ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከአፍሪካ አገራት ኤርትራ እና ካሜሮን ብቻ ለምን ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና አልሰጡም?
በቅርቡ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ካናዳ እና አውስትራሊያ ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና ከሰጡ በኋላ ሌሎች በርካታ አገራት ይከተላሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የአፍሪካ አገራት የፍልስጤም አገርነትን እንዴት ይመለከቱታል?
እአአ በ1980ዎቹ በርካታ የአፍሪካ አገራት የፍልስጤሙ መሪ ያሲር አረፋት በአልጀርስ ነጻነታቸውን ካወጁ በኋላ ለፍልስጤም አገርነት እውቅና ሰጥተዋል።
እንደ ቶማስ ሳንካራ እና ኔልሰን ማንዴላ ያሉ መሪዎች የአፍሪካን የነጻነት ትግል ከፍልስጤማውያን ትግል ጋር አቻ አድርገው ነበር የሚመለከቱት።
ይሁን እንጂ ካሜሮን እና ኤርትራ ከዚህ በተለየ መቆምን መርጠዋል።
ለምንድን ነው እነዚህ ሁለት የአፍሪካ አገራት ለፍልስጤም አገርነት እውቅና ያልሰጡት?
ካሜሮን
የምዕራብ አፍሪካዋ አገር ካሜሮን ከእስራኤል ጋር ጥብቅ ቁርኝት አላት።
በጄኔቫ የአፍሪካ ደህንነት እና ስትራቴጂክ ጥናት የመከላከያ ዳይሬክተር የሆኑት ዳቪድ ኦቶ እስራኤል ካሜሮንን የምታያት በአፍሪካ እንዳላት አንዲት ጠንካራ አጋር ነው ይላሉ።
ኦቶ አክለውም "ካሜሮን ከእስራኤል ጋር ያላትን ግንኙነት፣ በዲፕሎማሲ ረገድ ማበላሸት አትፈልግም" ይላሉ።
የሁለቱ አገራት ግንኙነት እጅግ በጣም ጠንካራ ብቻ ሳይሆን በደህንነት ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ ጭምር ነው።
"እስራኤል የካሜሮንን መንግሥት በመከላከል ላይ ተሳትፋለች፤ አሁንም እየተከላከለችው ትገኛለች" ይላሉ።
እስራኤል የአገሪቱን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እንዲሁም የፕሬዚዳንቱን ደህንነት የሚጠብቀውን ልዩ ኃይል አሠልጥናለች፤ አስተምራለች።
"ካሜሮን ከእስራኤል ጋር በመሠረተችው ግንኙነት የተነሳ፣ ለእስራኤል በሁሉም ረገድ አጋር የሆነችው አሜሪካ በጀርባ በር እንድትደግፋት አድርጓታል"
ካሜሮን በፍልስጤም ላይ ያላት አቋም የተቃኘው በአገሪቱ ውስጥ እንግሊዘኛ ተናጋሪ ከሆኑ ተገንጣይ ቡድኖች ጋር ካላት ፍጥጫ ጋር የተዛመደ ሊሆን ይችላል።
"ለፍልስጤም እውቅና መስጠት በአገሪቱ ውስጥ ለተገንጣዮች እንቅስቃሴ እውቅና የመስጠት ጫናን ይፈጥራል። መንግሥት ደግሞ ካሜሮን አንድ እና የማትለያይ መሆኗን ግልጽ አድርጓል" ይላሉ ኦቶ።
የካሜሮን አቋም በብዛት የሚገለጸው በዝምታ እና በተጠና ጥንቃቄ ላይ ነው።የኤርትራ አቋም ግን በታሪክ በተለየ ሁኔታ የተቃኘ ለነጻነት ካደረገችው ትግል ጋር የተገናኘ ነው።
ኤርትራ
እአአ በ1988 ያሲር አረፋት ፍልስጤም ሉዓላዊት አገር መሆኗን አወጁ።
በዚህ ጊዜ ታድያ የአፍሪካ አገራትን ድጋፍ በእጅጉ ሽተው ነበር።
ከእነዚህ የአፍሪካ አገራት መካከል ደግሞ አንዷ ኢትዮጵያ ናት።
ኤርትራዊው የፖለቲካ ተንታኝ አብዱራሃማን ሰይድ "የአፍሪካውያን ዋና መቀመጫ ወይም በወቅቱ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በኋላ ላይ የአፍሪካ ኅብረት የተባለው መቀመጫውን ያደረገው በኢትዮጵያ አዲስ አበባ ነው" ይላሉ።
"የኢትዮጵያ ወታደራዊ አገዛዝ የሶቪየት ደጋፊ የነበረ በመሆኑ የፍልስጤምን መብቶች እና ትግል በጣም ይደግፍ ነበር።"
በወቅቱ ደግሞ ኤርትራ ነጻነቷን ለማግኘት ከኢትዮጵያ ጋር ውግያ እያደረገች ነበር።
የፖለቲካ ተንታኙ ሰይድ "በግልጽ በወቅቱ ኢትዮጵያ ኤርትራን በቁጥጥሯ ስር አድርጋ ነበር። ኤርትራውያን ደግሞ ከኢትዮጵያ ወረራ ነጻ ለመውጣት እየታገሉ፣ የትጥቅ ትግል እያደረጉ ነበር" ይላሉ።
"ለፍልስጤማውን ከኢትዮጵያ ጋር ማንኛውም ዓይነት ግንኙነት ለመመሥረት ከኤርትራውያን ራሳቸውን ማራቅ ይጠበቅባቸው ነበር። ያንንም ይመስለኛል ያሲር አረፋት ያደረጉት፤ ያ ደግሞ በኤርትራውያን እና በአሁኑ ፕሬዚዳንት ዘንድ በአጠቃላይ በበጎ አልታየም " ብለዋል።
ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለፍልስጤማውያን ጥያቄ ቀና አመለካከት በማሳየት እአአ በ2012 ፍልስጤም በተባበሩት መንግሥታት "አባል ያልሆነች ታዛቢ አገር" ሚና እንዲኖራት ድምጽ ሰጥተዋል።
ነገር ግን እንደ ኦስሎ አኮርድ ያለ ለፍልስጤም ራስን በራስ ማስተዳደር ውስን እድል የሰጠ፣ ዌስት ባንክን እና ጋዛን እንዲያስተዳድሩ እና ለነጻ አገርነት መሠረት የጣለውን የሰላም ጥረት ውድቅ አድርገዋል።
"እአአ በ1993 የኦስሎ ስምምነትን እርባና ቢስ የሆነ፣ የግጭቱን ምክንያት ከስሩ የማያፈታ ወይም የፍልስጤሞችን ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ የማይመልስ በማለት ውድቅ ካደረጉት መካከል የኤርትራው ፕሬዚዳንት ከቀዳሚዎቹ አንዱ ናቸው" ይላሉ አብዱራሃማን ሰይድ።
ፕሬዚዳንት ኢሳያስ የሁለት አገር መፍትሄን እንደማይደግፉም በግልጽ ተናግረዋል።
ነገር ግን 55 በመቶ የሆነው የአገሬው ሕዘብ የእስልምና እምነት ተከታይ በመሆኑ ግፊት ሳይደረግባቸው አይቀርም።
"ኤርትራ ነጻነቷን ለማግኘት ትግል አድርጋለች። ስለዚህ የነጻነት ትግልን ለመራ ወይንም የነጻነት ትግል አካል ለነበረ ሌላ ሕዘብ ነጻነቱን አለመደገፍ ከሞራል አንጻር ትክክል ሆኖ አይታይም። ከፍተኛ የሆነ ጫና ይገጥማቸዋል" ይላሉ የፖለቲካ ተንታኙ ሰይድ።
ቢቢሲ ሁለቱንም መንግሥታት በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን ቢጠይቅም ምላሽ አላገኘም።