ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አንዳንድ አገራት ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና ያልሰጡት ለምንድን ነው?
ፈረንሳይ እና ካናዳ በመጪው መስከረም ፍልስጤምን በአገርነት በይፋ ዕውቅና እንደሚሰጡ የአገራቱ መሪዎች በይፋ ተናግረዋል።
ፈረንሳይ እና ካናዳ ይህንን ውሳኔያቸውን ተግባራዊ የሚያደርጉ ከሆነ ለፍልስጤም በአገርነት ዕውቅና በመስጠት የመጀመሪያዎቹ የቡድን ሰባት አባል አገር ይሆናሉ።
ፍልስጤምን በአገርነት በይፋ እውቅና የመስጠት እወጃው የሚደረገው በኒው ዮርክ በሚካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ እንደሆነም ተነግሯል።
የፍልስጤም ባለሥልጣናት የአገራቱን ውሳኔ የተቀበሉ ሲሆን፣ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ግን ሐማስ መስከረም 26/2015 ዓ.ም. የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ እርምጃው "ሽብርተኝነትን የሚሸልም ነው" ብለዋል።
አሜሪካ የማክሮንን እርምጃ "በጽኑ እንደምትቃወመው" በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ማርኮ ሩቢዮ በኩል ያስታወቀች ሲሆን፤ ውሳኔውን "ግድየለሽ" ሲሉ ተችተውታል። እንዲሁም የካናዳን ውሳኔ ከአሜሪካ ጋር በተደረገው የንግድ ስምምነት ላይ አደጋ እንደሚደቅን አስጠንቅቀዋል።
ቡድን ሰባት (ጂ7) የሚባሉት የዓለማችን የኢኮኖሚ ኃያል አገራት ስብስብ ሲሆን እነዚህም ፈረንሳይን እና ካናዳን ጨምሮ፣ አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም፣ ጀርመን፣ ጣሊያን እና ጃፓን ናቸው።
እስራኤል ለፍልስጤም አገርነት እውቅና የማትሰጥ ሲሆን፣ አሁን ያለው የእስራኤል መንግሥት በዌስት ባንክ እና በጋዛ የፍልስጤም መንግሥት መመሥረቱ የእስራኤል ኅልውና ላይ ስጋት ይፈጥራል ሲል በመከራከር ትቃወማለች።
ኔታንያሁ በኤክስ ገጻቸው ላይ "በእነዚህ ሁኔታዎች ለፍልስጤም አገርነት ዕውቅና መስጠት ከእስራኤል ጋር በሰላም ለመኖር ሳይሆን እስራኤልን ለማጥፋት የመጀመሪያ እርምጃ ይሆናል። ግልጽ እናድርገው፤ ፍልስጤማውያን ከእስራኤል ጎን አገር አይፈልጉም። በእስራኤል ምትክ አገር ይፈልጋሉ" ሲሉ ለጥፈዋል።
ለፍልስጤምን እውቅና የሰጡት አገራት የትኞቹ ናቸው?
በአሁኑ ጊዜ lፍልስጤም ግዛት ከ193 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት መካከል ከ140 በላይ አገራት እውቅና ሰጥተዋታል።
በተባበሩት መንግሥታት የአረብ ቡድን አባላት፣ የእስልምና ትብብር ድርጅት እና የገለልተኛ አገራት ንቅናቄ አባላትን ጨምሮ እውቅና ሰጥተዋታል።
በግንቦት 2024 የፍልስጤም ግዛትን በይፋ እውቅና የሰጡትን ስፔን፣ አየርላንድ እና ኖርዌይን ጨምሮ አንዳንድ የአውሮፓ አገራትም እውቅና ሰጥተዋታል።
ከዚያ በፊት በጣት የሚቆጠሩ የአውሮፓ አገራት ብቻ ይህን አድርገዋል።
ከእነዚህም መካከል አብዛኞቹ እአአ በ1988 የሶቪየት ኅብረት አካል ነበሩ።
ሆኖም የእስራኤል ዋነኛ ደጋፊ የሆነችው ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮቿ ዩናይትድ ኪንግደም እና አውስትራሊያን ጨምሮ ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና አልሰጡም።
አውስትራሊያ "ሁለት አገራት ምሥረታ የሚለውን ሐሳብ ለማጠናከር" የፍልስጤምን አገርነት ልትደግፍ እንደምትችል አሳውቃለች።
አንዳንድ አገራት ፍልስጤምን እንደ አገር የማይቀበሉት ለምንድን ነው?
ፍልስጤምን እንደ አገር የማይቆጥሯት አገራት ይህን ያላደረጉት ከእስራኤል ጋር በድርድር ላይ የተመሠረት ስምምነት ስላልተደረሰ ነው ይላሉ።
በለንደን የኢኮኖሚክስ ትምህርት ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት እና የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካ ፕሮፌሰር የሆኑት ፋዋዝ ጌርገስ "ምንም እንኳ የፍልስጤም መንግሥት መመሥረት አለበት በሚለው ጉዳይ ላይ አዛኝ ብትመስልም፤ አሜሪካ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ቀጥተኛ ድርድር እንዲደረግ ትፈልጋለች። ይህ ደግሞ በሌላ መልኩ ለእስራኤል ፍልስጤም ላይ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት መስጠት ነው።"
በሁለቱ አገራት መካከል በ1990ዎቹ የሰላም ድርድር ተጀምሮ የሁለት አገራት ምሥረታ ሐሳብ የቀረበ ሲሆን፣ ይህ ሐሳብ እስራኤል እና ፍልስጤም ሁለት አገራት ሆነው በሰላም እንዲኖሩ የሚያልም ነው።
ነገር ግን ይህ የሰላም ድርድር ከአውሮፓውያኑ 2000 ወዲህ እየተቀዛቀዘ መምጣት ጀመረ። በ2014 በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል በዋሺንግተን የተካሄደው ድርድር ያለውጤት ተበተነ።
ሁለቱን አገራት የማያስሟሟቸው ነጥቦች የድንበር ጉዳይ እና የወደፊት የአገረ ፍልስጤም ዕጣ ፈንታ ጉዳይ ናቸው። የኢየሩሳሌም ጉዳይ እንዲሁም በእስራኤል ምሥረታ ጊዜ (በ1948-49 ጦርነት) የተሰደዱ የፍልስጤም ስደተኞች ነገርም አከራካሪ ናቸው።
እስራኤል፤ ፍልስጤም የተባበሩት መንግሥታት ሙሉ አባል የመሆኗን ጉዳይ ፈፅሞ አትቀበለውም።
በተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል አምባሳደር የሆኑት ጊላድ ኤርዳን ሐሳቡ ለጠረጴዛ መቅረቡ በራሱ "ለዘር ማጥፋት ሽብርተኞች" ትልቅ ድል ነው ብለዋል ሲል ኤኤፍፒ ዘግቦ ነበር።
አምባሳደሩ አክለውም በተለይ መስከረም 26/2015 ዓ.ም. ሐማስ በእስራኤል ላይ ከፈጸመው ጥቃት በኋላ ይህ መሆኑ ለቡድኑ ሽልማት እንደመስጠት ነው ብለዋል።
ከእስራኤል ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት መመሥረት የሚፈልጉ አገራት ለፍልስጤም የአገርነት እውቅና መስጠት አደጋ እንዳለው ያውቃሉ።
የእስራኤል አጋር አገራትን ጨምሮ አንዳንድ አገራት ደግሞ በ1933 በሞንቴቪድዮ ስምምነት መሠረት ፍልስጤም አገር ለመሆን የሚያበቃውን መሥፈርት አታሟላም ይላሉ።
መሥፈርቶቹ ቋሚ ሕዝብ፣ የተሰመረ ድንበር፣ መንግሥት እና ከሌሎች አገራት ጋር ግንኘኑት ለመመሥረት የሚያበቃ አቅም ናቸው።
ነገር ግን ሌሎች አገራት ደግሞ ፍልስጤም የአገራት እውቅና ከተሰጣት ራሷን የመቻል መብት ሊኖራት ይገባል ይላሉ።
ፍልስጤም በተባበሩት መንግሥታት ምን ቦታ አላት?
ፍልስጤም በተባበሩት መንግሥታት ያላት ቦታ አባል ያልሆነች ነገር ግን የታዛቢነት ሚና የሚል ነው።
በአውሮፓውያኑ 2011 ፍልስጤም የተባበሩት መንግሥታት ሙሉ አባል ለመሆን ጥያቄ አቅርባ ነበር። ነገር ግን በጊዜው የፀጥታው ምክር ቤት ድጋፍ ባለመስጠቱ ሐሳቡ ለድምፅ መስጠት አልቀረበም።
በ2012 ደግሞ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባዔ ፍልስጤም "አባል ያልሆነች ታዛቢ አገር" እንድትሆን ፈቀደ። ይህ ማለት ጉባዔው በሚያደርገው ውይይት ላይ መሳተፍ ትችላለች፤ ነገር ግን ድምፅ መስጠት አትችልም ማለት ነው።
ይህ ውሳኔ በወቅቱ በጋዛ ሰርጥ እና በዌስት ባንክ ተቀባይነት ቢያገኝም እስራኤል እና ዩናይትደ ስቴትስን አስቆጥቷል። በዚህ ውሳኔ መሠረት ፍልስጤም የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ችሎት፣ የዓለም አቀፉ የጦር ወንጀለኞች ፍርድ ቤት አባል እንድትሆን ሆነ።
በግንቦት 2024 የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ፍልስጤም በድርጅቱ ውስጥ ያላትን መብት ያሻሻለ ሲሆን፣ እንዲሁም እንደ አባል ተቀባይነት እንድታገኝ ጥያቄ ማቅረቡ የጋለ ክርክር አስከትሏል።
የውሳኔ ሃሳቡ ፍልስጤም ሙሉ በሙሉ በክርክሮች እንድትሳተፍ፣ አጀንዳዎች እንድታቀርብ እና ተወካዮቿ በኮሚቴ ውስጥ እንዲመረጡ አስችሏታል፤ ነገር ግን የመምረጥ መብት አልሰጣትም።
አባልነት ሊሰጥ የሚችለው በተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ብቻ ነው።
በዚያው ዓመት በሚያዝያ ወር ላይ ዩናይትድ ስቴትስ ከአምስቱ ቋሚ አባላት አንዷ እንደመሆኗ ፍልስጤምን እንደ አገር እውቅና እንድታገኝ አልጄሪያ ያቀረበችውን እና በበርካቶች ድጋፍ ያገኘውን ውሳኔ በመቃወም እርምጃውን "የተቻኮለ" ብለዋለች።
የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔዎች በሕግ አስገዳጅ ናቸው፣ ነገር ግን የጠቅላላ ጉባኤ ውሳኔዎች አይደሉም።
መቀመጫውን በዋሺንግተን ያደረገው የባለሙያዎች ቡድን (ቲንክ ታንክ) የፕሮግራም ዳይሬክተር ካሊድ ኤልጊንዲ "የተባበሩት መንግሥታት ሙሉ አባል መሆን ለፍልስጤማውያን የበለጠ ዲፕሎማሲያዊ ጥቅምን ይሰጣል፣ ይህም ውሳኔዎችን በቀጥታ ለመደገፍ፣ በጠቅላላ ጉባዔ ውስጥ ድምጽ ለመስጠት እና በመጨረሻም በፀጥታው ምክር ቤት ውስጥ መቀመጫ/ድምጽ መስጠት ትችላለች" ብለዋል።
"ነገር ግን እነዚህ ውሳኔዎች የሁለት አገራት ምሥረታ የሚለውን ሐሳብ እውን ያደርጉታል ማለት አይደለም። እሱ እውን የሚሆነው እስራኤል በኃይል ከያዘቻቸው ግዛቶች ለቃ ስትወጣ ነው" ሲሉ ያክላሉ።
"ፍልስጤም ሙሉ አባል የመሆን ሕልሟ ቢሳካ እንኳ ይህን ያህል ለውጥ አይኖረውም" የሚሉት ደግሞ በለንደን የስኩል ኦፍ ኦሪየንታል ኤንድ አፍሪካን ስተዲስ ምሑር የሆኑት ፕሮፌሰር ጊልበርት አርቻር ናቸው።
"እንዲሁ ትርጉም አልባ ድል ነው ነው የሚሆነው። ልቦለዳዊ አገረ-ፍስጤም ነው የምትሆነው። ምንም አቅም የሌለው 'የፍልስጤም አስተዳደር' ከ1967 ወረራ በተረፉ ሥፍራዎች ላይ ያለ፤ እስራኤል ላይ ጥገኛ የሆነ አስተዳደር ነው።"
ምሑሩ አክለውም ፍልስጤም ራስ ገዝ እና ነፃ ሆና ለማየት ገና ብዙ ዓመታት ይቀራሉ ይላሉ።