ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ፈረንሳይ ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና ሰጠች
ፈረንሳይ ለፍልስጤም አገርነት በይፋ ዕውቅና ሰጠች።
በኒው ዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ጉባዔ ላይ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና ሰጥተዋል።
"አሁን ጊዜው የሰላም ነው። በጋዛ እየተካሄደ ያለው ጦርነት ትክክል አይደለም" ብለዋል።
በመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ዛሬ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የጆርዳን እና የካታር መሪዎችም ንግግር የሚያደርጉ ይሆናል።
ሰኞ ፈረንሳይና ሳዑዲ አረቢያ ባዘጋጁት የሁለት አገራት መፍትሔን የተመለከተ ውይይት ላይ አሜሪካ አልተገኘችም። ጀርመንና ጣልያንም ውይይቱን አልተካፈሉም።
በቀጣይ ቤልጂየም፣ ሉግዘምበርግ፣ ማልታ፣ አንዶራ እና ሳን ማሪኖ ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል። ዩኬ፣ ካናዳ እና አውስትራሊያ ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና ሰጥተዋል።
በጋዛ ባለው ሰብአዊ ቀውስና በዌስት ባንክ ያለው የሰፈራ መስፋፋት ምክንያት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እስራኤል ላይ የሚያደርሰው ጫና በርትቷል።
ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና መስጠት ሐማስን ማበረታታት ነው ስትል እስራኤል ነቅፋለች።
እስራኤል በጋዛ በምትፈጽመው ጥቃት ከ65,000 በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸው ተዘግቧል። የእስራኤል ወታደሮች ጋዛን ለመቆጣጠር ጥቃት መፈጸማቸውን ቀጥለዋል።
በጋዛ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለረሃብ ተጋልጠዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ማክሮን ጦርነቱ መቆም እንዳለበትና ታጋቾች መለቀቅ እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
"ማብቂያ የሌለው አጥፊ ጦርነት መገታት አለበት። ከኃያልነት በላይ መብትን ማክበር መቅደም አለበት" ብለዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በመካከለኛው ምሥራቅ ዘላቂ ሰላም ማስፈን አንደተሳነው ፕሬዝዳንቱ ጠቅሰዋል።
"የሁለት አገራት መፍትሔን ለመተግበር የተቻለንን ማድረግ አለብን። እስራኤል እና ፍልስጤም ጎን ለጎን በሰላም መኖር ይችላሉ" ብለዋል።
የሳዑዲ አረቢያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ፈይሰል ቢን ፋራህ አል ሳዑድ፣ በተባበሩት መንግሥታት ላይ ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሰልማንን ወክለው ባደረጉት ንግግር በቀጣናው ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን የሁለት አገራት መፍትሔ መተግበር አለበት ብለዋል።
የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዝዳንት አርሰላ ቮን ደር ሊን እንዳሉት የአውሮፓ ኅብረት ጋዛን መልሶ ለመገንባት የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል።
"ሁላችንም አሁን ከምናደርገው በበለጠ መሥራት አለብን። ለፍልስጤም ድጋፍ የሚያደርግ ቡድን እናቋቁማለን" ብለዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በጋዛ ያለው ሁኔታ "በሞራል፣ በሕግና በፖለቲካም ተቀባይነት የሌለው" መሆኑን ገልጸዋል።
በእስራኤላውያንና በፍልስጤማውያን መካከል ሰላም እንዲሰፍን ብቸኛው መፍትሔ ሁለት አገራት መመሥረት መሆኑን አስረግጠዋል።
የመንግሥታቱን ድርጅት ጉባዔ እንዳይታደሙ አሜሪካ ቪዛቸውን ያገደችው የፍልስጤም ፕሬዝዳንት መሐሙድ አባስ በቪድዮ ንግግር አድርገዋል።
ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደረግ የጠየቁ ሲሆን ጋዛን በማስተዳደር ረገድ ሐማስ ሚና እንደማይኖረውም ተናግረዋል።
ሐማስ መሣሪያዎቹን ለፍልስጤም አስተዳደር እንዲያስረክብም አሳስበዋል።
"የምንፈልገው መሣሪያ የሌለበት የተዋሀደ አገር ነው" ብለዋል።
ሐማስ በእስራኤል ላይ ያደረሰውን ጥቃት አውግዘው "የእኛና የእናንተም የወደፊት ሕይወት በሰላም የተሞላ መሆን አለበት። ጦርነትና ውድመት ይብቃ" ሲሉ ለእስራኤላውያን መልዕክት አስተላልፈዋል።