ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ምዕራባውያን ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና መስጠታቸውን ተከትሎ እስራኤል የበቀል እርምጃ እንዳትወስድ ዩኬ አሳሰበች
ምዕራባውያን አገራት ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና ከመስጠታቸው ጋር በተያያዘ እስራኤል የበቀል እርምጃ እንዳትወስድ ዩናይትድ ኪንግደም አሳሰበች።
ዩኬ ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና መስጠቷን ተከትሎ እስራኤል በበቀል እርምጃ ዌስት ባንክን በቁጥጥር ስር እንዳታውል የዩኬ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የቬት ኩፐር አስጠንቅቀዋል።
ኃላፊዋ ይህንን የተናገሩት ፈረንሳይ ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና ለመስጠት በተቃረበችበት ወቅት ነው።
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዣን-ኖኤል ባሮት "ዛሬ የሰላም ቀን ነው" ብለዋል። ለፍልስጤም ዕውቅና የመስጠት ውሳኔ "ለፈረንሳይ ዲፕሎማሲያዊ ድል ነው" ሲሉም አክለዋል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማኽሮን ለተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔያቸውን እንደሚያሳውቁ ጠቅሰው "ውሳኔው ለእስራኤል አደጋ አይሆንም። ለፍልስጤም ዕውቅና መስጠት ሐማስን ዕውቅና መንፈግ ነው። ሽብርና ነውጥ ለሚነቅፉ ፍልስጤማውያን ይሁንታ የሚሰጥ ነው" ብለዋል።
ዩኬ፣ ካናዳ እና አውስትራሊያ ለፍልስጤም የአገርነት ዕውቅና ሰጥተዋል።
የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ "ሽብርተኛነትን ማበረታታት ነው" ሲሉ ነቅፈዋል።
የሁለት አገራት መፍትሔ በመስጠት የጋዛን ጦርነት ለማስቆም የተባበሩት መንግሥታት ውይይት እንደሚያደርግ ይጠበቃል።
እስራኤል አሁንም በጋዛ ጥቃት መሰንዘሯን የቀጠለች ሲሆን ዛሬ ቢያንስ 20 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማኽሮን "ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና መስጠት የፖለቲካ መፍትሔ ያመጣል" ብለዋል።
ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና ከተሰጠ በኋላ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ይደረሳል ብለው እንደሚጠብቁ አስታውቀዋል። የታገቱ ሰዎች እንደሚለቀቁና ወደ ጋዛ ሰብአዊ እርዳታ እንደሚገባም ይጠብቃሉ።
በፈረንሳይ የአሜሪካ አምባሳደር የሆኑት የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ልጅ ኢቫንካ ትራምፕ ባለቤት ጄራርድ ኩሽነር፣ ማኽሮን በፈረንሳይ ፀረ ሴማዊነትነት ለመታገል በቂ እርምጃ አልወሰዱም ማለታቸውንም ማኽሮን ተችተዋል።
የዩኬ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ የቬት ኩፐር በበኩላቸው እስራኤል የበቀል እርምጃ እንዳትወስድ አሳስበዋል። ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና መሰጠቱን ምክንያት በማድረግ እስራኤል ግዛቶችን በግዳጅ በቁጥጥር ሥር እንዳታውልም አስጠንቅቀዋል።
የኔታንያሁ ቀኝ ዘመም ደጋፊዎች ግዛቶችን በግዳጅ መያዝን እንደሚደግፉ በይፋ ሲናገሩ ቆይተዋል። የእስራኤል የገንዘብ ሚኒስትር ቤዛሌል ስሞትኪክ በቅርቡ ባቀረቡት ዕቅድ ላይ የዌስት ባንክን 82 በመቶ ግዛት መጠቅለልን አካተዋል።