ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሩሲያን የክተት ጥሪን ተከትሎ ዜጎች ወደ ሌሎች አገራት እየሸሹ መሆኑ ተነገረ
በዩክሬን ውስጥ በሚካሄደው ጦርነት እንዲሳተፉ የሩሲያ መንግሥት ያወጣውን የክተት ጥሪ ለማምለጥ ሩሲያውያን አገሪቱን ለቀው ለመውጣት እየሞከሩ ነው።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ረቡዕ ዕለት ከፊል ወታደራዊ የክተት ጥሪ በማድረግ ተጨማሪ 300,000 ሰዎች ጦሩን እንዲቀላቀሉ ካዘዙ በኋላ ከአገር ለመውጣት በድንበር አካባቢዎች የበርካቶች እንቅስቃሴ ታይቷል።
ለውትድርና ብቁ የሆኑ ወንዶች እየሸሹ ነው የሚለውን ዘገባ ግን የሩሲያ መንግሥት የተጋነነ ነው ሲል አስተባብሏል።
ሩሲያን ከጆርጂያ ጋር በሚያዋስነው ድንበር ከወታደራዊው ዘመቻ ለማምለጥ የሚሞክሩ ሰዎችን ጨምሮ በኪሎ ሜትሮች የሚረዝሙ ተሽከርካሪዎች ተሰልፈዋል።
ወደ ጎረቤት አገር ከሚሄዱት መካከል አንዳንዶቹ ብስክሌቶችን ተጠቅመው የመኪና ሰልፉን ለማለፍ እና በእግረኞች ላይ የተጣለውን እገዳ ለማምለጥ እየሞከሩ ነው።
አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ግለሰብ ድንበር ለማቋረጥ ለሰዓታት መጠበቁን ለቢቢሲ አስታውቋል።
ለ12 ሰዓታት ድንበር ላይ መጠበቁን የገለጸው ሌላኛው ግለሰብ ደግሞ ሩሲያን በመልቀቅ ትምህርቱን ለመቀጠል ምክንያት የሆነውን ከፊል የክተት ጥሪው መሆኑን ጠቅሷል።
ሩሲያውያን ያለቪዛ ከሚገቡባቸው ጥቂት ጎረቤት አገራት መካከል አንዷ ጆርጂያ ነች። ከሩሲያ ጋር 1,300 ኪሎ ሜትር ድንበር የምትጋራው ፊንላንድ ቪዛ ትጠይቃለች። በዚህ አቅጣጫም የሰዎች እንቅስቃሴ መጨመሩ ቢዘገብም ማስተናገድ በሚቻልበት ደረጃ ላይ እንዳለ ተናግራለች።
ሩሲያውያን በአውሮፕላን ሊጓዙባቸው ወደሚችሏቸው እንደ ኢስታንቡል፣ ቤልግሬድ እና ዱባይ ያሉ ቦታዎች ወታደራዊ ጥሪውን ተከትሎ የቲኬት ዋጋ ጨምሯል። አንዳንድ ጉዞዎች ሙሉ በሙሉ ተሽጠው አልቀዋል።
የቱርክ መገናኛ ብዙኃን መመለሻ የሌለው የጉዞ ቲኬት ሽያጭ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን እና ቪዛ ወደማይጠየቅባቸው አካባቢዎች የሚደረገው ጉዞ ዋጋ ወደ አንድ ሺህ ደላር ገደማ አሻቅቧል።
የጀርመን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር ሐሙስ ዕለት እንዳስታወቁት ክተቱን የሚሸሹ ሩሲያውያን ወደ አገራቸው መግባት ይቸላሉ።
ሊቱዌኒያ፣ ላቲቪያ፣ ኢስቶኒያ እና ቼክ ሪፐብሊክ የሚሸሹ ሩሲያውያንን አናስጠልልም በማለት የተለየ አቋም ይዘዋል።
የክተት ጥሪው ሞስኮ እና ሴንት ፒተርስበርግን ጨምሮ በታላላቅ የሩሲያ ከተሞች ተቃውሞን ቀስቅሷል። በዚህም 1,300 ሰዎች መታሰራቸውም ተዘግቧል።
ስለ ጉዳዩ የተጠየቁት የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ይህን ማድረጉ ከሕግ ጋር የሚጋጭ አይደለም ብለዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ሐሙስ ዕለት ባደረጉት ንግግር ሩሲያውያን ክተቱን እንዲቃወሙ አሳስበዋል።
በጦርነቱ ውስጥ የሞቱ የሩስያዊያንን በመጥቀስ “ተጨማሪ ሞት ትፈልጋላችሁ? አይሆንም? ስለዚህ ተቃወሙ፣ ሽሹ ወይም ለዩክሬን እጃችሁን ስጡ” ብለዋል።
የክተት አዋጁ በሩሲያ ውስጥ ባልተለመደ መልኩ ጠንካራ የተቃውሞ ምላሽ ገጥሞታል።
የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስቴር በመግለጫው የክተት ጥሪው “በሩሲያውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት የሌለው ሊሆን ይችላል” ብሏል።
“ፑቲን ኃይል ለማግኘት ትልቅ የፖለቲካ ኃላፊነት እየወሰደ ነው። እርምጃው ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ ለመዋጋት ፍላጎት ያላቸው ፈቃደኞችን እንዳሟጠጠች የሚያሳይ ነው” ብሏል።
ቢሳካ እንኳን አዳዲስ ምልምሎች ለውጊያ ዝግጁ ለመሆን ወራት ያስፈልጋቸዋል ተብሏል።
የሩሲያ ባለሥልጣናት ጥሪው የውትድርና አገልግሎት ያጠናቀቁትን ብቻ የሚመለከት እንደሚሆን ተናግረዋል።
የክተት ጥሪው በይፋ ከተገለጸው የበለጠ ሊሆን ይችላል የሚል ግምትም አለ።
ከጦርነቱ በኋላ በተወሰደውበት እርምጃ ሥራውን ወደ አውሮፓ ያዛወረው ገለልተኛው ኖቫያ ጋዜጣ በበኩሉ የቭላድሚር ፑቲን አዋጅ በምሥጢር የተያዘ እና የተደበቀ ተጨማሪ አንቀፅ ይዟል ሲል ዘግቧል።
ጋዜጣው በስም ያልተጠቀሰውን የመንግሥት ምንጭ በመጥቀስ አንቀጹ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ለመጥራት ይፈቅዳል ሲል ዘግቧል።