ለበረራ ከተነሳች ከ35 ደቂቃዎች በኋላ ሎስ ፓድሬስ በተባለ ደን ውስጥ ነበር ወድቃ የተከሰከሰችው።

ቴሬቨር ጃኮብም በፓራሹት ወደ መሬት ካረፈ በኋላ ወደ ስፈራው በመሄድ በአውሮፕላኑ አካል ላይ በተገጠሙ ካሜራዎች የተቀረጹ ምስሎችን ሰብስቧል።

በዚህም እሱ ዘሎ ሲወጣ አውሮፕላኗ ወደ ምድር ስታሽቆለቁል እና ወድቃ ስተከሰከስ የሚያሳይ ቪዲዮ ቀርጾ በዩቲዩብ ላይ በመቶ ሺዎች ከዚያም በሚሊዮኖች ተመልካች ለማግኘት መቻሉ ተገልጿል።

በዩቲዩብ ላይ ቪዲዮውን የተመለከቱ አንዳንድ ሰዎችም አውሮፕላኗ የወደቀችው በአደጋ ሳይሆን ሆን ተብሎ ነው የሚል ጥርጣሪያቸውን ሲገልጹ ነበር።

ለዚህም ጃኮብ የመዝለያ ፓራሹት አድርጎ ተዘጋጅቶ እንደነበረ እና አውሮፕላኗን ላይ አደጋ ለማሳረፍ ምንም አይነት ጥረት አላደረገም በማለት ተናግረዋል።

ከአደጋው በኋላ የአሜሪካ የትራንስፖርት ደኅንነት ቦርድ ክስተቱን ሪፖርት ያደረገ ሲሆን፣ ባለሥልጣኑም የአውሮፕላኗን ስብርባሪ መሰብሰብ እንዳለበት ቢነገረውም ነገር ግን የት እንደወደቀች እንደማያውቅ ገልጾ ነበር ተብሏል።

ከዚያም በኋላ ወደ አደጋው ስፍራ በሄሊኮፕተር በመሄድ ስብርባሪውን አግኝቶ ከስፍራው እንዲነሳ አድርጎ አጥፍቷቸዋል በማለት የዐቃቤ ሕግ መግለጫ አመልክቷል።

ግለሰቡ በፈጸመው አደገኛ ድርጊት እና ለምርመራ የሚጠቅሙ መረጃዎችን በማጥፋቱ በሚቀጥሉት ሳምንታት ፍርድ ቤት ቀርቦ ጥፋተኝነቱን ለማመን ተስማምቷል።

ከዚሁ ድርጊት ጋር በተያያዘ ቴሬቨር ጃኮብ ባለፈው ዓመት የነበረው አውሮፕላን የማብረር ፈቃዱ ተሰርዞበታል።