በእስራኤል የኦርቶዶክስ ትንሳኤ በዓል አከባበር ላይ ፖሊስ የጣለውን ገደብ የሃይማኖት መሪዎች ተቹ

በእየሩሳሌም የሚገኙ አቢያተ ክርስቲያናት መሪዎች በኦርቶዶክስ እምነት ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለውን የፋሲካ በዓል ለማክበር የእስራኤል ፖሊስ “ከባድና አላስፈላጊ ገደቦችን” ጥሏል አሉ።

መሪዎቹ ፓሊስ ዕሁድ በሚደረገው ስነ ስርዓት ላይ የሚታደሙ ምእመናን ቁጥር አምና ከነበረው 10 ሺህ ዘንድሮ ወደ 1 ሺህ 800 ዝቅ ማድረጉን ተናግረዋል።

በምስራቃዊ እየሩሳሌም ያለውን የደህንነት ሁኔታ የተቆጣጠረው ፖሊስ የምእመናን ደህንትና ነጻነት ለማረጋገጥ የተደረገ እርምጃ ነው ብሏል።

ሆኖም የሃይማኖት መሪዎች ምዕመናን ይህንን ገደብ ወደ ጎን ብለው በዓሉ ላይ እንዲገኙ እያሳሰቡ ነው።

የግሪክ ኦርቶዶክስ ሊቀ ጳጳስ አባ ማቲዎስ እና ሌሎች የእምነት መሪዎች በተገኙበት ትላንት በሰጡት መግለጫ የበዓሉን “ስነ ስርዓት እናከናውናለን እና ከኛ ጋር ማምለክ የሚፈልግ ምእመን ሁሉ እንዲታደም እጋብዛለሁ” ብለዋል።

ሊቀ ጳጳሱ "የእስራኤል ባለስልጣናት የፈለጉትን እዲያደርጉ እንተዋቸዋለን ቤተክርስቲያን ግን በነጻነትና በሰላማዊ መንገድ ታመልካለች" ብለዋል።

ይህ ጥሪ በጥንታዊቷ ከተማ ለሚገኙ እና ከሌላ ሀገራት ለተጓዙ ክርስቲያኖች ችግር እንዳይፈጥር ተሰግቷል። ፖሊሰ ተጨማሪ የፍተሻ ኬላዎችን ማዘጋጀቱም ታውቋል።

ባለፈው ዓመት በተከበረው የትንሳኤ በዓል ላይ የፖሊስ መኮንኖች ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን ለማስወጣት ሲሞክሩ ግጭት ሲፈጠር የሚያሳይ ቪዲዮ ተለቆ ነበር።

የቤተክርስቲያን መሪዎች ዘንድሮ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የእስራኤል ፖሊስ ገደብ መጣሉን ተናግረዋል።

የክርስትና እምነት ተከታዮች የትንሳኤ እንዲሁም የአይሁዶች የፋሲካ በዓል እና የእስልምና እምነት ተከታዮች የረመዳን ጾም በተመሳሳይ ወቅት በመምጣቱ ሳቢያ በእየሩሳሌም ውጥረቱ ከፍ እያለ ነው።

የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር የአይሁድ ጎብኚዎች አል አቅሳ የተሰኘውን መስጅድ በረመዳን ወር የመጨረሻዎቹ 10 ቀናት ውስጥ ከመጎብኘት እንደሚታገዱ አስታውቀዋል። ይህ ውሳኔም ከጸጥታ ጋር የተያያዘ ነው።

ሆኖም የቀኝ አክራሪው የብሄራዊ ደህንት ሚኒስትር ትችት ገጥሞታል።

አል አቅሳ ወይም ሙስሊሞች አል ሃራም እያሉ የሚጠሩት መስጅድ በአምነቱ ትልቅ ቦታ ከሚሰጣቸው ስፍራዎች ሶስተኛው ነው።

ስፍራው በአይሁዶች ደግሞ የቤተመቅደሱ ተራራ በመባል የሚታወቅ ሲሆን በእነሱም እምነት ቅዱስ ስፍራ ነው። በዚህም ምክንያት አለመግባባትን ለመቀነስ በሚል የእስራኤል መንግሥት ውሳኔውን ያሳለፈው።